ዩክሬን ሞንጎሊያን ሊጎበኙ ያቀዱትን ፑቲንን በቁጥጥር ሥር እንድታውል ጥሪ አቀረበች

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዩክሬን በሚቀጥለው ሳምንት ሞንጎሊያን ሊጎበኙ ያቀዱትን የሩሲያን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በቁጥጥር ሥር እንድታውል ለአገሪቱ ባለስልጣናት ጥሪ አቀረበች።

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው ፑቲን ከትዕዛዙ በኋላ የአይሲሲ አባል የሆነች አገርን ለመጎብኘት ሲያቅዱ የመጀመሪያቸው ነው።

ፕሬዝዳንቱ ሕጻናትን በሕገወጥ መንገድ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው ሲል ነው ፍርድ ቤቱ የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው።

እነዚህ ወንጀሎች የተፈጸሙት ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከከፈተችበት ጀምሮ መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ የሞንጎሊያ ባለስልጣናት “በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መመሪያዎች የመገዛት ግዴታ አለባቸው” በማለት ለቢቢሲ ተናግረው፤ ነገር ግን ይህ ማለት በቁጥጥር ሥር ማዋል ብቻ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ክሬምሊን በበኩሉ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ስለታቀደው ጉብኝት “ስጋት የለኝም” ብሏል።

“ከሞንጎሊያ አጋሮቻችን ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት አለን” ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አክለውም “የፕሬዚዳንቱ እያንዳንዷጉብኝት በጥንቃቄ ዝግጅት ተደርጎበታል” ብለዋል።

የአይሲሲ ቃል አቀባይ ዶ/ር ፋዲ ኤል አብደላህ፣ ፍርድ ቤቱ ሞንጎሊያን ጨምሮ አባል አገራቱ በገቡበት የሮም ስምምነት መሰረት የመተባበር ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

ሆኖም በስምምነቱ መሰረት አባል አገራቱ የእስር ትዕዛዝን ተፈጻሚ ለማድረግ ከሌሎች አገራት ጋር የገቡትን ስምምነት የሚጥስ ከሆነ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብትን የሚተላለፍ ከሆነ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አይጠበቁም።

ሆኖም ከእነዚህ ውጭ “አባል አገራቱ የማይተባበሩ ከሆነ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ጉዳዩን አጣርተው ለምክር ቤቱ ማሳወቅ ይችላሉ። ምክር ቤቱ ተገቢ ነው ብሎ ያመነውን ማንኛውንም እርምጃ ሊወስድ ይችላል” ብለዋል ዶክተር ፋዲ።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሞንጎሊያ “ቭላድሚር ፑቲን የጦር ወንጀለኛ መሆናቸውን” እንደምታውቅ ተስፋ አድርገው ባለስልጣናቱ በሄግ ለሚገኘው ለአይሲሲ አቃቤ ሕግ አሳልፈው እንዲሰጡ ጠይቋል።

ቢቢሲ በለንደን የሚገኘውን የሞንጎሊያን ኤምባሲ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ፑቲን ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪካ ሊያደርጉት የነበረውን የመሪዎች ጉባኤ ጉዞ መሰረዛቸው ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ ፈራሚ አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፑቲንን በቁጥጥር ሥር እንድታውል የጠየቃት ሲሆን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ሩሲያ ይህንን ጦርነት እንደማወጅ እንደምትቆጥረው አስጠንቅቀው ነበር።

ፕሬዚዳንት ፑቲን የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸውን የመሰረዝ ውሳኔ በጋራ የተወሰነ መሆኑን ራማፎሳ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ከፕሬዝዳንት ፑቲን በተጨማሪ የሩሲያ የሕጻናት መብት ኮሚሽነር ማሪያ ሎቮቫ-ቤሎቫም በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተፈላጊ ሰው ሆነዋል።

በፕሬዝዳንቱም ሆነ በኮሚሽነሯ ላይ የፍርድ ቤቱ የእስር ትዕዛዝ ቢወጣም፣ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ሥልጣን ግን የለውም።

ይህ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚያወጣው ትዕዛዝ ተፈጻሚ የመሆን መብት ያለው ባቋቋሙት እና ስምምነት በፈረሙ አገራት ውስጥ ብቻ ነው።

ሩሲያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ አይደለችም፤ ስለዚህ የፕሬዝዳንት ፑቲን ለፍርድ ቤቱ ተላልፎ የመሰጠት ጉዳይ የመነመነ ነው።

ሩሲያ በበኩሏ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ምንም ትርጉም የለውም ብላለች።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በተደጋጋሚ የሚቀርቡባትን መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

ክሬምሊን ዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሥልጣን እንደማይቀበል እና በዚያም ለመታዘዝ ምንም ዓይነት ግዴታ እንደሌለበት በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ቆይቷል።