ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ 9 ምዕመኖቿ በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንደተገደሉ አስታወቀች
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በጋምቤላ ክልል መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ላይ ከደቡብ ሱዳን ዘልቀው በገቡ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ዘጠኝ ምዕመኖቿ እንደተገደሉ አስታወቀች።
ጥቃቱ የተፈጸመው ግንቦት 12/ 2015 ዓ.ም አመሻሽ አስራ አንድ ሰዓት ላይ ሲሆን፣ ከሟቾች ውስጥ የስድስት ዓመት ህጻን እና አንዲት የምታጠባ እናት እንደሚገኙበትም ቤተ ክርስቲያኗ ትናንት ግንቦት 21/ 2015 ዓ.ም ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።
ይህ ጥቃት የደረሰው በምዕራብ ጋምቤላ ቤቴል ሲኖዶስ አገልግሎት ክልል ውስጥ በሚገኘው ማታራ በሚባል ቀበሌ ነው።
ጥቃቱን ያደረሱት ከደቡብ ሱዳን ዘልቀው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች መሆናቸውን የገለጸችው ቤተ ክርስቲያኗ፣ ከሞቱት በተጨማሪ በርካቶች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሲኖዶሱ የሴቶች አገልግሎት ተዘጋጀ በተባለው ጉባኤ ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ ሴቶች፣ እናቶች እና ልጆቻቸው ተሳታፊ ነበሩ።
ተሳታፊዎቹ የቀኑን መርሃ ግብር አጠናቀው ለእራት በተቀመጡበት ወቅት ጊዜ ጥቃቱ መፈጸሙን ከቤተ ክርስቲያኗ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ታጣቂዎቹ ህጻናቱን በኃይል አፍነው ሊወስዱ ሲሞክሩ እናቶች በመከላከላቸው ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተዋል ብላለች ቤተ ክርስቲያኗ ባወጣችው መግለጫ።
ከሞቱት ውስጥ የስድስት ዓመት ህጻን የሆነችው ንያካካ ዊዩአል ኒኜት እና አንዲት የምታጠባ እናትም እንደሚገኙበትም መግለጫው ጠቅሷል።
በዚህ ጥቃት የቆሰሉ በርካታ እናቶች በጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህክምና እየተረዱ ናቸው ተብሏል።
ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ በአሳሳቢ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙ መረጃዎችን ዋቢ እድርጎ መግለጫው ጠቅሷል።
የምዕራብ ጋምቤላ ቤቴል ሲኖዶስ መሪዎች ጥቃቱ በተፈጸመበት ቀበሌ ተገኝተው ድጋፍ ቢያደርጉም ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ተጨማሪ አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።
ጥቃቱ የደረሰበት ይህ አካባቢ የልጆች አፈና እና የከብት ዝርፊያ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት የጠቆመው መግለጫው፣ በመንግሥት እና በሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት እየተደረገ ያለው ክትትልና ትኩረት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን አቅርባለች።
በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ተሻግረው በሚመጡ የጎሳ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተደጋጋሚ ሲሆን፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሰዎች ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በተጨማሪ ህጻንትን እና ከብቶች ይዘው ይወስዳሉ።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።