"ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም" ጠ/ሚ ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, PM Office
ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሐሙስ መጋቢት 11 2017 ዓ.ም. ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ "ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውጋት ፍላጎት የላትም" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ከተናገሩ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ሰፍኖ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ኢትዮጵያ "ያላት ፍላጎት እንነጋገር ነው" ያሉ ሲሆን፣ "በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ ሕዝቦች በሚጠቀሙበት መርህ፣ በገበያ መርህ እንወያይ. . . ውጊያ አያስፈልግም" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኤርትራ ሕዝብ የሚያስፈልገው ልማት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ተባብረን መልማት እና መስራት እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ ፍላጎት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።
"የቀይ ባሕር ፍላጎታችን ከሶማሌ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራ፣ ከኬንያ የሚያጣላ የሚያዋጋ መሆን የለበትም። የጋራ ሀብት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 5000 የባሕር ዳርቻ በቀጠናው ላይ እንደሚገኝ እና ለሁሉም በቂ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀይ ባሕር እና በአባይ ጉዳይ የመንግሥት አቋም ምን እንደሚመስል በጎረቤት አገራት ዘንድ ግልጽ ነበር ሲሉም አክለዋል።
"ሰሞኑን ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግጭት ይፈጠራል የሚል ስሞታዎች ይሰማሉ" ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ሕዝብ ማረጋገጥ የምፈልገው "ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ሊያስገኝላት የሚችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ውጥረት ውስጥ ገብታ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት ስምምነት ለ50 ዓመት የሚዘልቅ ሊዝ መሆኑ በወቅቱ የተገለፀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሶማሌላንድ ውስጥ የጦርና የንግድ ሠፈር እንዲኖራት የሚፈቅድ መሆኑም ተነግሮ ነበር።
ይህንን ስምምነት ተከትሎ ውጥረት ውስጥ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ መንግሥት አሸማጋይነት እርቅ አውርደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት አገር የባሕር በር ያስፈልጋታል ሲሉ ዛሬም በድጋሚ ተናግረዋል።
የኤርትራ ሕዝብ ልማት የሚፈልግ ሕዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "ኢትዮጵያ ላይ ማንም አገር ወረራ ሊፈጽም እና ከጀመርነው ሕልም ሊያስቆመን ይችላል የሚል ስጋት የለብንም" ሲሉ ተደምጠዋል።
በቂ ዝግጅት ስላለን ማንም አያስቆመንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዝግጅት የምናደርገው ጦርነት ለማስቆም ነው ሲሉ አክለዋል
"የባህር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ አቁሟል " ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ " የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አቋምም በዓለም ላይ ትልቅ አገር ሆኖ የባሕር በር የሌለው የለም ስለሆነም በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊሆን ይገባል የሚል ነው " ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በእርሳቸው የስልጣን ዘመን ተታኩሳ እንደማታውቅ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ምንም ዓይነት ትንኮሳ ከየትኛውም ወገን መኖር የለበትም። ትንኮሳ ካለ ምላሹ የከፋ ስለሚሆን" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በኢትዮጵያ ወገን ትንኮሳ አንደማይኖር አረጋግጠዋል።
የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕልውና ነው ሲሉ በድጋሚ የተናገሩት ዐቢይ፣ ". . . መለወጥ እና ማደግ የሚፈልግ ሕዝብ ጫፍ ጫፉ ተሰምሮለት እስር ቤት ሊቀመጥ አይችልም" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ይህንን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሚገነዘቡ የዓለም አቀፍ ኃይሎች እንዲያደራድሩ ጠይቀዋል።
"ይኼን ማንም ሠላም ወዳድ ነኝ የሚል መንግሥት፣ ግለሰብ፣ ቡድን ከወንድሞቻችን ጋር አነጋግሮን፣ በሕግ፣ በቢዝነስ ተርም የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ፣ ወንድሞቻችንም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስብል መፍትሄ እንዲፈጠር" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የወጪ ገቢ ምርቶቿን የምታንቀሳቅሰው 31 ኪሎ ሜትር በተዘረጋው የጂቡቲ ወደብ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት "የሕልውና ጉዳይ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት በምጽዋ እና አሰብ ላይ የባሕር ኃይል ባለቤት ነበረች።ይኹን እንጂ ኤርትራ እአአ 1993 ነጻ አገር መሆኗን ተከትሎ ፣ ወደብ እና የባህር ጠረፍ አልባ ሆናለች።












