ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“የወሲብ ፊልም ጠዋት፣ ዕኩለ ቀን እና ማታ እመለከት ነበር”
ሻውን ፍሎሬስ የ11 ዓመት ልጅ እያለ ነበር ጓደኛው የወሲብ ፊልምን ያስተዋወቀው እና መመልከት የጀመረው።
የ30 ዓመቱ ወጣቱ ሻውን “ወዲያውኑ ነበር ቀልቤን የገዛው” ይላል።
“ዋው፣ ሰዎች ዓለማቸውን እየቀጩ በሚመስሉበት በዚህ ቦታ እያደረጉት ያለው ምንድን ነው?”
የሻውን የማወቅ ጉጉት፣ በፍጥነት ለማቆም አስቸጋሪ ወደ ሆነ ነገር ተለወጠ።
ጠዋት፣ ቀትር እና ማታ የወሲብ ቪድዮዎችን መመልከት ልክ “ጥርስን እንደ መፋቅ” የለመደው ድርጊት ሆኖ መዝለቁን ይገልጻል።
ሻውን ከቢቢሲ አይፕሌየር ጋር ባደረገው ቆይታ ወቅት “ምንም ነገር ለመሥራት አቅም ሳጣ አንድ ጉዳይ እንዳለ ተረዳሁ” ይላል።
“እግር ኳስ መጫወት አልፈልግም ነበር፤ ቤት ውስጥ መሆን ብቻ ነበር የምፈልገው፤ ነገር ግን የጥፋተኝነት እና የሀፍረት ስሜት አብሮት ነበር። እና ምንም ለማድረግ ብሞክር ማየቴን ማቆም አልቻልኩም። የሆነ ነገር እንዳለ ያወቅኩት ያኔ ነው።”
እንደዚህ ያሉ ቪድዮዎችን በሚመለከቱ ሁሉም ሰዎች ላይ ጤናማ ያልሆነ ስሜት ይፈጥራል ማለት ባይሆንም፣ ሾን ግን በዕይታ ባህሪው ምክንያት የተፈጠሩበት ስሜቶች ላይ ብቻውን አይደለም።
በዩናይትድ ኪንግደም በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው ኦፍኮም፣ በ2024 ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በግንቦት 2024 ብቻ በአገሪቱ ውስጥ 29 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች በበይነ መረብ የወሲብ ፊልሞችን ይመለከቱ ነበር።
በተጨማሪም፣ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሱስ ሕክምና ማዕከል የሆነው ዩኬኤቲ (UKAT) ይፋ ባደረገው አዲስ ጥናት መሠረት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሪታንያውያን 1.8 ሚሊዮን ያህል፣ አንዳንዶቹ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ፣ የወሲብ ፊልሞችን በመደበኛነት እንደሚመለከቱ ይገምታል።
በማገገሚያ ማዕከሉ የሕክምና ባለሙያዎች መሠረት፣ ብዙ ሰዎች የወሲብ ፊልሞችን ተገቢ ባልሆነ መልኩ በመመልከታቸው የተነሳ ድጋፍ ይፈልጋሉ።
ዶ/ር ፓውላ ሃል፣ ከዩኬ መንግሥት እውቅና የተሰጣት የወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት ሳይኮቴራፒስት ስትሆን ለንደን ውስጥ በሎሬል ሴንተር ትሠራለች።
ይህ ማዕከል በወሲብ እና በወሲብ ፊልሞች ሱስ የተጎዱ ሰዎችን በመርዳት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
“በሎሬል ሴንተር ውስጥ የወሲብ ፊልሞችን በሚመለከት ድጋፍ ፈልገው የሚመጡ ደንበኞች ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእጥፍ ጨምሯል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ዶ/ር ሃል አክላም እርዳታ የሚሹ ወጣቶች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ታስረዳለች።
“ከአስር ዓመት በፊት አብዛኛዎቹ ደንበኞቻችን በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ባለትዳር ወንዶች ነበሩ” ትላለች።
“ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ደንበኞቻችን በ20ዎቹ እና 30ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሆነዋል።ብዙዎቹ አላገቡም፤ ፍቅረኛም የላቸውም። በሕይወታቸው ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የወሲብ ፊልም የመመልከት ሱስ፣ በዚህም ፍቅረኛ የማግኘት ወይም ይዞ የመቀጠል ችግር ውስጥ መግባታቸውን የተገነዘቡ ናቸው።”
“አንዴ ከጀመሩ ማቆም በጣም ከባድ ነው”
የዩናይትድ ኪንግደም የሱስ ሕክምና ማዕከል (UKAT) መሪ ቴራፒስት የሆነው ሊ ፈርናንዴዝ የወሲብ ፊልም በመመልከት ሱስ ተጠምደው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ይገልጻል።
አሁን በየዕለቱ ከወሲብ ፊልም ዕይታቸው ጋር ከሚታገሉ ሰዎች፣ እርዳታ እፈልጋለሁ የሚል በርካታ ጥያቄዎችን ይቀበላሉ።
ከ2020 በፊት፣ በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጥያቄዎች ነበሩ የሚቀርቡላቸው።
ፈርናንዴዝ የቴክኖሎጂ መሻሻል እና የወሲብ ፊልሞችን በቀላሉ በድረገጾች ላይ ማግኘት መቻሉ፣ በሁሉም ዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎች በኦንላየን ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ፊልሞች እንዲመለከቱ እያደረገ መሆኑን ያስረዳል።
“አንድ ሰው 12 ዓመቱም ሆነ 60 ዓመቱ ስልኩን አውጥቶ ወደ ድረገጾች በመግባት የወሲብ ፊልም መመልከት በጣም ከባድ አይደለም” ካለ በኋላ፣ “በጣም አሳሳቢ ነው” ሲል ይገልጸዋል።
እንደ ፈርናንዴዝ ገለጻ፣ ሰዎች በኦንላየን ላይ የወሲብ ፊልሞችን ለመመልከት ካላቸው ምክንያቶች ውስጥ የማወቅ ጉጉት፣ መሰላቸት፣ ከጭንቀት እፎይታ ለማግኘት እና የወሲብ እርካታ ማጣት እንደሚገኙበት ያስቀምጣል።
በእነዚህ ምክንያቶች የወሲብ ፊልሞቸን መመልከት ሊጀምር ቢችልም፣ ፈርናንዴዝ “በጣም ሱስ አስያዥ” እንደሆነ ይገልጻል።
“ልክ እርካታ የማግኘት ዓይነት ስሜትን ያሟላል” ሲል ካስረዳ በኋላ፣ “አንድ ጊዜ ከጀመሩ ግን ለማቆም በጣም ከባድ ነው” ሲል ያክላል።
“የወሲብ ፊልሞች በተወሰኑ ድረገጾች ላይ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ቀርቷል”
ምንም እንኳ የወሲብ ፊልሞችን አዘውትሮ መመልከት እንደ ሱስ ቢታይም በምርመራ ወቅት ግን በዚያ መልክ አይታወቅም።
ከዚያ ይልቅ ችግር ያለበት በበይነ መረብ ላይ የወሲብ ፊልሞች አጠቃቀም (POPU) ወይም የሚረብሽ ባህሪ ተደርጎ ይመደባል።
ከወሲብ ፊልሞች ጋር ተደጋጋሚ የዕይታ ጊዜ ያላቸው እና የቅርብ ግንኙነት የመሠረቱ ሰዎች ላይ ያለው ውጤት ግን አሉታዊ መሆኑ ተለይቷል።
ታዳጊ ወጣቶች ጠንካራ ይዘት ያላቸውን እነዚህ ፊልሞችን በነጻ፣ በቀላሉ እያገኙ፣ እያዩ ማደጋቸው፣ ከመጠን በላይ ለዚህ ዓይነት ፊልም ተጽእኖ ተጋልጠው መቆየታቸው የሚያስከትለው ቀውስ ከሚገመተው በላይ ነው።
የዩኬ የሕፃናት ኮሚሽነር በቅርብ ይፋ ባደረገው ጥናት በ2023 10 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት በዘጠኝ ዓመታቸው የወሲብ ፊልም ያዩ ሲሆን፣ 27 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በ11 ዓመታቸው አይተዋል።
የወቅቱ የሕፃናት ኮሚሽነር ዴም ራቸል ደ ሱዛ “ወጣቶች ለወሲብ ፊልሞች ያላቸው ተጋላጭነት በጣም የተስፋፋ እና የተለመደ እንደሆነ ይነግሩኛል። ሕፃናት መጀመሪያ የወሲብ ፊልሞችን የሚያዩበት አማካይ ዕድሜ 13 ዓመታቸው ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የወሲብ ፊልሞቹ ከአሁን በኋላ በተወሰኑ ለአዋቂዎች ብቻ በተመደቡ ድረ-ገጾች ብቻ የተገደቡ አይደሉም። ልጆች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ኃይል የተቀላቀለበት፣ አዋራጅ ወይም ህመም የሚያስከትሉ ወሲባዊ ድርጊቶችን የሚያሳዩ የወሲብ ፊልሞችን ማየት እንደሚችሉ ይነግሩኛል።
“እንዲህ ዓይነቱን ነገርን የማየት ዕድል በጣም ሰፊ ነው። ባደረግሁት ጥናት ብዙ ጊዜ የወሲብ ፊልሞችን የሚመለከቱ ሰዎች ኃይል የተቀላቀለበት የፆታ ድርጊቶች ውስጥ የመሳተፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።”
ዴ ሱዛ አክለውም ለወጣቶች የወሲብ ፊልሞች ከእውነታው የራቁ መሆናቸውን እንዲረዱ ከሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ጋር ወሲብን የተመለከተ ትምህርት መስጠት “አስፈላጊ” ነው ብለዋል።
ያልተገባ የወሲብ ባህሪያትን ማከም ላይ የተሰማራው የሳይኮቴራፒስት ባለሙያው ሲልቫ ኔቭስ በለጋ ዕድሜ የወሲብ ፊልሞችን መመልከት አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይስማማል።
ነገር ግን ለወጣቶች ደረጃውን የጠበቀ የወሲብ ትምህርት ባለመሰጠቱ መረጃ ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ እንደሚያደርጋቸው ያስረዳል።
በፊልሞቹ ላይ የሚታዩት የተጋነኑ እና ከእውነታው ጋር የተራራቁ ድርጊቶች “ወሲብ ይህ ነው ብለው እንዲያስቡ” እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።
የ26 ዓመቷ ኮርትኒ ዳንኤላ ቦአቴንግ የወሲብ ፊልሞችን ማየት የጀመረችው የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ነበር።
ለእሷ ለዚህ ምክንያቱ በከፊል ትክክለኛ የወሲብ ትምህርት እጥረት በመኖሩ ነበር።
በትምህርት ቤት ውስጥ ከወሲብ ትምህርት ከማስተማር ይልቅ፣ በሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍለ ጊዜ ሥነ ተዋልዶ መማሯን ታስታውሳለች።
አክላም በወሲብ ዙሪያ ነውር ሆነው የተኮለኮሉት ሀሳቦችን ለመሞከር እና ለመረዳት የበለጠ ሳቢ አድርጎታል ትላለች።
“የወሲብ ቪዲዮዎችን መፈለግ ጀመርኩ” ስትል ገልጻለች። “ወደ አዲስ ዓለም ብርግድ ብሎ የተከፈተ፣ በጣም ሰፊ በር ነበር።”
“የወሲብ ፊልሞች ከእውነታው የራቁ ነገሮችን እንድጠብቅ አድርገውኛል”
ኮርትኒ ፊልሞቹን አንዳንድ ጊዜ ቅዳሜ እና እሁድ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ከትምህርት ቤት በፊት መመልከት ጀመረች። ቀስ እያለ ግን በየቀኑ ወደ ማየት ተሻጋገረች።
“ይህ በእኔ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር የተረዳሁት ያኔ ነበር፤ ምክንያቱም ፊልሙን መመልከቴን አብዝቼ ስለተጠመድኩበት” ትላለች።
ኮርትኒ ድንግልናዋን ያጣችው በ18 ዓመቷ ሲሆን፣ ሁኔታውንም “አስቀያሚ” በማለት ታስታውሰዋለች።
“እውነተኛ ሕይወት ከወሲብ ፊልም ወይንም ከግለ ወሲብ ካገኘሁት ደስታ ጋር እንደማይመሳሰል ተሰምቶኝ አያውቅም” ትላለች።
ኮርትኒ በሂደት የወሲብ ፊልም ላይ ጤናማ ያልሆነ ጥገኝነት ማዳበሯን ተገነዘበች።
“ዘወትር ፊልሞቹን ማየት ለማቆም እታገል ነበር” የምትለው ኮርትኒ በ20ዎቹ የዕድሜዋ መጀመሪያ ላይ የወሲብ ፊልም ማየት አቁማ ከወሲብ ለመራቅ ወሰነች።
ከእጮኛዋ ጋርም እስከ ሰርጋቸው ቀን ድረስ ለመታቀብ ቃል ገብተዋል።
ሻውን ከመጠን ያለፈ የወሲብ ፊልም ማየቱ አብዝቶ ግለ ወሲብ በመፈጸም “እንዲደክም” አድርጎታል።
“የወሲብ ፊልም ለራሴ ያለኝን ስሜት በማዛባት፣ በወሲብ ዙሪያ፣ በአካሌ፣ ስለ ብልቴ የተሳሳተ ምሥል ሰጠኝ” ይላል።
ባለሙያዎች ሰዎች ይህንን መረዳታቸው ጠቃሚ መሆኑን ይመክራሉ።
ኮርትኒ በበኩሏ “ብዙ የተማርኳቸውን ነገሮች እንድሰርዝ እንድደልዝ አድርጎኛል። ትክክለኛው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምን እንደሆነ መማር ነበረብኝ።
“ራሴን ከሌሎች ሴቶች አካል ጋር ሳላወዳድር፣ ተክለ ሰውነቴን መውደድ መማር ነበረብኝ። ሰዎችን፣ ወንዶችን እና ሴቶችን መውደድን መማር ነበረብኝ። እነሱን እንደ ወሲባዊ ቁስ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ማየት ነበረብኝ። ወደ ኋላ መመለስ ብችል ኖሮ አልጀምረውም ነበር” ትላለች።
ሻውን የወሲብ ፊልሞችን ማየት ለማቆም የወሰነው ውሳኔ በሕይወቱ ካሳለፋቸው ሁኔ “ምርጥ ውሳኔዎች” መካከል አንዱ ሲል ይገልጸዋል።
“የወሲብ ፊልሞች ሱሱ ያለኝን ግንኙነት እንዳጣ አድርጎኛል፤ እና አሁን በአጠቃላይ ከምወዳቸው እና ከምሳሳላቸው ሰዎች ጋር ለመገናኘት እየሞከርኩ ነው” ሲል ተናግሯል።