ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፊሊፒናውያን በጎርፍ በተጥለቀለቁ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚጋቡት ለምንድን ነው?
የጃማይካ አጊላር ሰርግ በየትኛውም የውጭ ሀገር የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚጠበቀው የተለየ ነገር አልነበረውም።
ጃማይካ፤ ነጭ ረጅም ቬሎዋን አድርጋ፣ የአባቷን ክንድ አጥብቃ ይዛ፣ በቤተ ክርስቲያኑ ሌላኛው ጫፍ ወደ ቆመው ሙሽራዋ በዝግታ ተራምዳለች።
በሰርጓ ላይ ብቸኛው የተለየ ነገር እሷም ሆነች እንግዶቿ በሙሉ እስከ ጉልበታቸው የሚደርስ ውሃ ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ብቻ ነው።
በወቅቱ በነበረው የተራዘመ የዝናብ ወቅት (ሞንሶን) እና በተከሰተው አውሎ ነፋስ ምክንያት በጣለው ከባድ ዝናብ የተነሳ ቤተክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ተጥለቅልቆ ነበር።
ይህ ግን ጥንዶቹ የሰርጋቸውን ሥነ ሥርዓት ከማካሄድ አላገዳቸውም። "ፈታኝ ነው፤ ነገር ግን አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ አተኩረናል" ይላሉ።
ከፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ በስተሰሜን በሚገኘው የባራሶኢን ቤተክርስቲያን የተቀረጸው ሰርጉን የሚያሳይ ቪዲዮ፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ለመሠራጨት ጊዜ አልወሰደበትም።
የፊሊፒናውያንን በፈተና ውስጥ በጽናት የመቆም አቅም የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ሆኖ ተቆጠረ።
በሚያስገርም ሁኔታ ግን ይህ ዓይነቱ ሁነት ሲፈጠር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከሁለት ዓመት በፊት ሌላ ፊሊፒናውያን ጥንዶች በተመሳሳይ ወቅት፣ በዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጎርፍ ውስጥ ተራምደው ሰርጋቸውን አከናውነዋል።
በአውሮፓውያኑ 2018 ደግሞ ሌሎች ጥንዶች በማኒላ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው በቡላካን ግዛት በሚገኝ በጎርፍ በተጥለቀለቀ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል።
በጎርፍ የታጀቡት ሰርጎች የሚያሳዩት ቁርጠኝነትን ብቻ አይደለም፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎችን የሚፈትነውን የጎርፍ ችግር አጉልተው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጭምር እንጂ።
በተበላሹ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቶች መብዛት፣ ደካማ የከተማ ንድፍ እንዲሁም በየጊዜው እየከበደ እና እየጨመረ የመጣው ከባድ የአየር ሁኔታ ይህ ችግር እየተባባሰ ለመምጣቱ ምክንያት ናቸው።
ሰርግ እና የጎርፍ መዘዞች
ለ27 ዓመቷ ሙሽራ ከጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ሁሉ የከበዳት ከሰርጉ አንድ ቀን በፊት የነበረው ምሽት ነው። የሰርግ ሥነ ሥርዓቱን ማካሄድ ወይም ማስቀረት መወሰን እጅግ ከባድ እንደ ነበር ትናገራለች።
የሰርጉ ዕቅድ አውጪዎች ዝናቡ የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋቸው ነበር።
"ለእኛ በጣም ወሳኝ ጊዜ ነበር። መሰረዝ እና እንደገና ለሌላ ቀን መዘጋጀት አለብን? ለእኔ 50/50 ነበር። ለመሰረዝ እያሰብኩ ነበር" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። በመጨረሻ ግን በመጀመሪያው ዕቅዳቸው ለመጽናት ወሰኑ።
የ27 ዓመቱ ሙሽራ ጄድ ሪክ ቨርዲሎ፤ "ፈታኝ ነበር፤ ነገር ግን ለግንኙነታችን እና እኛን ለሚወዱን ሰዎች በጣም አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ አተኩረናል" ብሏል። ሁለቱም በሥነ ሥርዓቱ "በጣም መደሰታቸውን" ገልጿል።
እንደ ባል እና ሚስት ካደረጓቸው የመጀመሪያ ነገሮች አንዱ በአካባቢው ወደሚገኝ የጤና ማዕከል በመሄድ ዶክሲሳይክሊን የሚባለውን መድኃኒት መውሰድ ነበር።
ይህ መድኃኒት ጉበትን እንደሚያጠቃው ሌፕቶስፒሮሲስ ያሉ በጎርፍ የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያገለግል አንቲባዮቲክ ነው።
በጎርፍ የተጥለቀለቀው የባራሶኢን ቤተክርስቲያን፤ ይህ ሰርግ ከተካሄደ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓት አስተናግዷል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲከናወን አስከሬኑን የያዘው ነጭ ሬሳ ሳጥን እንጨት ላይ ተደርጎ ፊት ለፊት ተቀምጦ ነበር።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 'ታይፉን ዊፋ' ተብሎ የሚጠራው እና ፊሊፒንስ ውስጥ ክሪሲንግ በመባል የሚታወቀው አውሎ ንፋስ የቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ፤ በዚህ ዓመት ሀገሪቱ የመታ ሦስተኛው አውሎ ንፋስ ነው።
ፊሊፒንስ ይህ ዓይነቱ የአየር ሁኔታ በሚፈጠርበት የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በመገኘቷ ምክንያት ለአውሎ ንፋስ እጅጉን ተጋላጭ ከሆኑት የዓለም ሀገራት አንዷ ነች።
በዚህ ቀጣና በየዓመቱ ወደ 20 የሚጠጉ ትሮፒካል አውሎ ነፋሶች የሚፈጠሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ በቀጥታ በሀገሪቱ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ።
ዝናብ ከጀመረበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ስድስት ሰዎች እንደተገደሉ ተዘግቧል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በዚህ ወር መጨረሻ ሁለት ተጨማሪ አውሎ ነፋሶች እንደሚፈጠሩ ወይም ወደ ፊሊፒንስ እንደሚገቡ እየተገመተ በመሆኑ ሀገሪቱ ከከባድ ዝናብ የምታርፍበት ዕድል ያለ አይመስልም።
ታሪካዊ ክስተቶች እንደሚያሳዩት፤ እጅግ ጠንካራ እና ገዳይ የሆኑ አውሎ ነፋሶች የሚከሰቱት በዓመቱ መጨረሻ ከገና በዓል በፊት ነው።
ይህ የጎርፍ መጥለቅለቅ የተከሰተው፤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርቆስ ጁኒየር በመጪው ሰኞ ለኮንግረሱ የሚያቀርቡትን ዓመታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ንግግር ከመድረሱ ከቀናት አስቀድሞ ነው።
ፕሬዝዳንቱ የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያቀርቡት ዕቅድ ብዙዎች በትኩረት የሚከታተሉት ጉዳይ ነው።
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ወቅት የፕሬዝዳንቱ ፎቶዎች በመዲናዋ የመንገድ መብራቶች ላይ ሲሰቀል የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በስፋት መሠራጨታው ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
ይህንን ተከትሎ ማርቆስ ንግግራቸውን ለማርቀቅ የሚያደርጉትን ዝግጅቱን አቋርጠዋል።
ተቺዎች የመንግሥት ሀብት ከፖለቲካ ትርኢት ይልቅ ለአደጋ ምላሽ ላይ ሊውል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የንግድ ስምምነትን ድርድር ለማድረግ ዋሽንግተን የሚገኙት ማርቆስ፤ ሀገሪቱን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት የአደጋ ምላሽ ሰጪ ኤጀንሲዎች ዝግጁ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ጎርፍ የሚያጋጥመው ለምንድን ነው?
አብዛኛው የጎርፍ መጥለቅለቅ የተከሰተው ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚኖሩባት ሜትሮ ማኒላ ከተማ ውስጥ ነው።
ይህች ከተማ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ካላቸው ትልልቅ ከተሞች አንዷ ስትሆን፤ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓቷ ለነዋሪዎች ትልቅ ፈተና ነው። ያልተሰበሰቡ እና ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተወገዱ ቆሻሻዎች የውሃ መስመሮችን ይበክላሉ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቶችንም ይደፍናሉ።
የሜትሮ ማኒላ "በጣም ያረጀ" እና "በቂ ያልሆነ" የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚያስከትል በፕሬዝዳንት ማርቆስ አስተዳደር ውስጥ የሕዝብ ሥራዎች ሚኒስትር የሆኑት ማኑዌል ቦኖአን ይናገራሉ። የከተማዋ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የተገነባው በአውሮፓውያኑ1900ዎቹ ነው።
ቦኖአን፤ ኤቢኤስ-ሲቢኤን ኒውስ ለዜና አውታር እንደተናገሩት፤ የማስወገጃ ሥርዓቱ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ጥቅም ላይ በመዋሉ 70 በመቶ ያህሉ በደለል የተዘጋ ወይም የተደፈነ ነው።
ሚኒስትሩ፤ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመቋቋም የሚያስችል ማስተር ፕላን እየተዘጋጀ መሆኑን እና ችግሩን ለመፍታት በቢሊዮን የሚቆጠር የሀገሪቱ ገንዘብ መመደቡን ተናግረዋል።
በመንግሥት የተቀመጠው አንዱ አፋጣኝ መፍትሄ፤ በዋና ከተማዋ የሚገኙ 32 የውሃ ፓምፕ ጣቢያዎችን በመጠገን የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ እንደሆነ ገልጸዋል።
"በተቻለ ፍጥነት መፍትሄ ለመፈለግ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መዘጋጀት አለብን" ብለዋል።
የጎርፍ ጉዳይ አንድ ቀን ሊፈታ የሚችል ችግር እንደሆነ የሚያስቡት አዲስ ተጋቢዎቹ ጥንዶች፤ ከእንግዲህ ሌሎች ተጋቢዎች በሰርጋቸው ቀን በቤተ ክርስቲያን አዳራሽ በውሃ ውስጥ ማሳለፍ አይኖርባቸውም የሚል ተስፋም አላቸው።
የ27 ዓመቱ ሙሽራ ጄድ፤ "ፊሊፒንስ ውስጥ ባሕር እና ወንዞች ስላሉ ብዙ ውሃ አለን ማለት ነው። መንግሥት በጎርፍ ማስተንፈሻ፣ በፓምፕ ጣቢያዎች እና ሰፋፊ ቦዮች ላይ በጀቱን ማፍሰስ አለበት" ይላል።
"በአንድ ቀን ውስጥ ማሻሻያዎች ሊከናወኑ አይችሉም። ነገር ግን በዓመታት ውስጥ ሊሠሩ ይችላሉ፤... ሁላችንም የሚደርስብንን ተፅዕኖ መገደብ ላይ እስካተኮርን ድረስ [መፍትሄ እንደሚመጣ] ተስፋ አለኝ" ሲል ተናግሯል።