በግሪክ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው በደረሰ አደጋ ቢያንስ 32 ሰዎች ሞቱ

አደጋው የደረሰበት ሥፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሰሜን ግሪክ ሁለት ባቡሮች በመጋጨታቸው በደረሰው አደጋ ቢያንስ 32 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት አስታወቀ።

የነፍስ አድን ሠራተኞች በላሪሳ ከተማ አቅራቢያ ከተጋጩት ባቡሮች ተሳፋሪዎቹን ለማውጣት እየተረባረቡ ነው።

350 መንገደኞቹን አሳፍሮ ሲጓዝ እንደነበር የተገለጸው ባቡር ከእቃ መጫኛ ባቡር ጋር ተጋጭቶ ነው አደጋው የደረሰው።

በአካባቢው የዜና ምንጭ ድረ ገጾች ላይ የወጡ ምስሎች፣ ከተቆራረጡ የባቡሩ ፉርጎዎች ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።

በአደጋው ቦታ የነፍስ አድን ሥራ ለመስራትም 150 የእሳት አደጋ ሠራተኞች እና 40 አምቡላንሶች መሰማራታቸውን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ገልጿል።

በቴሰሎንኪ እና ላሪሳ መካከል ይጓዝ ከነበረው የመንገደኞች ባቡር ጋር የተፈጠረው ግጭት መንስዔ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

ስቴርጊኦስ ሚኔሲስ የተባሉ አንድ ተሳፋሪ ስለተፈጠረው ሁኔታ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሲያስረዱ “ከፍተኛ ፍንዳታ ሰማን። የአስር ሰከንድ ቅዠት ነበር። ከዚያ ተገለበጥን። ድንጋጤ ነበር። የኤሌክትሪክ ኬብሎች በእሳት የተያያዙት ወዲያውኑ ነበር” ብለዋል።

“እሳት በግራም በቀኝም በኩል ነበር። ለ10 እና ለ15 ደቂቃዎች ትርምስ ነበር። ሰዎች ይጮኻሉ። መስታወቶች ይሰባበራሉ። ዘለን ያመለጥንበት ቦታ ከፍታ 2 ሜትር ነበር። ምን ማድረግ እንችል ነበር?” ሲሉ እኝህ ተሳፋሪ ሕይወታቸውን እንዴት እንዳተረፉ ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው አንግሎስ ቲያሞራስ የተባሉ መንገደኛም ግጭቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ያህል እንደተሰማቸው ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ላዞስ የተባሉ መንገደኛም ያጋጠማቸው አደጋ በጣም አስደንጋጭ እንደነበር ለፕሮቶቴማ ጋዜጣ ተናግረዋል።

የቴሳሊይ ክልል አስተዳዳሪ በበኩላቸው የተከሰተው በጣም አስከፊ ግጭት መሆኑን ገልጸዋል።

የእሳት አደጋ መካላከያ ተቋም ቃል አቀባይ ቫሲሊስ ቫርታኮይያኒስም ግጭቱ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ለነፍስ አድን ሠራተኞችም በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።