እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ከፍተኛ የሐማስ አዛዥን መግደሏን ገለፀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በጋዛ በሚንቀሳቀስ መኪና ላይ በፈጸመችው ጥቃት ከፍተኛ የሐማስ አዛዥን መግደሏን አስታወቀች።
የእስራኤል ጦር እና ደኅንነት ኤጀንሲ ሺን ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ በጋዛ ከተማ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ቃሳም ብርጌድ የጦር መሣሪያ ምርት ኃላፊ የነበረው ራኤድ ሳድ "መወገዱን" አስታውቀዋል።
ሳድ ከታዋቂዎቹ የቃሳም አዛዦች አንዱ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ከጋዛ ከተማ በስተምሥራቅ እስራኤላውያን ላይ ጥቃት በፈፀመበት ወቅት በርካታ ብርጌዶችን መርቷል።
በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለቢቢሲ በጥቃቱ አራት ሰዎች ሞተዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በርካታ መንገደኞችም በፍንዳታው ጉዳት እንደደረሰባቸው ጨምረው ገልጸዋል።
በጋዛ የሚገኙ የአካባቢው የሐማስ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጥቃቱ የሳድ ረዳት እንዲሁም አቡ ኢማድ አል-ላባን የተባሉ ዝቅተኛ ማዕረግ ያላቸው ባለሥልጣንም ተገድለዋል።
ቢቢሲ በጋዛ ተገኝቶ እንዳይዘግብ በእስራኤል መንግሥት የተከለከለ በመሆኑ የክስተቱን ዝርዝር ሁኔታ ማረጋገጥ አልቻለም።
የእስራኤል ጦር እና ደህንነት መስሪያ ቤቱ የጋራ መግለጫ አክሎ እንደገለጸው ሳድ በጋዛ ሰርጥ በሚጠመዱ ፈንጂዎች ምክንያት ለተገደሉት በርካታ ወታደሮች ሞት ተጠያቂ ነው።
ሳድ በጥቅምት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አዲስ የተቋቋመው አምስት አባላት ያሉት ወታደራዊ ምክር ቤት አባል እንደሆነ ይታመናል።
እስራኤል በተደጋጋሚ ሳድን ለመግደል ሙከራ አድርጋለች።
እአአ በመጋቢት 2024 የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ከተማ ባደረጉት ድንገተኛ ዘመቻ ወቅት እርሱን ለመያዝ ወይም ለመግደል ጥረት ማድረጋቸው ተዘግቧል።
በወቅቱ ምንጮች እንደገለጹት ሳድ ዒላማ በተደገረው ሕንፃ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ከጥቃቱ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ማምለጥ ችሏል።
ሳድ እስራኤል ለረዥም ጊዜ በጣም ከምትፈልጋቸው የሐማስ አባላት አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ጦሩ እርሱን ለመግደል ለሁለት አስርት ዓመታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱ የተፈፀመው በአሜሪካ የሚመራው የተኩስ አቁም ስምምነት ከፀደቀበት ከጥቅምት 10 ጀምሮ ጋዛን በከፈለው ቢጫ መስመር ተብሎ በሚጠራው እና በፍልስጤማውያን ቁጥጥር ስር ባለው አካባቢ ላይ ነው።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አካባቢ እና ከመስመሩ በስተምሥራቅ ያለውን ቦታ ይቆጣጠራል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመርያ ዙር የሰላም ዕቅድ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል ላይ በሐማስ መሪነት የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ 20 በሕይወት ያሉ እና 28 የሞቱ ታጋቾች እንዲለቀቁ ያስቻለ ነው።
ሐማስ በፈጸመው በዚህ ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ ከ250 በላይ ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።
በአሁኑ ወቅት ከአንድ የእስራኤል የፖሊስ ባልደረባ አስከሬን በስተቀር ሁሉም ታጋቾች ተለቅቀዋል።
የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከ70,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የሐማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ትኩረቱ ሐማስ ትጥቁን እንዲፈታ እና ጋዛን መልሶ ማልማት ስለሚቻልበት ሁለተኛ ዙር የትራምፕ ዕቅድ ላይ ነው።
ጋዛ በትራምፕ በሚመራው "የሰላም ቦርድ" ተቆጣጣሪነት "ከፖለቲካ ነጻ በሆነ እና በፍልስጤማውያን ምሁራን በሚዋቀር ኮሚቴ" ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር እንደምትመራ ዕቅድ ተቀምጧል።
ምንም እንኳን በጋዛ ይሰማራሉ ብሎ የሚጠበቁት የፀጥታ አካላት የሚውጣጡበት መንገድ ግልጽ ባይሆኑም ከተለያዩ አገራት የሚዋቀር አረጋጊ ኃይል ይኖራል ተብሏል።
በስተመጨረሻም ተሃድሶ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው የፍልስጤም አስተዳደር ግዛቱን እንዲቆጣጠር እና የእስራኤል ኃይሎች ለቅቀው እንዲወጡ ይደረጋል።
ከዚያ በኋላ "ወደ የፍልስጤም የራስን ዕድል በራስ መወሰን እና የአገርነት አስተማማኝ መንገድ ለመድረስ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይችላሉ"።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤም መንግሥት እንዲቋቋም የሚቀርቡትን ጥሪዎች በተደጋጋሚ ውድቅ በማድረጋቸው የዕቅዱ በርካታ ነጥቦች አወዛጋቢ ናቸው።
ትራምፕ እና ኔታንያሁ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት እአአ ታህሳስ 29 በአሜሪካ ይገናኛሉ።















