ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ሁለት ሕጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የተጠረጠረችው እጇን ለፖሊስ ሰጠች
በአዲስ አበባ ከተማ አንዲት የቤት ሠራተኛ ሁለት ህጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለች በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሏን ፖሊስ አስታወቀ።
በሕጻናቱ ላይ የተፈጸመው ይህ የግድያ ወንጀል ያጋጠመው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አራብሳ ኮንዶሚንየም ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤት መንደር መሆኑን ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለመግለጽ እጅግ አሰቃቂ ነው ያሉት የግድያ ወንጀል ድርጊት የተፈጸመባቸው ሁለቱ ህጻናት የሁለት እና የሦስት ዓመት እድሜ ያላቸው ህጻናት ናቸው።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “እጅግ በጣም አሳዛኝ እና ዘግናኝ” በተባለው በዚህ ወንጀል የተጠረጠረችው የቤት ሠራተኛ የ19 ዓመት ወጣት መሆኗን ገልጸዋል።
በሁለት ህጻናት ላይ ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ተጠርጣሪዋ የቤት ሠራተኛ በቁጥጥር ስር የዋለችው ወንጀሉን መፈጸሟን በማመን ለፖሊስ እጇን ከሰጠች በኋላ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮማንደር ማርቆስ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ከረፋዱ ከ3፡30 እስከ 4 ሰዓት መሆኑን ገልጸው፤ ተጠርጣሪዋ ህጻናቱን አንቃ እና ስለት ተጠቅማ በአስቃቂ ሁኔታ መግድሏ የሚያመላክቱ መላምቶች አሉ ብለዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ከወንጀሉ በኋላ ለፖሊስ እጇን የሰጠችው ተጠርጣሪዋ ድርጊቱን ለመፈጸም ምክንያቷ ምን እንደሆነ እንዲሁም የአእምሮ ጤንነት ሁኔታዋን ለማወቅ ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ፖሊስ እያሰባሰበ ያለው መረጃ እንደሚጠቁመው ግን ተጠርጣሪዋ አሰሪዋ ከሆኑት ከህጻናቱ ወላጆች ጋር የተፈጠረ ጸብ ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር አመላክቷል።
በወንጀሉ የተጠርጠረችው ግለሰብ በቤት ሠራተኛነት ግድያው ለተፈጸመበት ቤተሰብ ስታገለግል መቆየቷን ኮማንደር ማርቆስ አመልክተው፤ የቤት ሠራተኛዋ ወንጀሉን የፈጸመችው ወላጆች የሌሉበትን ሰዓት ጠብቃ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
“ምንም በማያውቁ ጉዳይ በህጻናቱ ላይ የተፈጸመው ይህ አሰቃቂ ወንጀል ሁሉንም በእጅጉ አሳዝኗል” ያሉት ኮማንደር ማርቆስ፤ ወላጆች የሚቀጥሯቸው የቤት ሠራተኞችን ማንነት ጠንቅቀው ማወቅ ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል።
“እንደ ቤተሰብ ሆነው የሚኖሩ የቤት ሠራተኞች እንዳሉ ሁሉ እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ወንጀል የሚፈጽሙም ስላሉ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት” ሲሉ መልዕክታቸውን አስታላልፈዋል።
በአንድ ቀን በአሰቃቂ ሁኔታ ሁለት ታዳጊ ልጆቻቸውን ያጡት ወላጆች በከባድ ሐዘን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም በእጅጉ መረበሻቸውን ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።
ፖሊስ በወንጀሉ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ቢቢሲ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘው መረጃ አመልክቷል።