ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዝ ተዋጊ ጄቶች የኢራንን ድሮን ለማክሸፍ ሚሳዔል ሊገጠምላቸው ነው
በመካከለኛው ምሥራቅ የተሰማሩ የእንግሊዝ ተዋጊ ጄቶች የኢራን ድሮኖችን ማምከን የሚችሉበት አዲስ ሚሳዔል ሊገጠምላቸው ነው።
የሚገጠምላቸው ሚሳዔል በአነስተኛ ገንዘብ የኢራንን ድሮኖች ለማክሸፍ እንደሚውል ተገልጿል።
የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር "ዒላማዎችን ለመምታት አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው ሚሳዔል የሚረክስ ዘመናዊ መሣሪያ ነው" ሲል ገልጾታል።
ይህ ፀረ ድሮን ሚሳዔል አድቫንስድ ፕሪሲሸን ኪል ዌፐን ሲስተም (Advanced Precision Kill Weapon System) ይባላል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት የኢራን ሻሒድ ድሮኖችን መቋቋም ተቸግረዋል። እነዚህ የኢራን ድሮኖች በርካሽ ዋጋ የሚገነቡ ቢሆንም የላቀ ጉዳት እያደረሱ ነው።
ከሁለት ዓመታት በፊት በኢራን እና እስራኤል መካከል በተነሳው ግጭት ዩናይትድ ኪንግደም ሚሳዔል በመጠቀም ድሮኖችን መትታ መጣሏ ተገልጿል። እያንዳንዱ ሚሳዔል 200,000 ፓውንድ እንዳወጣም ተዘግቧል።
ሌሎች አገራት የሚጠቀሟቸው ሚሳዔሎች 22,377 ፓውንድ እንደሚያወጡ የመከላከያ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
እንግሊዝም ይሄንን ሚሳዔል ለመጠቀም መወሰኗ ይፋ ተደርጓል።
የኢራን ሻሒድ ድሮን ከ20,000 እስከ 50,000 ዶላር ያወጣል። እንግሊዝ የኢራንን ድሮን ለማምከን ልትጥቀምበት ያሰበችውን ሚሳዔል አሁን ላይ የአሜሪካ መከላከያ እየተገለገለበት ይገኛል።
የኢራን ድሮን ዝቅ ብሎ መብረር የሚችል ስለሆነ በቀላሉ ከዕይታ ይሰወራል።
ከተዋጊ ጄቶች ላይ በተተኮሱ ሚሳዔሎች አማካኝነት ድሮኖቹን መምታት ተችሏል።
ሳይፕረስ ውስጥ በሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም ወታደራዊ ሰፈር ላይ ባለፈው ወር የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል። ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ ሁለት ድሮኖችን ማምከን ተችሏል።
የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ኢራን በምትደግፈው ሄዝቦላህ እንደሆነ ይታመናል።
እንግሊዝ የምትጠቀምበት መሣሪያ በጨረር የሚመራ ሮኬት በመሸከም በአነስተኛ ወጪ ድሮኖችን መምታት የሚችል መሆኑ ተገልጿል።
ቢኤኢ ሲስተምስ እና ኪንቲኪ የተባሉ መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች "በወራት ውስጥ" ግንባታውን እንደሚያጠናቅቁም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ይፋ አድርጓል።
ኳታርም 10,000 ፀረ ድሮን ሚሳዔሎችን ከአሜሪካ ለመግዛት አቅዳለች።
የኢራን ጦርነት ከተነሳ አንስቶ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ሚሳዔል እና ድሮኖችን ተኩሳለች።
እስራኤል፣ ባሕሬን፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ዮርዳኖስ የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 2,000 ድሮኖች፣ 438 ባለስቲክ ሚሳዔሎች እና 19 ክሩዝ ሚሳዔሎችን ማክሸፏን አስታውቃለች።