ፓኪስታን ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ልትመርጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፓኪስታን የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ለመምረጥ ማቀዷን አስታወቀች።
ኢዝላማባድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ልትመርጣቸው መሆኑን ያስታወቀችው፤ ፕሬዚደንቱ ባለፈው ወር በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የተጫወቱትን ሚና በመጥቀስ ነው።
የፓኪስታን መንግሥት በኤክስ ገፁ ላይ ባጋራው መረጃ ትራምፕ ሽልማቱ ይገባቸዋል ብሏል።
የፓኪስታን መንግሥት "በቅርቡ በሕንድ እና ፓኪስታን ቀውስ ውስጥ ላሳዩት ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነት እና ወሳኝ አመራር እውቅና ለመስጠት" ሽልማቱ ይገባቸዋል ብሏል።
ሕንድ ባለፈው ወር ከፓኪስታን ጋር የገባችውን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካ እንደ አሸማጋይ ሆና ስትቀርብ፤ ከሦስተኛ ወገን ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነት እንደማትፈልግ በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች።
ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል።
የዚህ ዓመት የሰላም ኖቤል አሸናፊ የሚታወቀው በጥቅምት ወር ነው።
ትራምፕ በግንቦት ወር የኒውክሌር መሣርያ በታጠቁት ጎረቤት አገራት ሕንድ እና ፓኪስታን መካከል ለአራት ቀናት የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ በድንገት የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን አስታወቀዋል።
የፓኪስታን መንግሥት ቅዳሜ ማለዳ ላይ ባጋራው ልጥፍ ላይ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢዝላማባድ እና ከኒው ዴሊሂ ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማድረግ፣ ታላቅ ስልታዊ አርቆ አስተዋይነት እና የመሪነት መንፈስ አሳይተዋል፤ ይህም በፍጥነት እየተባባሰ ያለው ሁኔታ እንዲሻሻል አድርጓል።
"ይህ ጣልቃ ገብነት እውነተኛ ሰላም ፈጣሪነት ላይ ያላቸውን ሚና ማሳያ ነው" ብሏል።
በጉዳዩ ላይ ከዋሽንግተንም ሆነ ከኒው ዴህሊ የተሰማ ምላሽ የለም።
ትራምፕ፤ ሕንድ እና ፓኪስታን ግጭቱን ያቆሙት በአሜሪካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በመድረሳቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።
ፓኪስታን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሃሳብ የሰጠች ሲሆን ሕንድ ግን አስተባብላለች።
ባለፈው ወር ትራምፕ ሕንድ እና ፓኪስታን ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ለማስቀጠል የተኩስ አቁም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
" ከእናንተ ጋር ብዙ ንግዶችን ማካሄድ እንፈልጋለን አልኩ (ሕንድ እና ፓኪስታንን)። [ግጭቱን] እናስቁመው" ማለታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የኖቤል ሽልማቱ ሃሳብ በፓኪስታን ፓርላማ የሴኔት መከላከያ ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩት ሙሻሂድ ሁሴን አድንቆትን አግኝቷል።
"ትራምፕ ለፓኪስታን መልካም ናቸው" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል። "ይህ ለትራምፕ ኢጎ የሚመች ከሆነ ይሁን። ሁሉም የአውሮፓ መሪዎች አለቅጥ እግሩ ስር ሲርመሰመሱ ነበር" ብለዋል።
ነገር ግን በአሜሪካ የፓኪስታን የቀድሞ አምባሳደር ማሌሃ ሎዲ እቅዱን "አሳዛኝ" ሲሉ ተችተዋል።
"እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን የዘር ማጥፋት ጦርነት የደገፈ እና እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት 'ምርጥ' ብሎ የተናገረ ሰው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።
አክለውም "ብሄራዊ ክብራችንን ይነካል" ብለዋል።
አርብ እለት ትራምፕ በብዙ ሀገራት መካከል የሰላም ድርድር ማካሄዳቸውን በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
አክለውም "በጭራሽ፣ ምንም ብሰራ የኖቤል የሰላም ሽልማት አላገኝም" ብለዋል በቁጭት።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን እንደመጡ የሩስያ እና ዩክሬን እንዲሁም የእስራኤል እና ጋዛ ጦርነቶችን በፍጥነት ለማስቆም ቃል ገብተው ነበር።
ባራክ ኦባማን እአአ በ2009 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በሆኑ ከስምንት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው በተደጋጋሚ ይተቿቸዋል።
በ2013 ትራምፕ የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሽልማቱን እንዲሰርዝ ጠይቀዋል።















