ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥንታዊ ገዳማትን ለመታደግ የሚሠሩት ሴቶች
የአየር ንብረት ለውጥ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ የቲቤት ገዳማት ሕልውናን አደጋ ውስጥ ከቷል።
የቲቤት ነዋሪዎች ግን ገዳማቱን ለመታደግ እየሞከሩ ነው።
ካግ ኮዴ ገዳም ከጥንታዊ ገዳማት አንዱ ነው። የተሠራው በዳላጊሪ ተራራማ ሥፍራ ነው። በቲቤትና ኔፓል ድንበር ላይ ይገኛል።
ታሺ ኩንጋ መነኩሴ ነው። ሪንፖሼ የተባለውን የእምነት መሪ (ጉሩ) አፈ ታሪክ ያስታውሳል።
በአፈ ታሪኩ መሠረት ሰይጣን በቲቤት ገዳም ቀውስ ያስነሳል። ጉሩው ሰይጣኑን በኔፓል ደቡባዊ አካባቢ ወዳለ አካባቢ ያባርረዋል።
የሰይጣኑን ቅሪተ አካል በተራራማው አካባቢም ይቀብረዋል። ሙስታግ በተባለው በዚህ ተራራ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ሰይጣኑ ተቀብሮበታል የተባለውን አካባቢ ያከብሩታል።
“የሰይጣኑ ልብ ያለበት ቦታ ላይ ነው ሎ ማንታንግ የተገነባው። ይህም እአአ በ1380 ነው” ይላል መነኩሴው።
በዚህ አካባቢ ብዙ ገዳማት አሉ።
በአካባቢው የሚኖሩት ቀደምት ማኅበረሰቦች ሎባስ ይባላሉ። በቲቤት ተራራ ለዘመናት ኖረዋል።
ጎንፓስ ብለው የሚጠሩት ይህ ተራራማ አካባቢ እጅግ የሚያከብሩት ሥፍራ ነው።
በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ ገዳማት ይገኙበታል። እነዚህ ገዳማት መጎዳት የጀመሩት ከሁለት አሠርታት ወዲህ ነው።
የጉዳታቸው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአውሎ ንፋስና ዝናብ ከመጠን በላይ መሆን አፈሩ እንዲሸረሸርና ገዳማቱም እንዲጎዱ አድርጓል። የገዳማቱ ጣሪያዎች ማፍሰስ ጀምረዋል።
መነኩሴው እንደሚለው፣ በቡዲሂስቶች ሃይማኖት መሠረት በገዳማቱ ያሉት ሥዕሎችና ቅርሶች እንደ አማልክት ይቆጠራሉ።
“እነዚህ የእምነቱ መሠረቶች እየተጎዱ ነው። የተጎዱ አማልክት ደግሞ ልናመልክ አንችልም” ይላል።
“ማንም ቅርሳችንን ሊጠግን አልቻለም። አማልክቶቹ በዚህ ተቆጥተዋል ብለን እናምናለን” ሲልም ያክላል።
እነዚህ የቡዲስት ገዳማት የቲቤት ባህል ማዕከል ናቸው። ቅርሶችን ጠብቀው ያቆዩም ናቸው።
ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥ ይህንን የዘመናት ቅርስ እያወደመ ይገኛል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በቅርስ ጥገና ልምድ እያዳበሩ ነው። ሥዕሎቹን ለማደስ ይሞክራሉ።
የሚያፈሱ ጣሪያዎችን እየጠገኑም ነው። ጣሪያዎች በድጋሚ ውሃ እንዳያፈሱ በእንጨት ይጠግኗቸዋል።
የቅርስ እድሳቱ ዋና ኃላፊ ሉዊጂ ፊጌኒ ነው። በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ወደ ቅርስ ጠጋኞች እየለወጠ መሆኑን ይናገራል።
አርሶ አደሮቹ ብሩሽን ከሸራ አገናኝተው ባያውቁም በረዥም ሥልጠና ቅርስ ጥገና ውስጥ ገብተዋል።
“ከ15ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተሠሩ ሥዕሎችን እንዲጠግኑ ለማድረግ ጊዜ ወስዷል። በስተመጨረሻ ግን ተሳክቷል” ይላል ሉዊጂ።
በአካባቢው ካለው የቱሪስት ፍሰት አንጻር ጭምርም ቅርሶቹን ጠብቆ ማቆየት ግድ ሆኗል።
የቅርስ እድሳት ላይ መሳተፍ የጀመሩት 10 ሰዎች ተሰባስበው ነበር። አሁን 45 ደርሰዋል። አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው።
መጀመሪያ ላይ በዚህ ቡድን ውስጥ ሴቶችን ለማሳተፍ ፈቃደኛነቱ አልነበረም።
በአካባቢው ባህል መሠረት ሴቶች የተቀደሰ ነገር እንዲነኩ አይፈቀድም።
ኋላ ላይ ግን ሴቶችን በቅርስ እድሳቱ ማሳተፍ ተጀመረ።
“ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ዓመታት የዘለቀ ውይይት አድርገን ነው ሴቶችን ለማሳተፍ የቻልነው” ይላል ሉዊጂ።
በቲቤት ያገቡ ሴቶች እንደ ማብሰል፣ ማጽዳት ያሉ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶች ይሰጧቸዋል።
የ40 ዓመቷ ታሺ ማንግሞ፣ ከብት በማገድ እና ዕጽዋት በመሰብሰብ ነበር አብዛኛውን ጊዜ የምታሳልፈው። ገቢዋ ብዙም አልነበረም።
ቅርስ የማደስ ትምህርት መሰጠት ሲጀምር ያለማንገራገር ተመዘገበች።
“ሴቶች ከቤት ውስጥ ሥራዎች እንድንወጣ አስችሎናል። እዚህ ሥራ ውስጥ ባንገባ ኖሮ ሕይወት ባለበት ይቆም ነበር” ትላለች።
ሌላዋ የ42 ዓመት ቅርስ ጠጋኝ ዶልማ ተስሪንግ፣ ሥነ ጥበብና ቅርስ እድሳት ተምራለች።
በዚህ ሥራ የቲቤትን ቅርስና ባህል ከመጠበቅ ባሻገር መንፈሳዊ ጥቅም እንደምታገኝ ታምናለች።
“የተበላሹ የአማልክት ምሥሎችን መጠገን አካባቢው ያለውን ዋጋ ይጨምራል። ምን ያህል እየጣርን እንደሆነ ማየት ይቻላል” ትላለች።
የአየር ንብረት ለውጥ አሁንም ለአካባቢው ስጋት ነው። የሂማልያ ተራራዎች ለከፍተኛ ሙቀት መጨመር ተጋላጭ ከሆኑ መካከል ነው።
ዝናብም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ያሳድራል። የተራዘመ ድርቅም በአካባቢው ይስተዋላል።
አምና የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው መጠኑን ባለፈ ዝናብ ምክንያት ወንዞች እየሞሉ ነው።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ለተሻለ ሕይወት ወደ ከተማ እየፈለሰም ነው።
ታሺ ጉሩንግ እዛው በአካባቢው ቆይተው ቅርስ እያደሱ ለመኖር ከመረጡ አንዱ ነው።
አሁን የሥነ ጥበብ ማዕከል ባለቤት ሆኗል። የተለያዩ የቡድሀ ቅርሳ ቅርሶችን ያሳያል።
ከሥነ ጥበብ ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ ልጆቹን ያስተምራል።
“እነዚህ ገዳማት ባይኖሩ ኖሮ እኔም እንደ ጓደኞቼ ወደ ውጭ አገር እሰደድ ነበር” ይላል።
አብዛኞቹ በቅርስ እድሳት የተሰማሩት ሴቶች በሥራቸው አማካይነት አካባቢው እየታደሰ እንደሆነ ያምናሉ።
በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው በአካባቢው ጠላት ሆኖ ያለው ሰይጣን ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ለውጥ እንደሆነም ይናገራሉ።
“ባህላችንን መታደግ ካለብን ተባብረን ገዳማትን ማዳን አለብን” የሚሉትም ለዚህ ነው።