ካሊፎርኒያ ለስደተኞች የተሰጡ 17,000 የንግድ ተሽከርካሪ መንጃ ፈቃዶችን አገደች

የካሊፎርኒያ ግዛት በሕጋዊ መንገድ አሜሪካ ውስጥ ለመኖር ላልተፈቀደላቸው ስደተኞች ተሰጥተዋል ያላቸውን 17,000 መንጃ ፈቃዶች ሰረዘ።

የትራንስፖርት ቢሮ የካሊፎርኒያ ባለሥልጣናት እነዚህ መንጃ ፈቃዶች "በሕገ-ወጥ መንገድ" እንዲሁም "አደገኛ ለሆኑ ስደተኛ አሽከርካሪዎች" እንደሰጡ አረጋግጠዋል ብሏል።

እንዲሁም የመንጃ ፈቃዱ ባለቤቶች ፈቃዳቸው በ60 ቀናት ውስጥ የአገልግሎት ጊዜው እንደሚያበቃ ተናግረዋል።

በነሐሴ ወር አሜሪካ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የመቆየት ፈቃድ ያልነበረው አንድ የጭነት መኪና አሽከርካሪ በፍሎሪዳ ሦስት ሰዎችን ገጭቶ በመግደሉ፣ የትራምፕ አስተዳደር ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች ከንግድ ጭነት ማጓጓዣ እና አውቶቡስ መንዳት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እንዲጨምር ግፊት አድርጓል።

የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም የአስተዳደሩን መግለጫ ፖለቲካዊ ሲሉ አጣጥለውታል።

የትራምፕ አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ በአገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩ ስደተኞች ፈቃድ የሰጡ የካሊፎርኒያ እና ሌሎች ግዛቶችን ሲተች ቆይቷል።

"ይህ የግዙፉ ችግር ጫፍ ብቻ ነው" ሲሉ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሼን ዱፊ ተናግረዋል።

"ቡድኔ ካሊፎርኒያ እያንዳንዱን ሕገወጥ ስደተኛ ከከፊል የጭነት መኪናዎች እና ከትምህርት ቤት አውቶቡሶች መሪ ላይ ማንሳቱን እንዲያረጋግጥ ግፊት ማድረጉን ይቀጥላል።"

የኒውሶም ጽሕፈት ቤት ፈቃዳቸው እየተሰረዘባቸው ያሉት አሽከርካሪዎች ከፌደራል መንግሥት ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ እንደነበራቸው ተናግሯል።

የመንጃ ፈቃዶቹ ትክክለኛ የማብቂያ ጊዜ የሌላቸው እና የካሊፎርኒያ ሕግን የጣሱ መሆናቸውን የዘገቡት መገናኛ ብዙኃን፣ አንድ ስደተኛ በአሜሪካ ውስጥ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃዱ እንዳበቃ ወይንም ከማብቃቱ በፊት የአገልግሎት ጊዜ መጠናቀቅ ነበረበት ብለዋል።

የኒውሶም ቃል አቀባይ ብራንደን ሪቻርድስ የትራንስፖረት ቢሮ ኃላፊው ለኤምቲቪ የመንገድ ደንቦች ላይ የሰጡትን ቃለ ምልልስ በመጥቀስ "በድጋሚ የሴአን 'የመንገድ ደህንንቶች' ጎዶሎ በመሆኑ እውነትን ማሳየት ተስኖታል። መሪውን ለማስደሰት በተደረገ ጥረት በቀላሉ ሊረጋገጡ የሚችሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን አሰራጭተዋል" ብለዋል።

በፍሎሪዳ በመኪና አደጋው ሦስት ሰዎች ከሞቱ በኋላ በመስከረም ወር ላይ ደፊ፣ የንግድ መኪኖችን ለማሽከርከር ስደተኞች መንጃ ፈቃድ እንዳያገኙ የሚያደርግ አዲስ ሕጎችን አስተዋውቀዋል። እንዲሁም ግዛቶች የአመልካቹን የስደተኝነት ሁኔታ ከፌዴራል መሥሪያ ቤት ቋት ውስጥ እንዲያረጋግጡ እና ፈቃዶቹ ቢበዛ ለአንድ ዓመት ብቻ የሚያገለግሉ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

በአዲሱ ሕጎች ላይ ማብራሪያ የሰጠው የትራንስፖርት ቢሮ 97 በመቶ የሚሆኑት በአሁኑ ጊዜ "ለግል አገልግሎት የማይውሉ መኪኖች" አሽከርካሪዎች፣ 194,000 ይሆናሉ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ "የጭነት መኪና ከማሽከርከር ይወጣሉ" ሲል ገምቷል። ነገር ግን በአገሪቱ 3.8 ሚሊየን የንግድ መኪና አሽከርካሪዎች እንዳሉ በመጥቀስ ሕጎቹ ውስን ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ እንደሚኖራቸው አምናለሁ ብሏል።

የፌደራል ይግባኝ ሰሚ ችሎት በዚህ ሳምንት በጭነት መኪና ሹፌሮች የቀረበን ክስ ተከትሎ አዲሱን ሕግ እንዲታገድ አድርጓል።

የኒውሶም ቢሮ 17,000 ፈቃዶች በተሰጡበት ወቅት ደንቦቹ ተፈፃሚ እንዳልሆኑ ገልጿል።

የንግድ ተሽከርካሪዎችን ለማሽከርከር የተሰጡ መንጃ ፈቃዶች ላይ የሚደረገው ምርመራ የተጠናቀቀበት ብቸኛው ግዛት ካሊፎርኒያ ነው። ሌሎች የመንግሥት ግምገማዎች ረቡዕ በተጠናቀቀው የ43-ቀን የመንግሥት መዘጋት ቢዘገዩም በቅርቡ ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት ኩባንያ የሆነው ፍሬሞንት ኮትራት ካሪየርስ እንደገለጸው፣ ከ130,000 በላይ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች የሚኖሩት በካሊፎርኒያ ውስጥ ነው።

ይህም ካሊፎርኒያ በአገሪቱ ውስጥ ሁለቱ ትላልቅ ወደቦች መገኛ በሆነችው እና በግብርና ምርቶች ግንባር ቀደም በመሆኗ ጭመር ነው። ከፍተኛ የአሽከርካሪ ብዛት ያለው የቴክሳስ ግዛት ብቻ ነው።