ትራምፕ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸውን ወደ ሩሲያ አስጠጋለሁ ያስባላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ እሰጥ አገባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በማኅበራዊ ሚዲያ የሰጡት አስተያየት ያበሳጫቸው ዶናልድ ትራምፕ ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸው ወደ ሩሲያ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
በዚህም የተነሳ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የማኅበራዊ ሚዲያ የቃላት ጦርነት አድጎ ወደ ኒውክሌር ፍጥጫ ሊያመራ ይችል ይሆን? የሚል ጥያቄን አጭሯል።
ትራምፕ ለወሰዱት እርምጃ የሩሲያስ ምላሽ ምን ይሆናል? በሩሲያ እና በአሜሪካ የኒውክሌር ፍጥጫ ላይ ለመግባት መንገድ ላይ ናቸው?
በአሜሪካና በሩሲያ መካከል በአውሮፓውያኑ 1962 የተከሰተው እና የኩባ የሚሳዔል ቀውስ ተብሎ የሚጠራው የ13 ቀናት ፍጥጫ ዓይነት ይፈጠር ይሆን?
ሩሲያን በማየት ይህ የሚፈጠር አይመስልም።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የትራምፕ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦችን አስጠጋለሁ ትዕዛዝን በማጣጣል ነው የዘገቡት።
አንድ የሩሲያ የጦር አዛዥ 'ሞስኮቭስኪ ኮምሶሞሌትስ' ከተባለ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ትራምፕ "ዝም ብለው በንዴት ተሞልተው እየበጠበጡ" ሲሉ ነው ነገሩን ያቃለሉት።
አንድ ጡረተኛ ሌተናንት ጄነራል በበኩላቸው 'ኮመርሳንት' ለተባለ የሩሲያ የመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ስለ ሰርጓጅ መርከቦች የተናገሩት "ትርጉም የሌለው መቀባጠር ነው፤ በዚህ ነው ደስታውን የሚያገኘው" ብለዋል።
"ትራምፕ ሰርጓጅ መርከቦችን በተመለከተ ምንም ዓይነት ትዕዛዝ እንዳልሰጡ እርግጠኛ ነኝ" ሲሉ አንድ የሩሲያ ደኅንነት ባለሙያ ለዚሁ ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኮመርሳንት በተጨማሪ ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በአውሮፓውያኑ 2017 ሰሜን ኮሪያን ለማስጠንቀቅ በሚል ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦችን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር (ፔኒንሱላ) መላካቸውን መግለጻቸውን አስታውሷል።
ሆኖም በወቅቱ ይህንኑ ያሉትን ማስፈራሪያ ትተው ብዙም ሳይቆዩ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ጋር ተገናኙ።
ምናልባትም በአስገራሚ ሁኔታ የዶናልድ ትራምፕ የኒውክሌር የባሕር ሰርጓጅ መርከቦች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ ማለታቸው የቀጣዩ የአሜሪካ-ሩሲያ ጉባኤ እንደሚካሄድ ማመላከቻ ይሆን? ከዚያ ብዙም ላይርቅ ይችላል።
ነገር ግን ከሩሲያ ባለሥልጣናት በኩል ምላሽ አለመሰጠቱ አስገራሚ ነው።
ምላሾች ይዥጎደጎዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሩሲያ "ዝምታ ነው መልሴ" ብላለች።
የሩሲያው ቤተ መንግሥት ክሬምሊንም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጡም። የሩሲያው መከላከያ ሚኒስቴርም እንዲሁ ጭጭ እንዳለ ነው።
ሩሲያ ለአሜሪካ አጸፋዊ በሆነ መልኩ ኒውክሌር ተሸካሚ ሰርጓጅ መርከቦቿን ወደ አሜሪካ አስጠጋለሁ አላለችም።
ይህም ምናልባት ሩሲያ ሁኔታውን እያጠናች እና ምን ማድረግ እንዳለባት እየገመገመች ሊሆን ይችላል ወይም ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላት ያሳያል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሩሲያ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላት የሚጠቁሙ ናቸው።
ትራምፕ እና የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሜድቬዴቭ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ለቀናት እርስ በርስ እየተዋረፉ ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ ለሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት ቋጭታ የሰላም ስምምነት ላይ እንድትደርስ የሰጡትን የ50 ቀናት ቀነ ገደብ ወደ ሁለት ሳምንት ማውረዳቸውን ተከትሎ ነው የሁለቱ ባለሥልጣናት የቃላት ጦርነት የተጧጧፈው።
ትራምፕ ለሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጦርነቱን በነዚህ ቀናት ውሰጥ ካላቆሙ ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልካቸው ነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ያነጣጠረ ከባድ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።
ሜዴቬዴቭ ትራምፕ ከሩሲያ ጋር "በቀነ ገደብ እየተጫወተ ነው፤ እያንዳንዷ አዲስ የቀነ ገደብ ዛቻ የጦርነት እርምጃ ነው" ሲሉ በማኅበራዊ ገጻቸው ተችተዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በመወፈረፍ እና በማስፈራራት የመለሱ ሲሆን "ሥልጣን ላይ ነኝ ብሎ አሁንም ለሚያስበው የከሸፈው የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሜድቬዴቭ ለሚናገረው ነገር እንዲጠነቀቅ ንገሩት። ወደ አደገኛ ሁኔታ እየገባ ነው" ብለዋል።
ሜድቬዴቭ በቀጣዩ የቴሌግራም ልጥፋቸው "የማያስፈልግ ዛቻ" ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን፣ ይህንን ለመግለጽ የተጠቀሙበት "ዴድ ሃንድ" የሶቭየት ኅብረት አጸፋዊ የኒውክሌር ሥርዓት ኮድ ስም መሆኑን አንዳንድ ወታደራዊ ተንታኞች ገልጸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ይህንን ማለታቸውን ተከትሎ ትራምፕ ሰርጓጅ የኒውክሌር መርከቦቻቸው እንዲንቀሳቀሱ እና "በተገቢ ቀጣናዎች እንዲሰማሩ" ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ሜድቬዴቭ "ተንኳሽ" አስተያየት ሰጥተዋል ያሉት ትራምፕ ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸው ተንቀሳቅሰው "በተገቢው ቀጣና" ላይ እንዲሰማሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕ ሁለቱ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦች "በተገቢው ቀጣና" ከማለት ውጪ የት እንደሚሰፍሩ አልገለጹም።
ትራምፕ፤ ለሩሲያ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ቋጭታ የተኩስ አቁም እንድታደርግ ቀነ ገደብ አስቀምጠው ካለበለዚያ ማዕቀብ ይጣልባታል በሚል ማስፈራራታቸውን ተከትሎ ነው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠንከር ያለ ምላሽ የሰጡት።
ሩሲያን ከአውሮፓውያኑ 2008 እስከ 2012 የመሩት ሜድቬዴቭ እንደ ሊበራል መሪ ይታዩ ነበር። "ነጻነት፣ ነጻነት ካለመኖር ይሻላል" በሚለው ታዋቂ አባባላቸው ይታወሳሉ።
ሆኖም በቅርብ ጊዜያት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጦረኝነትን የሚሰብኩ ሆነዋል።
በተለይም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በኃይል የተሞሉ እና ፀረ-ምዕራባውያን የማኅበራዊ ሚዲያ አስተያየቶችን በመለጠፍ ታዋቂ ሆነዋል።
የቀድሞው መሪ እንደ ክሬምሊን ድምጽ ስለማይታዩ በርካታ ልጥፎቻቸው ዝም ብለው ይታለፉ ነበር።
በድንገት ግን በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ታየ፤ መታየት ብቻ አይደለም ትራምፕን በከፍተኛ ሁኔታ አበሳጫቸው።
የማኅበራዊ ሚዲያን ልጥፍ አለመውደድ አንድ ነገር ነው፤ በርካቶችም ይህ አንዴ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ተሰምቷቸው ይሆናል።
ነገር ግን ልጥፉን ካለመውደድ ብዛት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦችን ማሰማራት ከማስገረም በላይ ነው።
እናም ትራምፕ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦቻቸው ወደ ሩሲያ ቀረብ ብለው እንዲሰማሩ ለምን ትዕዛዝ ሰጡ?
ትራምፕ ራሳቸው ከኒውስማክስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለዚህ ውሳኔያቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል "ሜድቬዴቭ ስለ ኒውክሌር አንስቶ በጣም መጥፎ ነገሮችን ብሏል። ኒውክሌር የሚለው ቃል ሲጠቀስ ዓይኔ ይፈጣል፤ እናም የመጨረሻው ዛቻ ስለሆን መጠንቀቅ ይሻላል እላለሁ" ብለዋል።
ሜድቬዴቭ በማህበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ በኒውክሌር ያስፈራራሉ ሲባል ከመቆየቱ አንጻር ይህ አዲስ አይደለም።
ግልጽ የሆነው ነገር ትራምፕ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አስተያየት ለሳቸው እንደተባለ አድርገው ነው ምላሸ እየሰጡ ያሉት።
ወይስ ይህ የትራምፕ አስተያየት የስትራቴጂያቸው አካል ነው?
ትራምፕ በፖለቲካ፣ በንግድ ያልተጠበቁ ነገሮችን ማከናወን ሁልጊዜም የሚያደርጓቸው ጉዳዮች ናቸው። ያልተጠበቁ እርምጃዎችን በመውሰድ ከንግግር ወይም በድርድር ወቅት ተቃናቃኞቻቸውን ሚዛን ማሳጣት ትራምፕ የሚጫወቱት ነው።
ለምሳሌ የዩክሬንን ጦርነት ለመቋጨት የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ማሳማራት በዚሁ በትራምፕ ያልተጠበቁ ውሳኔዎች ሊወድቅ ይችላል።















