ጋናዊው ጎልማሳ በእንቅልፍ ልቡ መራቢያ አካሉን ቆርጦ ለከፍተኛ ጉዳት ተዳረገ

ቢላዋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋናዊው አርሶ አደር ጎልማሳ ተኝቶ ሳለ መራቢያ አካሉን ከቆረጠ በኋላ ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጓል።

የ47 ዓመቱ ጎልማሳ በእንቅልፍ ልቡ እራሱን ከቆረጠ በኋላ በወንድ የዘር ፍሬው እና ብልቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ኮፊ አታ የተባለው አርሶ አድር ለቢቢሲ ሲናገር፤ መራቢያ አካሉን የቆረጠው በሕልሙ ሥጋ ሲቆርጥ ካየ በኋላ ነው።

“ወንበር ላይ እንደተቀመጥኩ ኃይለኛ እንቅልፍ ወሰደኝ። በሕልሜ ፊት ለፊቴ የነበረ ሥጋ ስቆርጥ አየሁ” በማለት ይናገራል።

አርሶ አደሩ በሕልሙ ሥጋ ሲቆርጥ ይመልከት እንጂ በእውነታው ግን የቆረጠው መራቢያ አካሉን ነበር።

“ቢላውን እንዴት አንስቼ እራሴን እንደቆረጥኩ አላውቅም። ግራ ተጋብቻለሁ” የሚለው ኮፊ አታ፤ ጉዳቱ ከደረሰበት በኋላ የድረሱልኝ ጩኸት ካሰማ በኋላ ጎረቤቶቹ መምጣታቸውን ይናገራል።

ሁለት ጎረቤቶቹ ከአታ መኖሪያ ቤት ዘልቀው ሲገቡ አርሶ አደሩ በአንድ ክፍል ውስጥ ብቻው በደም ተዘፍቆ እንዳገኙት ተነግሯል።

በጋና ትልቅ ከሚባሉ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ በሆነው ኮምፎ አኖክዬ ሆስፒታል ሕክምናውን እያደረገ የሚገኘው አርሶ አደር፤ ሐኪሞች ለሕክምናው ያስፈልግሃል ያሉትን ገንዘብ ለማግኘት እየተማጸነ ይገኛል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ጉዳቱ ያጋጠመው ኮፊ አታ “አሁን ላይ መርፌ እና ፈሳሽ ነገር ብቻ ነው እየሰጡኝ ያሉት። ቀዶ ሕክምና ማድረግ አለብኝ” በማለት የሕክምናውን ወጪ ለመሸፈን ገንዘብ እያሰባሰበ መሆኑን ለቢቢሲ ፒጅን ተናግሯል።