በጣሊያን ለሐማስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮ አሰባስበዋል የተባሉት 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የጣሊያን ፖሊስ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Stefano Guidi/Getty Images

የጣሊያን ፖሊስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሐማስ 7 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ አሰባስበዋል ያላቸውን ሰዎች በቁጥጥር ሥር አዋለ።

ገንዘቡ የተዋጣው ለፍልስጤማዊያን ሰላማዊ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ በሚል እንደሆነ ፖሊስ ያወጣው መግለጫ ያሳያል። ነገር ግን የተዋጣው ገንዘብ "በጣም ውስብስብ በሆነ መንገድ" ለታጣቂው ቡድን እንደተላከ አክሎ ይገልፃል።

ፖሊስ ካሰራቸው ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ በምርመራ ሂደቱ 8 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ንብረት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

የጣሊያን ፖሊስ እንደሚለው ተጠርጣሪዎቹ "ለሽብር ድርጊት አገልግሎት ላይ እንደዋለ የሚገመት የገንዘብ ዝውውር አድርገዋል" በሚል ነው የተከሰሱት።

የጣሊያን ፀረ-ሽብር ፖሊስ እና የፋይናንስ ፖሊስ በጥምር ባደረጉት ምርመራ ነው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የበቁት።

ምርመራው የተጀመረው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ሐማስ በእስራኤል ላይ ካደረሰው ጥቃት በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ከጥቃቱ በፊት "በርካታ አጠራጣሪ የገንዘብ ዝውውሮች ሪፖርት መደረጋቸውን" ተከትሎ ነው ፖሊስ ምርመራውን የጀመረው።

ፖሊስ "ውስብስብ" የተባለው የገንዘብ ማሰባሰብ በዋናነት በጣሊያኗ ጄኖዋ ግዛት እንዲሁም ሚላን ውስጥ በሚገኙ ቅርንጫፎች ውስጥ ይካሄዱ እንደነበረ ደርሼበታለሁ ብሏል።

"ተጠርጣሪዎቹ ለፍልስጤማዊያን ሰላማዊ ዜጎች የተዋጣ እርዳታ ሰብስበዋል። ነገር ግን 71 በመቶ የሚሆነው ገቢ ለሐማስ ወታደራዊ ክንፍ እንዲሁም ለአጥፍቶ ጠፊ ግለሰቦች ቤተሰቦች እና በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ለተያዙ ሰዎች የዋለ ነው" ይላል የፖሊስ መግለጫ።

የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ማቴዮ ፒያንቴዶሲ እንዳሉት ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በጣሊያም የፍልስጤም ማኅበረሰብ ፕሬዝደንት የሆነው ሞሐመድ ሀኑን ይገኝበታል።

ሞሐመድ ሁኑን ከዚህ ቀደም ለሐማስ የገንዘብ መዋጮ ያደርጋል የሚል ክስ ቀርቦበታል "ሐሰት ነው" የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር።

የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ በኤክስ ገፃቸው ለፖሊስ ምስጋና አቅርበው ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ እስካልተፈረደባቸው ድረስ "ወንጀለኛ" አይባሉም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።