ከ350 ዓመት በፊት በሰመጠችው መርከብ ወርቅና ሌሎች ውድ ቁሳቁሶች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Allen Exploration
ስኖራ ዲ ላ ማራቪላስ ትባላለች። የስፔን መርከብ ነበረች።
እንደ ጎርጎሮሶዊያኑ በጥር 04/1656 የዛሬ 350 ዓመት በአትላንቲክ ውቅያኖስ አደጋ ገጠማት።
ስፔን በእነዚያ ዘመናት ግዙፍ መርከቦችን ወደተየለያዩ የዓለም ክፍሎች ለንግድ ትልክ ነበር።
በአጭሩ ማራቪላስ እየተባለች የምትጠራው ይህች መርከብ ሌላ ጉዳት የደረሰበትን እና በጊዜው ውድ ዕቃዎችን ጭና የነበረችን መርከብ ጭነት አራግፋ፣ መልሳ በመጫን ንብረቱን ይዛ ወደ ስፔን ስትመለስ ነበር አደጋው ያጋጠማት።
ይህ አደጋ ዛሬ ኢኳዶር በምትባለው አገር አቅራቢያ ያጋጠመ ነበር።
በዚህ አደጋ ከ650 ተሳፋሪዎች በሕይወት የተረፉት 45ቱ ብቻ ነበሩ።
ባለፉት ሦስት ምዕተ ዓመታት ታዲያ የማራቪላን ሁኔታ ለማወቅ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም ምንም ፍንጭ ሳይገኝ ቀርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Allen Exploration
ብዙ ሃብትና ንብረት ጭና እንደነበረም ይታወቅ ስለነበረ የተለያዩ ቡድኖች አንዳችን ነገር ካገኘን በሚል ብዙ ሙከራዎን አድርገዋል።
ከባሃማስ ደሴት ጠረፍ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መስጠሟ ይታወቅ ስለነበረም ይህን ፍለጋ በተደራጀ መንገድ ለማካሄድ ቡድኖች ተቋቁመው ነበር።
ይህ ፍለጋ ለ350 ዓመታት ብቅ ጥልቅ እያለ ቀጥሎ ነበር።
በመጨረሻም ባለፉት ሁለት ዓመታት ይበልጥ በተደራጀ ሁኔታ ሥራ የጀመረው አሌን የፍለጋ ቡድን በለስ ቀንቶታል።
ይህ ቡድን የቅርስ፣ የቁፋሮና የፍለጋ ልዩ ባለሙያዎችን የያዘ ነው።
የቡድኑ መሥራችና በጎ አድራጊ ካርል አለን እንዳሉት ማራቪላስ የባሃማስ የባሕር ኃይል ታሪክ አንድ አካል ናት።
በዚህ መርከብ ፍለጋ ከተገኙ ሃብቶች መካከል የወርቅ ሰንሰለት ይገኝበታል። ይህ የወርቅ ሰንሰለት በቅዱስ ጄምስ መስቀል ያጌጠ ነው።
ስፔን በዚያ ዘመን የመርከብ ጉዞዎችን እና አዳዲስ ገበያዎችንና ሃብቶችን ፍለጋ በምታደርጋቸው ጉዞዎች ትታወቅ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Allen exploration
የፖርቹጋሉ አሳሽ ቫስኮ ደጋማ ሕንድ ለመድረስ የመጀሪያው አውሮፓዊ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ ሰው በ21 መርከቦች 8 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ከ1502 እስከ 1503 ድረስ አስከትሎ ተጉዟል።
ስፔንም ተመሳሳይ ጉዞዎችን የሚያደርጉ አሳሾች ነበሯት።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን ታዋቂ ከነበረችው ከዚህች የሰጠመች መርከብ ከወርቅ ሌላ በርካታ ውድ ሳንቲሞች ተገኝቷል።
እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮች፣ 2 ሜትር የሚጠጋ የወርቅ ሰንሰለትና 34 ኪሎ ግራም የሚመዝን ግግር ብር ተገኝቷል።
ይህ አለን የተባለውና በፍለጋ ላይ የተሠማራው ቡድን ከነዚህ ሃብቶች በተጨማሪ ከመርከቡ ጋር የተያያዙ በርካታ ሌሎች ቁሳቁሶችንም አግኝቷል።
ከእነዚህ መካከልም ልዩ የወይን ጠጅ ጠርሙሶችና ሌሎች የመጠጥ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።
ከእነዚህ ሁሉ የላቁ ናቸው የተባሉ በ12ቱ ደቀ መዛሙርት ምሥሎች የተወከሉ ጌጣጌጦች መገኘታቸው ነው።
ብዙዎቹ ቁሳቁሶች አሁን በበሓማስ ደሴት የባሕር ኃይል ሙዝየም ውስጥ ገብተው ለሕዝብ ዕይታ ቀርበዋል።
“በውቅያኖስ መሀል ላለች አገር ይህ ሃብት ይገባታል። ከባሕር ጋር ያላት ታሪኳም መታወቅ አለበት” ብለዋል የሙዚየሙ ዳይሬክተር ማይክል ፓትማን።
“ብዙ ሰዎች ሉካያን የተባሉት ነባር ሕዝቦች ከሺህ 300 ዓመት በፊት እዚህ መኖራቸውን ብዙ ሰው አያውቅም። 50ሺህ ነባር ሕዝቦች በስፔኖች ከዚህ መፈናቀላቸው አይታወቅልንም።
“እነዚህ ሕዝቦች ወደ ቬንዝዌላና ሌሎች አካባቢዎች ተገፍተው እንዲጠፉ መደረጉን ብዙ ሰው አያውቅም” ሲሉ በአገራቸው የመርከቧ ቅሪቶች መቀመጣቸው የሚኖረውን ፋይዳ አብራርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Allen Exploration












