ከ35 ዓመታት በላይ በምክር ቤት አባልነት ያገለገሉት የ83 ዓመቷ አሜሪካዊት ፖለቲከኛ በመጪው ምርጫ እወዳደራለሁ አሉ

የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከ35 ዓመታት በላይ በምክር ቤት ያገለገሉት የ83 ዓመቷ ፖለቲከኛ እና የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በመጪው የአሜሪካ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።

በአሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያ ሴት አፈ ጉባኤ በመሆን ታሪክ የሰሩት ናንሲ ፔሎሲ አገራቸው በመጪው 2016 ህዳር ወር ላይ በምታደርገው ምርጫም ተሳታፊ እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት።

ፖለቲከኛዋ በአውሮፓውያኑ 2007-2011 እንዲሁም 2019- 2013 ባሉት ወቅቶች ሁለት ጊዜ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜም ሳንፍራንሲስኮን ወክለው የተመረጡት በአውሮፓውያኑ 1987 ነው።

የሳቸው እንደገና ለመወዳዳር መወሰንም በአሜሪካ የፖለቲከኛ መሪዎች እድሜ በተመለከተ ክርክር እንዲያንሰራራ ያደርጋል ተብሏል።

“በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከተማችን ሳንፍራንሲስኮ እሴቶቻችን እንድናሳድግ የምትጠብቅን ወቅት ነው። ከተማዋ እንድታድግ የምንሰራበት ጊዜ ነው” ሲሉም ፖለቲከኛዋ ቀደም ሲል ትዊተር ተብሎ በሚጠራው በኤክስ ማህበራዊ ድረገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

“አገራችን አሜሪካ ሰንደቅ አላማዋን፣ ለሁሉም ነጻነት እና ፍትህ የሰፈነባት መሆኗን ለዓለም የምታሳይበት ወቅት ነው። ለዚያም ነው ለድጋሜ ለመመረጥ የምወዳደረው። ድምጽዎትንም እንዲሰጡኝ በአክብሮት የምጠይቀው” ሲሉም ነው ያሰፈሩት።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ታሪክ የሰሩት ናንሲ ፔሎሲ የበርካታ ፕሬዚዳንቶችን አጀንዳ ወደፊት በማምጣት እንዲሁም በማክሸፍ ወሳኝ ሚናም እንደተጫወቱም ይነገራል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የጤና ሽፋን እንዲሁም በስልጣን ላይ ያሉት የፕሬዚዳንት ባይደን የመሰረተ ልማቶች እና የአየር ንብረት ለውጦችን በተመለከተ የቀረቡ ረቂቅ ህጎች እንዲጸድቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግም እውቅና አትርፈዋል።

በተለይም የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን በነበሩበት ወቅት በቀጥታ በመሞገትም ይታወቃሉ።

ፖለቲከኛዋ መቃወም ብቻ ሳይሆን የአንድ መግለጫቸውንም ቅጂ ቀዳድው ጥለዋል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ሪፐብሊካኖች በጠባብ ምርጫ የምክር ቤቱን የበላይነት ስፍራ መያዛቸውን ተከትሎም አፈጉባዔዋ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል። ኬቨን ማካርቲም ከረዥም ሂደት በኋላም እሳቸውን በመተካት አፈ ጉባኤ ሆነዋል።

ፖለቲከኛዋ ከኃላፊነት ለመነሳት መወሰናቸው በመጪው ዓመት ጡረታ ይወጣሉ የሚል መላ ምቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ናንሲ ፔሎሲ በመጪው ምርጫ እንደሚወዳደሩ በኤክስ ገጻቸው በይፋ ከማወጃቸው በፊት በአንድ የቁርስ ፕሮግራም ለከፍተኛ አማካሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መናገራቸውም ተዘግቧል።