ቼልሲ ከአርሴናል እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ቼልሲ ከአርሴናል

በለንደን ደርቢ ቼልሲ አርሰናልን የሚያስተናግድበት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሁለቱም ቡድኖች በሳምንቱ አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊግ ያስመዘገቡትን ትልቅ ውጤት ተከትሎ ጨዋታውን ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ግን ትኩረት ያደረገው በሊቨርፑል ላይ ነው።

"ሊቨርፑል ባለፈው ዓመት የትኛውንም ጨዋታ ያሸንፋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። በፎረስት ከደረሰበት የሦስት ለምንም ሽንፈት በኋላ ግን ነገሮች ተለውጠዋል" ብሏል።

ሱተን የሊቨርፑልን ጨምሮ በሳምንቱ መጨረሻ የሚከናወኑ ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ገምቷል።

ቅዳሜ

ብሬንትፎርድ ከ በርንሌይ

ብሬንትፎርድ ባለፈው ሳምንት ባለቀ ሰዓት ያከነውን ፍጹም ቅጣት ምት ባያባክን ከብራይተን ጋር አቻ መለያየት ይችል ነበር።

ቡድኑ በሜዳው ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፏል።

በርንሌይ ደግሞ ለመገመት አስቸጋሪ ከሆኑ ቡድኖች አንዱ ነው።

ቡድኑ መፋለም፣ ጥሩ መነሳሳት እና የተደራጀ ቢሆንም ጎል ማስቆጠር ላይ ክፍተት አለበት።

ግምት፡ 2 - 0

ማንቸስተር ሲቲ ከ ሊድስ ዩናይትድ

ሊድስ ባለፈው ሳምንት ከአስቶን ቪላ ጋር ነጠብ መጋራት የሚችልበትን ዕድል ቢኖረውም ተሸንፏል።

ማንቸስተር ሲቲ ወደ ጠንካራ አቋሙ የተመለሰ ቢምስልም ጥሩ ሳምንትን መሳለፍ አልቻለም።

በዚህ ጨዋታ ሲቲ በቀላሉ እንደሚያሸንፍ እጠብቃለሁ።

ግምት፡ 4 - 0

ሰንደርላንድ ከ በርንመዝ

በርንመዝ ከአንድናድ ተጫዋቾች መጎዳት ጋር በተያያዘ አቋሙ ወርዷል።

የአንቶኒ ሲሜንዮ ከጉዳት መመለስ ለቡድኑ ውጤታማነት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

ሰንደርላንድ ባለፈው ሳምንት በፉልሃም አንድ ለምንም ተሸንፏል።

ግምት፡ 1- 2

ኤቨርተን ከኒውካስል

ኤቨርተን ከ ኒውካስል

ዴቪድ ሞዬስ በኤቨርተን ጥሩ እየሠሩ ሲሆን ባለፈው ሳምንትም ማንቸስተር ዩናይትድን አሸንፈዋል።

ቡድኑ የጎል አስቆጣሪዎች ችግር አለበት።

ካሉት የተጫዋቾች ስብስብ አንጻር ኒውካስል ከሜዳው ውጭ ወጥ ሆነ አቋም ማሳየት እየከበደው ይገኛል።

ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ቶተንሃም ከፉልሃም

ቶተንሃም በሻምፒዮንስ ሊጉ ከፒኤስጂ ጋር ጥሩ ከመጫወቱ አንጻር ለፉልሃም ከባድ ሊሆንበት ይችላል።

ፉልሃም ወደ ወራጅ ቀጠና ላለመግባት ባለፈው ሳምንት ሰንደርላንድ ላይ ጣፋጭ ድል አስመዝገቧል።

ቶተንሃም በሜዳው ፉልሃም ደግሞ ከሜዳው ውጭ ጥሩ አይደሉም።

ግምት፡ 1 -1

እሑድ

ክሪስታል ፓላስ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከፍ ወይም ዝቅ ይላል እንጂ መሐል ላይ የመሆን ዝንባሌ እንደሌለው ከኤቨርተን ጋር ባለፈው ሳምንት አሳይቷል።

ሁለቱም ቡድኖች 3-4-2-1 አሰላለፍን ቢመርጡም የፓላስ ተጫዋቾች በለጠ የተዋሃዱ ይመስላሉ።

ዩናይትድ ከ2019 ወዲህ ሴልኸረስት ፓርክ ላይ አሸንፎ አያውቅም።

ይህ ውጤትም የተለየ አይሆንም።

ግምት፡ 1 - 0

አስቶን ቪላ ከዎልቭስ

አስቶን ቪላ ከ ዎልቭስ

ይህንን ጨዋታ ቪላ እንደሚያሽንፍ እገምታለሁ።

የቪላው አጥቂ ኦሊ ዋትኪንስ በጥሩ አቋሙ ለይ አለመገኘቱ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።

ዎልቭስ አሁን ካለበት የደረጃ ግርጌ በመነሳት በሊጉ ለመቆየት ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል።

ግምት፡ 2 - 0

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ብራይተን

ፎረስት ባለፈው ሳምንት አንፊልድ ላይ አስደናቂ ድል አስመዝግቧል።

ብዙዎች የሊቨርፑልን አቋም መውረድ ቢያነሱም ለፎረስት ተገቢው ክብር መሰጠት አለበት።

ብራይተን ጎል እንደሚያስቆጥር ስለማስብ ለመገመት ከባድ ጨዋታ ይሆናል።

ግምት፡ 1- 1

ዌስትሃም ከ ሊቨርፑል

ሊቨርፑል መሸነፉ የሚቀጥል ባይሆንም መቼ ማሸነፍ ይጀምራል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ይሆናል።

ማንቸስተር ሲቲ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ በመሸነፉ ውጤቱን ለመገመት ተቸግሬ ነበር።

ሊቨርፑል ምን ያህል ትሩ ቡድን መሆኑን ከግምት ባለማስገባት አሁን ባለው አቋም መገመትን እመርጣለሁ።

ዌስት ሃም በአዲሱ አሰልጣኝ ኑኖ እስፕሪንቶ ሳንቶ ስር ውጤታማ መሆን ጀምሯል።

ግምት፡ 2 - 1

ቼልሲ ከ አርሴናል

ይህ በሊጉ አናት ላይ በሚገኙ ሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግ ቸዋታ በመሆኑ ለመገመት ከባድ ይሆናል።

ባለፈው ሳምንት መድፈኞቹ ቶተንሃምን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈዋል።

አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ያላቸውን አስተሳሰብ ሳይቀይሩ ውጤታማ መሆን ጀምረዋል።

ቡድኑ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል የተሻለ መሆኑን ቢያሳይም የሚፈተንበት ጨዋታ ይጠብቀዋል።

ሚኬል አርቴታ ቡድን የትኛውንም ቡድን ማሸነፍ እንደሚችል በሻምፒዮንስ ሊግ ባየር ሙኒክ አሸንፎ አሳይቷል።

ቼልሲ ጥሩ መንቀሳቀስ እየቻለ ቢሆንም ከመድፈኞቹ ጋር ለዋንጫ ይፎካከራል ብዬ አላስብም።

ግምት፡ 0 - 2