የሕንድ አየር መንገድ በሠራተኛ እጥረት ምክንያት ከ300 በላይ በረራዎችን ሰረዘ

በበረራ መሰረዝ ምክንያት ጉዟቸው የተስተጓጎለ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Anushree Fadnavis/Reuters

የሕንድ ትልቁ አየር መንገድ ኢንዲጎ ከማክሰኞ ጀምሮ በገጠመው ቀውስ ከ300 በላይ በረራዎች በመሰረዙ በአገር አቀፍ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ለእንግልት ተዳርገዋል።

በሕንድ ከፍተኛ በረራን የሚያስተናግዱት በደልሂ፣ ሙምባይ፣ ሃይደራባድ እና ቤንጋሉሩ የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ናቸው።

አየር መንገዱ ለተፈጠረው መስተጓጎል የቴክኒክ ብልሽቶችን፣ የአየር ሁኔታን እና አዲስ የወጣው የሠራተኞች መመሪያዎችን በምክንያትነት ጠቅሷል።

ከአገሪቱ የአየር መንገዶች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የአገር ውስጥ ገበያ ድርሻ የያዘው ይህ አየር መንገድ ዋና ዋና ሜትሮዎችን እና ትናንሽ ከተሞችን ያገናኛል።

ኢንዲጎ የተፈጠረውን የበረራ መስተጓጎል ለማረጋጋት እስከ አርብ ድረስ ባለው መርሃ ግብሩ ላይ "ጥንቃቄ የተሞላበት ማስተካከያዎችን" ማድረጉን አስታውቋል።

ሐሙስ ማለዳ ኤኤንአይ የዜና ኤጀንሲ በዴልሂ ብቻ 33፣ በሙምባይ 85 እና 73 በቤንጋሉሩ የኢንዲጎ በረራዎች መሰረዛቸውንን ዘግቧል።

በበረራ መስተጓጎሎች የተበሳጩ መንገደኞችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተሰራጭተዋል።

በርካታ መንገዳቸውን ቅሬታቸውን ለመግለጽ ወደ ኤክስ ገጻቸው በመሄድ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

በኤክስ ገጽ ላይ የቀረቡት አብዛኛዎቹ ቅሬታዎች የአየር መንገዱን የተለመደ ምላሽ አሰጣጥ የሚነቅፉ ናቸው።

ይህም "ሥራዎቻችን በብዙ ነገሮች ላይ የተመሰረቱ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ከአቅማችን በላይ የሆኑ እና በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ" የሚል ነው።

የሕንድ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ለበረራ መስተጓጎል ምክንያት የሆነውን ጉዳይ በማጣራት ላይ ሲሆን አየር መንገዱ በረራዎች የተቋረጡበትን እና የዘገዩበትን ምክንያት እንዲያብራራም ጠይቋል።

እአአ ከኅዳር 1 ጀምሮ ኢንዲጎ አብራሪዎች የሚበሩበትን ሰዓት በሚገድበው እና ረዥም ሰዓት እረፍት እንዲያደርጉ የሚያዘው አዲስ መመርያ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ የአብራሪዎች እና የበረራ አስተናጋጆች እጥረት አጋጥሞታል ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሆኖም የሕንድ አብራሪዎች ፌዴሬሽን የበረራዎቹ መሰረዝ ከአዲሱ ሕግ ጋር "መያያዝ የለባቸውም" በማለት ሌሎች አየር መንገዶች በዚህ ምክንያት አለመጎዳታቸውን አስታውቋል።

ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጥ ኢንዲጎን ቢያነጋግርም ወድያውኑ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ይህ ቀውስ ላለፉት ሁለት አስር ዓመታት አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው አየር መንገድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ወራት ወዲህ አየር መንገዱ ያለው ስም እና ዝና እክል እየገጠመው እና የአገልግሎት ጥራቱም እየቀነሰ መጥቷል።

በቅርቡ ሎካልሰርክልስ የተሰኘው ቡድን ባደረገው ጥናት መሠረት 54 በመቶ የአየር መንገዱ ተጠቃሚዎች ባለፈው ዓመት ከበረራ መዘግየት ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።