ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አስጊው የወንድ ብልት ካንሰር
ብራዚላዊው የ63 ዓመት አዛውንት ዣዎ ብልታቸው ላይ ቁስለት ተመልክተው ወደ ሕክምና የሄዱት እአአ በ2018 ነበር።
“ችግሩ የቆዳ መስፋትና የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሆነ ሐኪሞች ነገሩኝ” ይላሉ።
መድኃኒት ቢወስዱም ቁስለቱ እየተባባሰ ሄደ።
በቁስለቱ ምክንያት ትዳራቸው ይረበሽ ጀመር። ከባለቤታቸው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ አልቻሉም።
ችግሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ቆርጠው ተነሱ።
ለአምስት ዓመታት የሕክምና ባለሙያዎችን አማከሩ። የተለያዩ መድኃኒቶች ወሰዱ። መፍትሔ ግን አልተገኘም።
በ2023 የብልት ካንሰር (penile cancer) እንዳለባቸው ተነገራቸው።
“ለቤተሰቤ አስደንጋጭ ነበር። ከብልቴ ላይ የሚነሳ ክፍል እንዳለ ማወቅ ረበሻቸው። አካሌን እንዳጣሁ ተሰማኝ” ይላሉ።
“ከሰው ጋር በቀላሉ የሚወራበት የካንሰር ዓይነት አይደለም። ሰዎች ቀልድ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ” ሲሉም ስሜታቸውን ይገልጻሉ።
የወንድ ብልት ካንሰር እምብዛም የሚከሰት ባይሆንም በሕመሙ ምክንያት የሚከሰት ሞት ቁጥር በመላው ዓለም እየተበራከተ ይገኛል።
ከፍተኛ የሕሙማን ቁጥር የተመዘገበው በብራዚል ነው። ከ100 ሺህ ወንዶች ለሕመሙ የመጋለጥ መጠን 2.1 ነው።
ከ2012 እስከ 2022 ድረስ በብራዚል 21 ሺህ ወንዶች በበሽታው መያዛቸው ተመዝግቧል።
ከእነዚህ መካከል 4 ሺህ የሚሆኑት ሞተዋል። ከ5 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ብልታቸው በቀዶ ሕክምና ተቆርጧል።
ማራሆ የተባለው የብራዚል ግዛት በርካታ ሕሙማን የሚገኙበት ነው። በበሽታው የመያዝ ዕድል ከ100 ሺህ ወንዶች 6.1 ነው።
የሕመሙ የመጀመሪያው ምልክት ብልት ላይ የሚወጣ ጠባሳ ነው።
ጠባሳው ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ሲሆን፣ ጠንካራ ሽታም ይፈጥራል።
ሕመሙ በቶሎ ከተገኘ የመዳን ዕድል ይሰፋል። ሕክምናዎቹ ቀዶ ሕክምና እና የጨረር ሕክምናን ይጨምራሉ።
በአፋጣኝ ሕክምና ካልተደረገ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ብልትን ማስወገድ የግድ ሊሆን ይችላል። ከብልት በተጨማሪ የዘር ፍሬና ሌሎችም የብልት አካላት ሊወገዱ ይችላሉ።
ዣዎ በከፊል ብልትን የማስወገድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።
“እኔ ላይ ይደርሳል ብለን የማናስበው ነገር ነው። ሲደርስብንም ለሰው ሁሉ አንነግርም” ይላሉ።
“ቀዶ ሕክምና ያስፈራኝ ነበር። ሌላ አማራጭ ግን አልነበረም። ቀዶ ሕክምናውን ካደረግኩ በኋላ የነበሩት የመጀመሪያ ሳምንታት የሐዘን ነበሩ። የብልት አካልን ማጣት አስከፊ ነው” ሲሉ ወቅቱን ያስታውሳሉ።
በሳዎ ፖሎ በሚገኘው ካማርጎ ካንሰር ማዕከል በዩሮሎጂ ክፍል የሚሠሩት ቲያጎ ካማሎ ሙሩዎ እንደሚሉት ብልት በከፊል ብቻ ከተወገደ መሽናት ይቻላል።
“ሙሉ በሙሉ ብልት ከተቆረጠ ግን የሽንት ትቦ ቦታው ወደ መቀመጫ አካባቢ ይዞራል። ሕመምተኛው ተቀምጦ መሽናት ይኖርበታል” ሲሉ ያስረዳሉ።
ለሕመሙ ከሚያጋልጡ መካከል የብልት ጫፍ ቆዳ አለመለጠጥ (phimosis) እና ሲጋራ ማጤስ ይጠቀሳሉ።
የብራዚል የዩሮሎጂ ማኅበር አባል ሞሪሶዮ ዴነር ኮርዴሮ እንደሚሉት ንጽህና አለመጠበቅም አንደኛው ለሕመሙ የሚያጋልጥ ነው።
“የብልት ጫፍ ላይ ያለውን ቆዳ በአግባቡ አለማጽዳት አንደኛው ምክንያት ነው። ይህ ባክቴርያው እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” በማለት ያብራራሉ።
ሌላው የኤችፒቪ በሰውነት ውስጥ መኖር ነው። ይህ ቫይረስ ከብልት ካንሰር በተጨማሪ ለአፍ ካንሰርም የሚያጋልጥ ነው።
“የኤችፒቪ ክትባት መውሰድ አስፈላጊ ነው። ብራዚል ውስጥ ክትባቱ ቢኖርም የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ውስን ነው” ይላሉ ባለሙያው።
ክትባቱን የሚወስዱ ሴቶች ቁጥር 57 በመቶ ብቻ ሲሆን የወንዶች ቁጥር ደግሞ 40 በመቶ ብቻ ነው።
ሕመሙን ለመከላከል የክትባት ተደራሽነት መጠን 90 በመቶ መሆን አለበት።
ባለሙያው እንደሚያስረዱት፣ ስለ ክትባቱ ያለው የተዛባ ምልከታ ብዙዎች ክትባቱን እንዳይወስዱ ምክንያት ሆኗል።
ጄኤምአይአር የተባለው የኅብረተሰብ ጤና ተቆጣጣሪ አካል በ2022 ባወጣው መጽሔት ላይ የወንድ ብልት ካንሰር በ43 አገራት ያለውን የስርጭት መጠን ተንትኗል።
ከ2008 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ቀዳሚ ተጋላጭ አገር ኡጋንዳ ነበረች። መጠኑም በ100 ሺህ ወንዶች 2.2 በመቶ ነበር።
በሁለተኛ ደረጃ በ2.1 መጠን የተቀመጠችው ብራዚል ስትሆን በሦስተኛነት በ1.4 መጠን ታይላንድ ተቀምጣለች። ኩዌት ደግሞ በ0.1 መጠን ነው በዝርዝሩ የተካተተችው።
ጥናቱን የመሩት ሌዊን ፉ እና ቲያን ቲያን እንዳሉት፣ በቀዳሚነት በታዳጊ አገሮች ውስጥ ሕመሙ እየተስፋፋ ቢመጣም በአውሮፓ አራትም እየተስተዋለ ይገኛል።
ዓለም አቀፍ የካንሰር ምዝገባ ማዕከል እንደሚለው፣ በ2050 በዓለም የብልት ካንሰር ከ77 በመቶ በላይ ይጨምራል።
ሕመሙ ከ60 ዓመት በላይ በሆናቸው ወንዶች ላይ አብዝቶ ይከሰታል።
የሕክምና ባለሙያው እንደሚሉት የብልት ካንሰር መከላከል የሚቻል ሕመም ነው።
“በሁሉም ዕድሜ ያሉ ወንዶች ብልታቸውን በሳሙና እና በውሃ በየቀኑ እና ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ መታጠብ አለባቸው” ሲሉ ይመክራሉ።
የብልት ጫፍ ቆዳ የተሸበሸበ ሲሆን በቀዶ ሕክምና ማስወገድና ኮንዶም መጠቀምም እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ዣዎ ቀጣይ የሕክምና ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
“ድነሀል እንደምባል ተስፋ አለኝ። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሕመሙ ጠፍቶልኛል። ሆኖም ግን ግማሽ ብልቴን አጥቼ ለመኖር ተገድጃለሁ” ይላሉ።