በዓይን ሳይታዩ የሚያክሙት ጥቃቅኖቹ ናኖ ሮቦቶች

ናኖሮቦት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ናኖሮቦት

ናኖሮቦትስ ወይም ናኖቦትስ (Nanobots) ይባላሉ።

የሮቦት ዓይነቶች ናቸው። ሮቦት ሲባል እንደምናስበው ግዙፍ አይደሉም።

እጅግ በጣም ጥቃቅን ሆነው ነው ናኖቦቶች የሚሠሩት።

በተለይም በሕክምናው ዘርፍ ያላቸው የላቀ ሚና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሽታ ላይ ብቻ አነጣጥረው መድኃኒት በመስጠት ይታወቃሉ።

ጥቃቅን የሆኑ የሰውነት ክፍሎችን አቆራርጠው በደም ሕዋስ ውስጥ በመጓዝ ቀዶ ሕክምና ያደርጋሉ።

ናኖቦቶች የሕክምናውን ዘርፍ እንዴት ይለውጡታል? ምንስ ጠቀሜታ አላቸው? በሚለው ዙርያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በሮቦቲክስ ፒኤችዲውን እየሠራ ያለውና ‘ጉዞ ቴክኖሎጂስ’ የተባለ ተቋም የመሠረተው ዳንኤል ጌታቸውን አነጋግረናል።

ናኖሮቦትስ የሚለውን ስያሜ ከማስረዳት ይጀምራል።

ናኖ- መለኪያ ነው። አንድ ቢሊዮንኛ በሚል መለኪያው ይገለጻል።

ሮቦት- ዕይታ፣ ድምጽ እና እንቅስቃሴን ተገንዝቦ ድርጊት የሚፈጽም ማሽን ነው።

‘ሮቦት’ ሲባል ብዙውን ጊዜ በሰዎች ሰውነት ልክ የተሠራ ተደርጎ እንደሚታሰብ ዳንኤል ይናገራል።

ከዚህ በተቃራኒው ግን በጣም ትንንሽ፣ በዓይን የማይታዩ ናኖቦቶችን መፍጠር ተችሏል።

“ከሰው ልጅ ሕዋስ ጋር በሚስተካከል መልኩ የተሠሩ ናቸው” ይላቸዋል።

ዳንኤል እንደሚለው፣ ሮቦት ቀጣዮቹን መሠረታዊ ነገሮች መያዝ አለበት።

የመጀመሪያው አካባቢውን ‘ሴንስ’ ማድረግ ወይም መገንዘብ መቻል አለበት።

ከዚያም በዚያ አካባቢ ላይ አንድን ድርጊት መፈጸም መቻል ወይም ውሳኔ ማስተላለፍ መቻል አለበት።

ናኖሮቦቶች በደም ስር ውስጥ የሚያሳይ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ናኖሮቦቶች በደም ስሮች ውስጥ ጭምር በመግባት አስፈላጊውን የሕክምና አገለግሎት ይሰጣሉ

ናኖቦት ሰውነት ውስጥ በሽታ ለመግደል ሲታዘዝ፣ በሽታው ያለበትን ቦታ ብቻ ለይቶ የመግደል እርምጃን ይወስዳል።

በዚህ አገላለጽ ድርጊት እንደሚፈጸምበት ‘አካባቢ’ የሰው ልጅ ነው ማለት ነው።

“ናኖቦት በተማረው ‘ዳታ’ ላይ ተመርኩዞ ድርጊት ይፈጽማል። የራሱ ሞተሮች ሊኖሩት ይችላሉ። ሊንቀሳቀስ ይችላል። መጠኑም በጣም ያነሰ ነው” ሲል ይገልጸዋል።

ናኖቴክኖሎጂ በወደፊቱ ዓለም በጉጉት ከሚጠበቁ ቴክኖሎጂዎች አንዱ ነው።

“ሰዎችን በትልቁ ማገዝ የሚችል ቴክኖሎጂ ነው” ሲል ባለሙያው ይገልጸዋል።

ናኖቦቶች መድኃኒት ከመዋጥ በተሻለ የሚሰጡትን ጥቅም ይጠቅሳል።

በሕክምና የሚሰጡ መድኃኒቶች ወይም መርፌዎች ለጎንዮሽ ጉዳት የሚያጋልጥ ንጥረ ነገር ሊኖራቸው ይችላል።

ናኖቦት ግን ሰውነት ውስጥ ገብቶ በሽታውን ለይቶ ማጥቃት የሚችል ነው።

ናኖቦቶች የጎንዮሽ ጉዳትን ከመቀነስ ባሻገር በፍጥነት ከህመም ለማገገም ይመረጣሉ።

“መድኃኒት ሳያስፈልግ ናኖቦቶች በሽታ አለበት የተባለ ቦታ በአድራሻው ሄደው ይገድላሉ” ሲል ዳንኤል ይገልጻል።

ለተለያየ ሰው እንዲሆኑ በተለያየ መንገድ የሠለጠኑ ናኖቦቶች ሰውነት ውስጥ ገብተው በሽታውን ሊገድሉ ይችላሉ።

ናኖሮቦቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንዳንዴም በጣም ውስብስብ እና አስቸጋሪ የሚባል የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎችን ይረዳሉ።

ለዚህም በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እና የጭንቅላት ዕጢ በሽታዎችን መጥቀስ ይቻላል።

“ናኖቦቶች ትንሽ ስለሆኑ በጣም ጠባብ የሚባል የሰውነት ክፍል ላይ ገብተው ቀዶ ሕክምና ሳያስፈልግ ጉዳቱን ማስወገድ ይችላሉ” ይላል ባለሙያው።

በሽታውን ከገደሉ በኋላ ከሰውነት ውጪ ስለሚደረጉም እንደ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት አያስከትሉም።

በዘርፉ የተሠሩ ጥናት እና ምርምሮች እንደሚጠቁሙት፣ ናኖቦቶች የደም ሕዋስ ውስጥ ገብተው የህመም ተጋላጭነትን ያሳውቃሉ።

በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠንን ለማወቅ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በካንሰር ሕክምና እንዲሁም ከዘረ መል ጋር በተያያዘ ሕክምና (Gene Therapy) ላይ ያላቸው ሚና እየጎላ መጥቷል።

ናኖቦቶች በስኳር፣ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ በልብ ህመም እና በሌሎችም ዘርፎች ምርምር እየተደረገባቸው ነው።

ከዘረ መል ጋር ከተያያዘ ሕክምና ረገድ፣ በቤተሰብ የጤና ታሪክ ሳቢያ የሚመጣ የህመም ተጋላጭነትን ከማወቅ አንስቶ እስከ ማከም ድረስ ናኖቦቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው።

የመርሳት እክል ወይም አልዛይመር ተጋላጭነትን ለመቀነስ በዘርፉ ምርምር እየተደረገ ይገኛል።

ከዚህ ባሻገር ከባቢ አየርን ወይም ውሃን የሚበክሉ ንጥረ ነገሮችን ለመለየት እና ለማከም እንዲውሉም ሙከራዎች እየተደረጉ ነው።

ሌላው በሰው ልጆች ሰውነት ላይ ለውጦችን ማድረግ ነው።

ዳንኤል “ራሳችንን ‘ኤዲት’ የምናደርግበት” ሲል ይገልጸዋል።

“ስልካችን ላይ ደስ ያለንን ፎቶ ዋልፔፐር እንደምናደርገው የዓይናችን ቀለም ካልወደድነው ቀለሙን ልንቀይረው እንችላለን” በማለት ምሳሌ ይሰጣል።

ናኖሮቦቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተንቀሳቃሽ ስልክ የቤት መብራት ማጥፋት እንደምንችለው፣ ወደፊት የሰው ልጅ የፀጉር ቀለሙን፣ ቁመቱን ወይም ቆዳውን በመለወጥ ራሱን ‘ከስተማይዝ’ [በሚፈልገው ዓይነት መቀየር] ይችል ይሆናል።

“ብዙ ሰው ይህንን ለማመን ሊቸገር ይችላል። ግን ናኖቴክኖሎጂ ባደገ ቁጥር ትልቁ የምናገኘው ጥቅም ሰዎች ሰውነታቸውን መቆጣጠር መቻላቸው ነው” ይላል ዳንኤል።

የሰው ልጅ በዘረ መል ተጋላጭነት የሚመጣ ህመምን ማጥፋት ጨምሮ በሌሎችም መንገዶች ጤናውን የሚጠብቅበት መንገድ ካለው እና ራሱን በሚፈልገው መንገድ መለዋወጥ ከቻለ “የሰው ልጅ የመጨረሻ በራሱ ላይ ሊያደርግ የፈልገውን አሳካ ይባላል” ሲል ያስረዳል።

ይህ አሉታዊ ጎንም አለው። የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ አሁን ያለው የፆታ ወይም የዘር መድልዎ አልያም በምጣኔ ሃብት ልዩነት የሚመጣ እኩልነት ማጣት በቀጣዩ ዘመን በቴክኖሎጂ ሊባባስ ይችላል።

ይህ ማለት አንዳንዶች ሰውነታቸውን እንዳሻቸው የሚለዋውጡበት ወይም የሚጠብቁበት ቴክኖሎጂ ቢኖርም ለሁሉም ተደራሽ ስለማይሆን በሰው ልጆች መካከል ያለውን ልዩነት ያሰፋዋል።

“ቴክኖሎጂው ቁጥጥር ይደረግበት እና የገቢ ምንጭ ይሁን ብለው ተቋማት ክፍያ ሲጠይቁ፣ ያንን መክፈል የማይችል ሰው መታከም የማይችል ከሆነ አደገኛ ይሆናል” ይላል ዳንኤል።

ዳንኤል እንደሚለው፣ በናኖ መለኪያ ስኬል ሮቦቶች እየተራቀቁ ሲሄዱ ሮቦቶቹን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል ይቀንሳል።

ናኖቦቶች የሰው ልጅ በሚያመነጨው ሙቀት ብቻ በቂ ኃይል አግኝተው ሊሠሩ ይችላሉ የሚሉ ጥናቶች እየተሠሩ ነው።

መጠናቸው አንሶና በተወሰነ ኃይል አቅርቦት የሚሠሩ ሆነው፣ በሰው ልጆች ላይ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችሉበት መንገድ ተፈጠረ ማለት “የሰውን ልጅን ክፍተት አገኘን ማለት ነው” በማለት ያስረዳል።

ይህ ክፍተት የሰው ልጆች ‘ኤዲት’ የሚደረጉበት ነው። በሰው ሰውነት ላይ ምን ሊጨመርበት ወይም ምን ሊቀነስበት እንደሚችል ማሰብ ይጀመራል።

ሰዎችን እንደ መሣሪያ መጠቀም የሚለው አስፈሪ ሐሳብ ሳይንሳዊ ልብወለድ መሆኑ ሊቀር የሚችልበትም ዕድል አይጠፋም።

ዳንኤል እንደሚለው፣ ቴክኖሎጂው ምን ያህል አቅም አለው? ምን ያህል ርቀትስ መሄድ ይቻላል? የሚለው ሲታይ ለመሣሪያነት ጥቅም ላይ የመዋል ስጋት ተያይዞ ይመጣል።

“ማን ምን ጥናት እያደረገ ነው? የሚለውን ማየት ነው” ይላል ባለሙያው።

ናኖቴክኖሎጂ በግንባታ፣ በወታደራዊ ሳይንስ እና በሌሎችም ዘርፎች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ቴክኖሎጂው ምን ይዞ ይመጣል? የሚለውን ቀድሞ ማሰብ እንደሚያሻ ግን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

“በአፍሪካ ዐውድ ስናስበው፣ ለወደፊት የሚመጣው ቅኝ ግዛት አካላዊ ወይም መሬትን የመውሰድ ሳይሆን ቀልብን የመውሰድ ነው” ሲል ዳንኤል ይገልጸዋል።

ወደፊት የሚመጣውን ስጋት “ታንክ እና ወታደር ተይዞ የሚጠበቅ አይደለም” የሚለው ባለሙያው፣ ዳንኤል ጌታቸው፤ የሚያጠፋ ቴክኖሎጂን መከላከል የሚችል ማኅበረሰብ መገንባት የግድ እንደሆነ ይመክራል።