ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጁቬንቱሱ አማካይ ፖል ፖግባ አበረታች መድኃኒት ወስዷል ተብሎ ለአራት ዓመት ከእግር ኳስ ታገደ
የጁቬንቱሱ አማካይ ፖል ፖግባ አበረታች መድኃኒት ወስዷል ተብሎ ለአራት ዓመታት ከእግር ኳስ ታገደ።
ፖግባ ከውሳኔው በኋላ “በጣም አዝኛለሁ፣ ደንግጫለሁ፣ ልቤ ተሰብሯል” ሲል መግለጫ ለቋል።
ፈረንሳዊው የ30 ዓመት አማካይ ባለፈው መስከረም ሰውነቱ ውስጥ ከተለመደው ከፍ ያለ ‘ቴስቴስትሮን’ ተገኝቷል ተብሎ በጊዜያዊነት ከሜዳ ታግዶ ነበር።
“በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቴ የገነባሁት ሁሉ ተንዶብኛል” ብሏል ፖግባ ባወጣው መግለጫ።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይት አማካይ ውሳኔው በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ይፋ አድርጓል።
ፖግባ ባለፈው ነሐሤ መጨረሻ ጁቬንቱስ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያውን ጨዋታ ካደረገ በኋላ ነው በነሲብ ምርመራ የተደረገበት።
የጣሊያን ብሔራዊ ፀረ-አበረታች መድኃኒት ችሎት ውጤቱን መርምሮ ተጫዋቹ አራት ዓመት ከሜዳ እንዲታገድ የሚል ምክረ-ሐሳብ አቅርቧል።
የጣሊያኑ ክለብ ጁቬንቱስ ችሎቱ ሐሙስ ዕለት ውሳኔውን እንዳሳወቀው ለቢቢሲ ገልጧል።
ፖግባ በመግለጫው ውሳኔው “ትክልል አለመሆኑን” ገልጦ “አውቄ አሊያም ሆነ ብዬ አበረታች መድኃኒት ወስጄ አላውቅም” ብሏል።
አክሎ “ከሕግ ውጣት ነፃ ስሆን ነገሮች ግልጥ መሆን ይጀምራሉ” የሚል መልዕክት አስተላልፏል።
“እንደ ፕሮፌሽናል አትሌት ብቃቴን ለመጨመር በሚል የተከለከለ ነገር ወስጄ አላውቅም። የወከልኳቸው ቡድኖችን የሚያንቋሽሽ፤ ሌሎች ፕሮፌሽናል አትሌቶችን የሚያረክስ ድርጊት ፈፅሜ አላውቅም።”
በቅጣቱ መሠረት ፖግባ እስከ አውሮፓውያኑ 2027 ድረስ ከሜዳ ይርቃል። ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ ሲመለስ ዕድሜው 34 ይሆናል ማለት ነው።
ቴስቴትሮን የአትሌቶችን አቅም የሚጨምር ንጥረ-ነገር ነው።
የፀረ-አበረታች መድኃኒት ተቆጣጣሪው ድርጅት ባወጣው መግለጫ ፖል ፖግባ ሰውነታችን በተፈጥሮ ከሚያመነጨው ቴስትሮን ባለፈ ተጨማሪ ንጥረ-ነገር ወስዷል ይላል።
ፖግባ ለእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ እየተጫወተ ሳለ በዓመት 7.75 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፈለው እንደነበር ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በክለቡ ለቆየባቸው እያንዳንዱ ዓመት ተጨማሪ የ3.75 ሚሊዮን ፓውንድ ጉርሻ ይሰጠው ነበር።
አልፎም ምስሉን ለመጠቀም በየዓመቱ 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኝ እንደነበር ይታወሳል።
ፖግባ ዩናይትድን ለቆ ቀድሞ ወደ ሚጫወትበት የጣሊያኑ ክለብ ጁቬንቱስ የተመለሰው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2022 ነው።
በ2018 ከፈረንሳይ ጋር የዓለም ዋንጫ ያነሳው ፖግባ ወደ ቱሪን ከተመለሰ በኋላ በጉዳት ምክንያት በርካታ ጨዋታዎች አምልጠውታል።