በስድስት ሰዓታት ውስጥ ሚስቱን እና ልጆቹን ጨምሮ የሕይወቱን 12 ዓመታት የረሳው ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶ/ር ፒየርደንቴ ፒቺዮኒ የሕይወቱ 12 ዓመታት ሙሉ በሙሉ ተወስዶበታል። በአውሮፓውያኑ 2013 ባጋጠመው የመኪና አደጋ የጭንቅላት ጉዳት ከደረሰበት ወዲህ ትውስታው ሁሉ ጥርግርግ ብሎ ጠፍቷል።
በሚቀጥለው ቀን በሆስፒታል አልጋ ላይ ሲነቃ 2001 ላይ ያለ መስሎት ነበር።
ሚስቱንም ሆነ ትልልቅ ልጆቹን አያስታውሳቸውም።የበለጠ የሚያስደነግጠው ደግሞ ወደሚወደው የሕክምና ሙያ መመለስ አለመቻሉ ነው።
ፒየርዳንቴ፣ ጓደኞቹ ፒየር ሲሉ ነው የሚጠሩት፣ ከአደጋው በፊት የነበረው ማንነቱን ለመፈለግ በብዙ ጥሯል።
ከዚህ በፊት የተለዋወጣቸውን ኢሜይሎች ሲበረብር የተደበቀ ማንነት እንዳለው ተረዳ።
የእርሱ ታሪክ ከማንም ጋር የሚገጥም አልነበረም። ስለዚህ በጣልያን የሚገኝ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ድራማ መነሻ ሃሳብ አድርጎ ተጠቅሞታል።
በቴሌቪዝን ድራማው ላይ ወጣቱ ዶክተር በጥይት ከተመታ በኋላ የ12 ዓመት ትውስታው ጠፍቶበታል።
ፒየር በጣሊያን ከተማ ሎዲ ከተኛበት ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል እአአ ግንቦት 31/2013 ከገባበት ሰመመን ነቃ።
"መጀመሪያው ያየሁት ነጭ መብራት ነው። እርሱም ባልደረቦቼ ከአደጋው በኋላ ያስተኙኝ የድንገተኛ ክፍል ብርሃን ነበር። ለስድስት ሰዓታት ያህል ኮማ ውስጥ ቆይቻለሁ እና ከገባሁበት ሰመመን ስነቃ የባልደረባዎቼን ዓይኖች ብቻ አየሁ።
"'ዛሬ ቀኑ ምንድን ነው?' ሲሉ ጠየቁኝ፤ ለአምስት፣ ለስድስት ሰከንድ አሰብኩና 'ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ነው' ብዬ መለስኩኝ።"
ከዚያም አንድ የሥራ ባልደረባው አይፓድ ላይ ሲጽፍ ተመለከተ። እአአ በ2001 ውስጥ ያልነበረ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ነበር።
በወቅቱ የነበሩት የተንቀሳቃሽ ስልኮች ማድረግ የሚችሉት መደወል እና ጥሪ መቀበል እንዲሁም የጽሑፍ መልዕክት መላክ ብቻ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Sylvain Lefevre / Getty Images
ከዚህ የባሰው የመጣው ከዚህ በኋላ ነው። "ሚስትህን ማየት ትፈልጋለህ? ሲሉ ጠየቁኝ።"
"እንዴታ፤ 'ሚስቴን ማየት እፈልጋለሁ' ስል መለስኩ"
"በአእምሮዬ ውስጥ የነበረው፣ ሚስቴን የጠበቅኳት [ወደ ተኛሁበት ክፍል ውስጥ ስትገባ] 12 ዓመት ወጣት ሆና ለማየት ነበር። ነገር ግን ወደ ክፍሌ ውስጥ የገባችው ሴት ሚስቴ ሳትሆን እርሷን የምትመስል ሴት ነች። ፊቷ ላይ በጣም ብዙ ሽብሸብ አለባት።"
ፒየር ልጆቹ አድገው ትልቅ ሰው መሆናቸውንም መቀበል ነበረበት።
"ማን ናችሁ? ብዬ ጠየቅኳቸው ልጆቼ የት ሄዱ? ምክንያቱም ልጆቼ መሆናቸውን ማመን አልቻልኩም።"
ከዘያ በኋላ ግን ሚስቱ ያስደነገጠውን ዜና ነገረችው። በአእምሮው ውስጥ በጣም ጤነኛ የነበሩት "እናቱ" ከሦስት ዓመት በፊት መሞታቸውን ነገረችው።
"ስነቃ፣ 53 ዓመቴ እንደሆነ ነበር የተሰማኝ፤ ግን 65 ዓመት እንደሆነኝ በኋላ ላይ ተረዳሁ።"
ክፉ ማንነቱ
ከአእምሮው የትውስታ ማኅደር ውስጥ የጠፋውን 12 ዓመት ለመመለስ የተለያዩ ማስረጃዎችን ሲቆፍር ፒየር በዚያ ጊዜ ውስጥ ሁሉ ደስተኛ ሰው እንዳልነበረ ተረዳ።
"ጓደኞቼን፣ የሥራ ባልደረቦቼን፣ ባለቤቴን ምን ዓይነት ሰው ነበርኩ ስል ጠየኳቸው። መልካም ሰው ነበርኩ ወይስ መጥፎ?"
"ባልደረቦቼ የድንገተኛ ክፍሉ አለቃ ሆኜ ስሾም በስሬ 230 ሰዎች ይሠሩ አንደነበር ነገሩኝ።"
በጣም የሚረብሽ አገላለጽ አላቸው።
"ቅጽል ስሜ 'ጋጥወጡ ልዑል' የሚል ነበር።"
ፒየር ሥራ ቦታው ዶክ ተብሎ የሚጠራ ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት ራሱን እንደ መጥፎ ሰው አድርጎ አስቦ ስለማያውቅ ለማመን እንደተቸገረ ናገራል።
"'በጣም በጣም ጨለምተኛ ነበርክ ሲሉ ነገሩኝ። በጣም በጣም ትጉህ ነበርክ. . . ነገር ግን ሌሎች ሰዎች ላይ በጣም ጨካኝ ነበርክ።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፒር የጠፉት ዓመታት፡ ትክክለኛ ማንነቱን መፈለግ
ፒየር በእነዚያ በጠፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ነገሮች መለዋወጣቸውን ሲረዳ የራሱን ትክክለኛ ማንነት ለማወቅ ጥረት ማድረግ ጀመረ።
"የተለዋወጥኳቸውን ሁሉንም ኢሜይሎች አነበብኳቸው። ከ76,000 በላይ ነበሩ። ማን እንደነበርኩ ለመረዳት ስሞክር በጥቂት ኢሜይሎች ውስጥ መጥፎ ሰው መሆኔን አግኝቼበታለሁ። መጥፎ ሰው እነደነበርኩ ማመን ይኖርብኛል፣ መጥፎ አለቃ፣ ክፉ ሰው።"
ኢሜይሎቹን ሲያገላብጥ የሥራ ባልደረቦቹ የነገሩት እውነት መሆኑን ተረዳ። "ኢሜይሎቹን በሙሉ ሳነብ በጣም በጣም ነው ያዘንኩት።"
ፒየር መልካም ሰው ለመሆን ወሰነ።
"በየቀኑ የዕለት ማስታወሻ ለመጻፍ ወሰንኩ። የተሰማኝን መጻፍ ጀመርኩ። በቀን ውስጥ አስፈላጊ የነበሩ ወይንም የማይረቡትንም ጨምሮ ጻፍኩኝ። ትክክል ባልሆነ ጊዜ ውስጥ የተገኘሁ ትክክል ያልነበርኩ ሰው ነኝ። ያ አልነበረም የኔ ጊዜ። ልረዳው በማልችለው ዓለም ውስጥ የነበርኩ፤ ባዕድ ሰው ነበርኩ። ብቸኝነት ተሰማኝ። ማንም እንደማይረዳኝ ዓይነት ተሰማኝ።"
ፒየር በጣም ድብታ ውስጥ ገባ።
"ለረዥም ጊዜ ብቸኝነት ተሰማኝ። ምክንያቱም እናቴ ሞታለች፣ ልክ ልጆቼ የሞቱ ያህል ነው የተሰማኝ፤ ስለዚህ ለምን እኖራለሁ? በዚያ ጊዜ ራሴን ስለማጥፋት አሰብኩ። ምክንያቱም ይህ የኔ ዓለም አይመስልም ነበር።"
ነገር ግን ፒየር ራሱን የሚያነቃቃበት እና አሉታዊ አመለካከቶችን የሚያስወግድበት መንገድ አገኘ።
ሚስቴን ዳግም አፈቀርኳት
ፒየር የመኪና አደጋ ሳያጋጥመው በፊት፣ ሕይወቱ 12 ዓመታት ደብዛቸው ሳይጠፋ በፊት በቀን 15 እና 16 ሰዓታት በሥራ ተጠምዶ ይውል ነበር።
ባለቤቱ እንደምትለው የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ከሆነ በኋላ ቤት የሚቆይበት ጊዜ እጅጉን እያነሰ መጥቷል።
"ባለቤቴ 'ፍቅረኛ ይኖርህ አይኑርህ ወይም ከአንድ በላይ ፍቅረኛ ይኖርህ አንደሆን ማወቅ አልቻልኩም። . . . ምክንያቱም በጣም ሥራ ወዳድ በሥራ የተጠመድክ ነበርክ።"
ፒይር በቤቱ ውስጥ ዳግም ፍቅሩን ማደስ ፈለገ። ለአጭር ጊዜ ራሱን ስቶ ከነበረበት ሲነቃ ዳግም ሚስቱን ሲያገኛት ፍቅሩ እንደ አዲስ ጀመረ።
"ባለቤቴ ወደ ተኛሁበት ክፍል ውስጥ ስትገባ ከጀርባ ነው ያየኋት። ከዚያ በፍቅር ወደቅኩ። በጣም ደስ የሚል ስሜት ነበር የተሰማኝ።"
የሚያስታውሳት ዓይነት ሴት አልነበረችም። ሌላ ሰው እንደሆነች ነው የተሰማው።
እርሱም "እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም ሚስቴን በሚስቴ ያጭበረበርኩት። ምክንያቱም ሌላ ሰው ነበረች። እናም ከእርሷ ጋር ዳግም ፍቅር ያዘኝ" ይላል።
ፒየር የወደፊት ሕይወቱ በብሩህ ነገሮች የተሞላ እንደሆነ ያምናል።
"በግል የወደፊት የሕይወት ጉዞዬ በጣም እኮራለሁ፤ . . . . አዲስ ለማድረግ፣ ዳግም ደስ የሚሉ ትዝታዎችን ለማስቀረት እጥራለሁ። ይህ የእኔ ልዩ ኃይል ነው።"















