በኢንዶኔዥያ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ900 በላይ ደረሰ

ፍርስራሽ መካከል የሚታይ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኢንዶኔዥያ በቅርቡ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ900 በላይ ሲሻገር በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ አሁንም ደብዛቸው ጠፍቷል።

ባለፈው ሳምንት በማላካ ስትሬት ላይ በተከሰተ ያልተለመደ እና ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከ100,000 በላይ ቤቶች ወድመዋል። ይህም በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ክፍሎች ከባድ ዝናብ እና የመሬት መንሸራተት አስከትሏል።

በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ለመታደግ የሚደረገው ጥረት የቀጠለ ሲሆን፣ እርዳታ ወደ አንዳንድ ቦታዎች በአየር መድረስ አለበት።

የኢንዶኔዥያ ጎርፍ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እስያን ካጠቁት በርካታ የአየር ሁኔታ ክስተቶች አንዱ ሲሆን በስሪላንካ፣ ታይላንድ፣ ማሌዥያ እና ቬትናም የሟቾች ቁጥር ወደ 2,000 እየተጠጋ ነው።

በኢንዶኔዥያ ውስጥ በጣም ከተጎዱት አካባቢዎች አንዷ በሆነችው አቼህ ታሚያንግ፣ የተረፉ ሰዎች መንደሮች በፍጥነት በሚፈስ ጎርፍ ሙሉ በሙሉ እንደተወሰዱ ገልጸዋል።

በሊንታንግ ባዋህ መንደር ውስጥ አንዲት የተረፈች ሰው ለቢቢሲ የኢንዶኔዥያ አገልግሎት እንደተናገረችው ሰዎች በቤታቸው ጣሪያ ላይ ተቀምጠው ራሳቸውን አድነዋል።

ፍትሪያና እንዲህ ብላለች "እንዲሁም ከአራት ዓመት ልጆቻቸው ጋር ለሦስት ቀናት ሳይበሉና ሳይጠጡ በቤታቸው ጣሪያ ላይ የተረፉ ሰዎች ነበሩ።"

በመንደሯ ውስጥ ካሉት ቤቶች ውስጥ 90% የሚሆኑት ወድመዋል፣ በዚህም ሳቢያ 300 ቤተሰቦች መሄጃ አጥተዋል።

አንድ ሰው ጎርፉ ቤቱን እስከ ሁለተኛው ፎቅ ድረስ ሲያጥለቀልቅ እሱና ቤተሰቡ በጀልባ እንዴት እንደተፈናቀሉ ተናግሯል፣ ነገር ግን በአቅራቢያው ካለ መንደር እንደገና መሸሽ ነበረባቸው።

"በዚያ ምሽት፣ ተኝተን ሳለ፣ ውሃ በድንገት የምንተኛባቸውን ፍራሾች አራሰ። ነገር ግን ከፍ ያለ ቦታ ስላልነበረ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አልቻልንም" ሲል ተናግሯል።

"እንደ ዕድል ሆኖ፣ የምራቴ ቤት ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነበር። ስለዚህ ወደ ላይ ወጣን እና እዚያ ነው የተረፈነው።"