የታዋቂው ደራሲ ሰልማን ሩሽዲን ዐይን ያጠፋው ግለሰብ የ25 ዓመት እስራት ተፈረደበት

ሩሽዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው ደራሲ ሰልማን ሩሽዲን በስለት ወግቶ አንድ ዐይናቸውን ያጠፋው ግለሰብ የ25 ዓመት እስራት ተፈረደበት።

ሐዲ ማትር የተባለው የ27 ዓመት ግለሰብ በግድያ ሙከራ ነው ክስ የቀረበበት።

እአአ በነሐሴ 2022 ሩሽዲ መድረክ ላይ ንግግር እያደረጉ ሳሉ ግለሰቡ በስለት ፊታቸውና አንገታቸውን በተደጋጋሚ ወግቷል።

ሩሽዲ አንድ ዐይናቸው ከመጥፋቱ ባሻገር ጉበታቸው የተጎዳ ሲሆን በነርቭ ሕመም ምክንያት እጃቸውም ፓራላይዝድ ሆኗል።

'ዘ ሳታኒክ ቨርስስ' የተባለው አነጋጋሪ መጽሐፋቸው በታተመ በ35ኛ ዓመቱ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።

ነብዩ መሐመድን በመጽሐፉ ባቀረቡበት መንገድ ምክንያት የግድያ ዛቻ ሲደርስባቸው ቆይቷል።

በግድያ ሙከራ ክስ የመጨረሻው ቅጣት የሆነው የ25 ዓመት እስራት ግለሰቡ ተፈርዶበታል።

ሩሽዲን ቃለ ምልልስ እያደረገላቸው የነበረው ሄንሪ ሪስ ላይ ጥቃት በመፈጸምም የተከሰሰ ሲሆን በዚህ ክስ የሰባት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

ሁለቱም ፍርዶች በተከታታይ በእስር ቤት በመቆየት የሚፈጸምበት ይሆናል።

አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው ተከሳሹ የንግግር ነጻነትን በመጥቀስ ሩሽዲን ተችቷል።

"ሰልማን ሩሽዲ ሌሎችን ይተቻል። ሌሎች ላይ ጉልበቱን ማሳየት ይፈልጋል። ያንን እኔ አልቀበልም" ብሏል ተከሳሹ።

ሩሽዲ ፍርዱ ሲተላለፍ አልተገኙም። ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ወቅት ለሞት የተቃረቡ መስሏቸው እንደነበር ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ተናግረዋል።

በኒው ዮርክ ጥቃት የፈጸመባቸው ሰው በቁጣ የተሞላ እንደነበር ገልጸዋል።

ሐዲ ማትር የተባለው የ27 ዓመት ግለሰብ ሩሽዲን 15 ጊዜ በስለት ጉንጫቸውን፣ ደረታቸውን፣ ዐይናቸውንና ጭናቸውን ወግቷል።

ዐቃቤ ሕግ ጥቃቱ ሩሽዲን ዒላማ ያደረገ ነው ሲል ተከራክሯል።

ጠበቃ ጄሰን ሽሚት "በቦታው ከነበሩት ሰዎች ባጠቃላይ ዒላማ የተደረገው ሩሽዲ ነበር" ብለዋል።

የተከሳሹ ጠበቃ በበኩላቸው ሩሽዲን ለመግደል ያለመ ጥቃት ነው የሚለውን አጣጥለው ተከራክረዋል።

ጥቃት አድራሹ "ሩሽዲ ጥሩ ሰው ነው ብዬ አላስብም። እስልምናን አንቋሿል" ብሏል።

የኢራኑ አያቶላ ካሚኒ በደራሲው ሩሽዲ ሞት ፍርድ ስለፈረዱበት ደስተኛ መሆኑን ገልጾም ነበር።

የሩሽዲ መጽሐፍ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል። ኢራን የሞት ፍርድ ካስተላለፈችባቸው በኋላ ደራሲው ለዘጠኝ ዓመታት ተደብቀው ኖረዋል።

እንግሊዛዊና ሕንዳዊው ሩሽዲ የግድያ ዛቻዎች ተቀዛቅዘዋል በሚል በአደባባይ መታየት ከጀመሩ በኋላ ነው ጥቃት የደረሰባቸው።

ከጥቃቱ በኋላ 'Knife: Meditations After an Attempted Murder' የተሰኘ የግል ታሪክ መጽሐፍ አሳትመዋል።