ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍሪካውያን አገር ቤት ላለ ዘመድ አዝማድ ገንዘብ መላክ ይብቃን እያሉ ያሉት ለምንድን ነው?
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከአገር ውጪ ያሉ አፍሪካውያን አገር ቤት ላሉ ዘመድ አዝማዶች ገንዘብ መላካቸው የነበረ ልምዳቸው ነው።
አሁን አሁን ላይ ግን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አፍሪካውያን ምንም ሳይሰሩ ቁጭ ብለው የእኛን እጅ እየጠበቁ ‘ሸክም’ ለሆኑብን ዘመድ አዝማዶቻችን ገንዘብ መላክ ሰልችቶናል እያሉ ነው።
ኬንያዊቷ ኤልሳ መጂምቦ ቲክቶክ ላይ ባጋራችው ቪዲዮ፤ “እኛ አፍሪካውያን ለሩቅ ዘመድ ሳይቀር ገንዘብ የመላክ ልምዳችንን እንዴት እንደምጣለው!” ማለቷ ብዙ መነጋጋሪያ ሆኖ ነበር።
በብዙዎች ዘንድ አፍሪካውያን ለዘመዶቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ “ብላክ ታክስ” ወይም ጥቁሮች ላይ የተጣለ ግብር ሲሉ ይገልጹታል።
እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ማኅብረሰብ አባላት ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚያቀኑ ሰዎች የሚሰሩት ለራሳቸው ሕይወት ብቻ አይደለም። አገር ቤት ላሉ ወላጆቻቸው፣ወንድም እና እህት፣ አጎት እና አክስት፣ ለአጎት እና አክስት ልጅ ከፍ ሲልም ለባል/ሚስት ዘመዶች ጭምር ነው።
ይኹን እንጂ ብዙዎች ገንዘብ መላክ አግባብነት ላይ ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ።
መኖርያዋን በአሜሪካ ያደረገችው ኬንያዊቷ ኤልሳ አላስፈላጊ እና ካባድ ጫናን የሚፈጥረው ልማድ መቆም አለበት በሚል ሐሳቧን ለማስረጽ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
ኤልሳ ወላጅ አባቷ የሩቅ የሆኑ ዘመዶቹን ሳይቀር ዕድሜ ልኩን ሲረዳ መቆየቱን ትናገራለች። አንድ ቲክቶክ ላይ ባጋራችው ቪዲዮ ላይ በስም የማትጠቅሰውን ዘመዷን ስትወቅስ ትሰማለች።
“እኔ ከመወለዴ በፊት አባቴን ገንዘብ ስትጠይቅ ነበር። አሁን እኔ ተወልጄ ራሴን ከቻልኩ በኋላ እንድረዳህ ልክ እንደ አባቴ እኔም ገንዘብ መጠየቅ ጀመርክ።አንተ ሰነፍ፤ ይህን መጥፎ ልማድህን አላበረታታም” ስትል ትታያለች።
ይህ የኤልሳ ቪዲዮ ብዙ አነጋግሯል። ሃሳቧን የደገፉ በርካቶች እንዳሉት ሁሉ አስተያየቷን የነቀፉ አልጠፉም።
ሌሎች ደግሞ በሃሳቧ ቢስማሙም ለቤተሰብ ገንዘብ ከመላክ ልንቆጠብ አንችልም ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ዕድሜዋ በ50ዎቹ ውስጥ የምትገኝ የዜምባብዌ ተወላጅ ላለፉት 30 ዓመታት 9 ወንድም እና እህቶቿን ስትደግፍ መኖሯን ለቢቢሲ ትናገራለች።
“አንዳንድ ግዜ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ፣ የቤት አስቤዛ ከገዛሁላቸው በኋላ እጄ ላይ የሚቀረው 20 ዶላር ብቻ ነው” ስትል ቁጭት እና ኩራት በተቀላቀለበት ስሜት ትናገራለች።
ይህች ሴት ምንም እንኳ እንደ ምግብ ያሉ መሠረታዊ ወጪዎቿን የምትሸፍነው በብድር ገንዘብ ቢሆንም የማገኘውን ለወንድም እና እህቶቼ መላክ ከእኔ የሚጠበቅ ነገር ተደርጎ ነው የሚታየው ትላለች።
ደሞዟ የእርሷ ብቻ ሳይሆን የመላው ቤተሰብ መሆኑን ትናገራች።
ትዳር ስትመሰርት ደግሞ ጨርሶ ኃላፊነቷ መብዛቱን ትገልጻለች። ይህች ትውልደ ዚምባቢያዊት እንደምትለው ለባሏ ወንድም የትምህርት ቤት ወጪ ለመክፍል ብድር ከባንክ መውሰዷን ትናገራች።
ስሜ አይጠቀስ ያለችው ይህች ትውልደ ዚምባቢያዊት ለባሏ ወንድም ትምህርት ቤት ክፍያ ለመፈጸም ከባንክ የወሰደችውን ብድር ከፍሎ ለመጨረስ ሁለት ዓመታት እንደወሰደባት ታስታውሳለች።
በኡጋንዳ የምትኖረው ሳንድራ አጃሎ የተባለችው የ28 ዓመት ወጣት በበኩሏ አሁን ላለሁበት ደረጃ በውጪ ያሉ ዘመዶች ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ትላለች።
ሳንድራ እና ሦስት ወንድም እና እህቶቿ ያለ አባት በእናታቸው ብቻ ነው ያደጉት። አቅመ ደካማዋ እናታቸው ታዲያ ለአራቱ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ የማሟላት አቅም አልነበራትም።
ይኹን እንጂ በውጪ ያሉ ዘመዶች የትምህርት ቤት ክፍያን ከመፈጸም ባሻገር፣ ለአስቤዛ እና አንዳንዴም ለሕክምና ገንዘብ እንደሚልኩ ሳንድራ ትናገራለች።
“እኛ ሸክም እየሆንባቸው ሳይሆን ይህ መረዳዳት ነው” ስትል የሴቶች ጸጉር ቤት ከፍታ እየሰራች ያለችው ሳንድራ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ቀላል ላይሆን ይችላል (ገንዘብ መላኩ)። አንዳንዴም አሰልቺ ሊሆንባቸው ይችላል። ግን ለእኛ የግድ አስፈላጊ ነው። የትኛውም ሰው እርዳታ ያስፈልገዋል። በተቻለን መጠን መረዳዳት አለብን” ትላለች ሳንድራ።
አሜሪካ በሚገኘው ዌሌስሊይ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናቶች መምህር የሆኑት ቺፖ ዴንዴሬ (ዶ/ር)፤ “ብላክ ታክስ” (ጥቁሮች ላይ የተጣለ ግብር) ገንዘብ ለሚልከው ማለቂያ የሌለው አዙሪት ሊሆን ይችላል ይላሉ።
እንደ ቺፖ (ዶ/ር) ማብራሪያ ከውጪ የሚላክ ገንዘብ ጊዜያዊ ለሆኑ ችግሮች ቀዳዳ መድፈኛ እንጂ አገር ቤት ላለ ሰው በዘላቂነት ሕይወትን ለመቀየር ጥቅም ላይ የሚውል አይደለም።
ቺፖ (ዶ/ር) በበርካታ አፍሪካ አገራት መንግሥታት ለዜጎቻቸው ነጻ የሕክምና አገልግሎት ስለማይሰጡ እንዲሁም የትምህርት ወጪ ስለማይሸፍኑ እና ጡረተኞች በቂ የሚባል ጥቅማ ጥቅም ስለማያገኙ የሌሎችን እጅ የሚጠብቁ ሰዎች እንዲበረክቱ ምክንያት ነው ይላሉ።
“ከመንግሥት የሚገኝ ጡረታ የለም ማለት ይቻላል። ስለዚህ የምንጦራቸው እኛ ነን። የመንግሥትን ስራ እየተወጣ ያለው በውጪ ያለ ዘመድ ነው።”
ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አግሪካልቸር እና ዴቨሎፕመንት የተባለ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም እንደሚለው ከሆነ እአአ 2023 አፍሪካውያን ወደ አገር ቤት የላኩት የገንዘብ መጠን 95 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ማለት ከኬንያ ኢኮኖሚ ጋር የሚስተካከል ነው።
በውጪ ያሉ ሰዎች ጠርቀም ያለ ገንዘብ በቀላሉ ያገኛሉ የሚለው እምነት በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ መኖሩ ደግሞ ሁኔታውን ከባድ ያደርገዋል።
መኖሪያውን በጀርመን ያደረገው የዚምባብዌ ተወላጅ የሆነው የ35 ዓመቱ ጋቤ ሙትስዬክዋ ለቤተሰቡ በሚልከው ገንዘብ ምክንያት መቆጠብ አለመቻሉን ያስረዳል።
ለአምስት ዓመታት በጀርመን የኖረው ጋቤ ገና ተማሪ ሳለ በትርፍ ሰዓቱ ሰርቶ ካገኘው ገንዘብ 2ሺህ ዩሮ ለቤተሰቡ መላኩን ያስታውሳል።
ከትምህርት በኋላም በቋሚነት ለቤተሰቡ የሚልከው ገንዘብ ለራሱ የወደፊት ሕይወት ገንዘብ እንዳይቆጥብ እንዳደረገው ለቤተሰቡ መናገሩን ይገልጻል።
“ለቤተሰብ ያለብኝ ኃላፊነት እና በራሴ የፋይናንስ ሁኔታ መካከል መጣጣም መኖር አለበት” የሚለው ጋቤ፤ አንዳንድ ግዜ ዘመዶቻችን የእኛ ገንዘብ የራሳቸው አድርገው የሚያስቡበት አጋጣሚ አለ ይላል።
ይህ ‘ብላክ ታክስ’ ስለተባለው ጽንሰ ሐሰብ ከተራ አፍሪካውያን እስከ እውቅ ሰዎች መነጋገርያ ሆኗል።
ከጥቂት ወራት በፊት የቀድሞ የቼልሲ እና የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ጆን ኦቢ ሚኬል “አፍሪካዊ ሆነህ ገንዘብ ካገኘህ ያ ገንዘብ የአንተ ብቻ አይደለም” ሲል ተናግሮ ነበር።
“ብዙ ዘመድ ካለ፣ በርካታ የአክስት እና አጎት ልጆች ካሉህ፣ የምታገኘው ገንዘብ የአንተ ብቻ አይደለም” ሲል ነበር የተናገረው።
የቀድሞ እግር ኳሰኛው ዘመዶቹ የልጆቻቸውን ወጪ የመሸፈን ኃላፊነት የእርሱ አድርገው እንደሚመለከቱ ጨምር ተናግሮ ነበር።