ናይጄሪያዊው ዶክተር የባለቤቱን የእህት ልጅ በመድፈር ወንጀል የዕድሜ ልክ እስር ተፈረደበት

በናይጄሪያ ዕውቅ የካንሰር ሕክምና ክሊኒክ ኃላፊ እና ሐኪም በፈጸመው የመድፈር ወንጀል ዕድሜ ይፍታህ ተፈረደበት።

ሐኪሙ ዶ/ር ኦሉፌሚ ኦላሊዬ ይህ ብይን የተጣለበት ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችን የባለቤቱን የእህት ልጅ በመድፈሩ ነው።

ሐኪሙ ይህን ጸያፍ ድርጊት ለአንድ ዓመት ያህል ሲፈጽም እንደነበር ተደርሶበታል።

በመጨረሻ አደጊዋ ለሾፌር እና ለደፋሪው ባለቤት ጥቆማ በመስጠቷ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶበታል።

ሐኪሙ ዶ/ር ኦሉፌሚ ኦላሊዬ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲል ተከራክሯል።

ነገር ግን የሌጎስ ፍርድ ቤት ነውረኛ ድርጊት መፈጸሙን በማስረጃ አረጋግጦ የዕድሜ ልክ አስር በይኖበታል።

ዶ/ር ኦላሊዬ የኦፕቲማል ኬር ፋውንዴሽን ዋና ኃላፊ ነበር። ድርጅቱ ለዜጎች ነጻ የጡት እና የማሕጸን ካንሰር ምርመራ እና ሕክምና በመስጠት ይታወቃል።

ዶክተሩ በቁጥጥር ሥር የዋለው ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ነበር።

በሐኪሙ ጥቃት ሲደርስባት የነበረችው ታዳጊ አሁን 18 ዓመት ሞልቷታል።

የሐኪሙ ባለቤት ለፍርድ ቤት እንዳስረዳችው ዶ/ር አላሊዮ ልጂቱን በሚደፍርበት ጊዜ ለሌላ ሰው ከተናገረች እንደሚገድላት ያስፈራራት ነበር።

ሐኪሙ ይቺን ወጣት ልቅ የወሲብ ፊልሞችን እንድትመለከት ያስገድዳትም ነበር ተብሏል።

ሐኪሙ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሎ እስከመጨረሻው የተከራከረ ሲሆን፣ ማስረጃዎችን የተመለከቱት እና ትናንት ማክሰኞ ፍርድ የሰጡት ዳኛ ራሕማን ኦሼዲ ወንጀለኛው “ጭራሽ ጸጸት የሚባል ያልፈጠረበት” ሲሉ ፍርዱን አክብደውበታል።

ሐኪሙ ይከራከር የነበረው ተጠቂዋ ሐሰተኛ ቃል እየሰጠች ያለችው በባለቤቱ ተገዳ ነው በሚል ነው። “ባለቤቴ ደግሞ ንብረቴን ለመውረስ ስለምትፈልግ ነው ይህን ሁሉ ታሪክ ያቀነባበረችው” ይላል።

የሐኪሙ ጠበቃ ለፍርድ ማቅለያ እንዲሆን ዶክተሩ በካንሰር ሕክምና ሕብረተሰቡን ማገልገሉን ቢጠቅሱም፣ ዳኛው ግን ይህ የናይጄሪያ ፍርድ ቤት ጾታዊ ጥቃት ላይ ያለውን ጠንካራ አቋም ማሳያ እና ማስተማሪያ ይሆናል በሚል ሐኪሙን የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ፈርደውበታል።

ሐኪሙ ይግባኝ ስለመጠየቁ የተባለ ነገር የለም።