የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምርጫው ዙሪያ ዛሬ የሚሰጠው ውሳኔ በጉጉት ይጠበቃል

ዳኛ ማርታ ኮሜ

ከሳምንታት በፊት የተካሄደውን የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ በቀረበለት ቅሬታ ዙሪያ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ውሳኔውን ያስተላልፋል።

የአገሪቱ የምርጫ እና ድንበር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳን ዊሊያም ሩቶን አብላጫ ድምጽ አግኝተዋል በማለት ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሲል ማወጁ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የሩቶ ተቀናቃኝ ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደዋል።

ለቀናት የሁለቱንም ወገን ሃሳብ ሲያዳምጥ የነበረው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ የሚሰጠው ውሳኔ በኬንያውያን ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።

የራይላ ኦዲንጋ ጠበቆች በምርጫው ሂደት ተአማኒነት የጎደላቸው አሠራሮች በማጋጠማቸው ፍርድ ቤቱ የምርጫ ውጤቱን እንዲሽር ሞግተዋል።

የዊሊያም ሩቶ እና የምርጫ ኮሚሽኑ ጠበቆች በበኩላቸው ምርጫው ስልመጭበርበሩ ምንም ማስረጃ አልቀረበም በሚል ውጤቱ እንዲጸና ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ እስካሳለፍነው አርብ ነሐሴ 27/2014 ዓ.ም. ድረስ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ሲያዳምጥ ቆይቶ፤ ዳኞች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ውሳኔ ለማስተላለፍ በአንድ ቦታ መክተማቸው ታውቋል።

በጉጉት እየተጠበቀ ያለው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኬንያን ፖለቲካ ገጽታ ይቀይራል ተብሎ ይታመናል።

ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት የጸጥታ አካላት በስፋት ተሰማርተዋል።

ወደ ፍርድ ቤቱ የሚያመሩ መንገዶች ለትራፊክ ዝግ ሆነዋል።

ብዙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በጊዜ ወደ ቤት እንሚልኩ ይጠበቃል።

ግጭት ሊቀሰቀስባቸው ይችላሉ ተብለው በተለዩ አካባቢዎችም የጸጥታ አካላት በስፋት ተሰማርተዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ ህገ ወጥ እና ያልተገቡ አሠራሮች ነበሩ በሚል የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫውን ውጤት ውድቅ አድርጎ ነበር።