ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሶማሊያ ውስጥ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ
አስራ አንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሶማሊያ ውስጥ ቦሳሶ አቅራቢያ በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።
የድርጅቱ የሶማሊያ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ይህ መኪና አደጋ የደረሰው ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ ሲሆን፣ ከሟቾቹ በተጨማሪ ቢያንስ 20 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል።
ስደተኞቹ ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በመነሳት በአደገኛ የባሕር መስመር ወደ የመን ለመሻገር በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካካይነት ወደ ቦሳቦ እየተጓዙ ነበር ተብሏል።
ስደተኞቹን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ በጉዞ ላይ ሳለ ተገልብጦ ነው አሰቃቂው የሞትና የመቁሰል አደጋው የደረሰው።
አደጋው በደረሰበት ስፍራ ያሉ ነዋሪዎች የ11 ሰዎችን አስከሬኖች እና በከባድ ሁኔታ የቆሰሉትን ስደተኞች ከአቅሙ በላይ ህሙማንን እያስተናገደ ወዳለው የቦሳሶ አጠቃላይ ሆስፒታል መውሰዳቸውን ተ የፍልሰተኞቹ ድርጅት ገልጿል።
በሶማሊያ የሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልሰተኞች ድርጅት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ስደተኞች ለመርዳት የህክምና አቅርቦቶችን ወደ ቦሳሱ መላኩን እና የሥነ ልቦና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የድርጅቱ የሶማሊያ ተልዕኮ ኃላፊ ፍራንዝ ሴለስታይን ገልጸዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ በሚወስደው “በምሥራዋዊው መስመር” በኩል የአሁኑን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የሞቱ እና የደረሱበት ያልታወቀ ከ1,100 በላይ ሰዎችን መመዝገቡ ተገልጿል።
ነገር ግን መሞታቸው ተረጋግጦ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከተከሰተው በታች መሆኑን አይኦኤም አመልክቷል። ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት ከ2015 (እአአ) ጀምሮ ከአገራቸው ወጥተው የደረሱበት አለመታወቁ በቤተሰባቸው ሪፖርት የተደረጉ ሰዎች ቁጥር ከ50,000 በላይ መሆኑን አመልክቷል።
መሥራቃዊ መስመር የሚባለው መንገድ ወደ ጂቡቲ ወይም አሁን አሰቃቂ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ይጓዙበት የነበረው የሶማሊያ መስመርን በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ባሕር አቋርጠው ወደ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት የሚጓዙበት መስመር ነው።
በአደገኛው የባሕር መስመር ለስደት በሚያቀኑት ሰዎች ላይ በባሕር እና በየብስ ጉዞ ከሚደርሰው አደጋ በተጨማሪ በአዘዋዋሪዎች አማካይነት የተለያየ አይነት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃዎች ግድያዎች ጭምር እንደሚፈጸምባቸው የአይኦኤም ሪፖርት ያመለክታል።
ነገር ግን ይህ ሁሉ አደጋ እና ሰቆቃ እየደረሰባቸው በዚህ መስመር ለስደት የሚወጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ባለፉት ጥር እና የካቲት ወራት ብቻ 21,469 ፍልሰተኞች የመን የገቡ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከገቡት 14,298 በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ገልጿል።
በተለይ ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ ተነስተው በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት በጂቡቲ ወይም በሶማሊያ በኩል በባሕር ለማቋረጥ የሞከሩ በመቶወች የሚቆጠሩ ሰዎች ባለፉት ዓመታት ባሕር ላይ በሚገጥማቸው አደጋ ለህልፈት መዳረጋቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ እንደቆየ ይታወቃል።