ኢላን መስክ የአሜሪካ ግምጃ ቤት መረጃዎችን እንዳይመለከት በፍርድ ቤት ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ የኢላን መስክ መሥሪያ ቤት በግምጃ ቤት የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያንን መረጃ እንዳይመረመር አግደዋል።
ዲፓርትመንት ኦፍ ገቨርንመንት ኤፊሸንሲ አሊያም ዶጅ እየተባለ የሚጠራው ፕሬዝደንት ትራምፕ ለኢላን መስክ ያቋቁመት መሥሪያ ቤት በአሜሪካ ብዙ ነውጥ እየፈጠረ ነው።
ዳኛ ፖል ኢንግልሜየር ቅዳሜ ባሳለፉት ውሳኔ ኢላን መስክ እና የቡድኑ አባላት እስካሁን የሰበሰቡትን መረጃ በፍጥነት እንዲያጠፉ አዘዋል።
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለውጥ እንዲያመጣ የተቋቋመው የመስክ መሥሪያ ቤት የግምጃ ቤትን መረጃዎችን ለመመርመር ይሁን ማግኘቱን ተከትሎ ነው የ19 ግዛቶች አቃቤ ሕጎች ክስ ያቀረቡት።
ክሱ እንደሚለው ዶጅ የተባለው መሥሪያ ቤት ኦፊሴሊያዊ የመንግሥት ቢሮ ስላልሆነ ውሳኔው የፌዴራል ሕግን የሚጥስ ነው።
ኢላን መስክ የዳኛውን ውሳኔ ተከትሎ በኤክስ ገፁ ባሰማው ቅሬታ "እጅግ የሚገርም ነው" ብሏል።
"ገንዘቡ ምን እንደዋለ ሳናውቅ እንዴት አድርገን ነው የግብር ከፋዮች ገንዘብ እንዳይባክን እና ማጭበርበርን ማስቆም የምንችለው?" ሲል ፅፏል።
የዲሞክራት ግዛቶች አቃቤ ሕጎች ናቸው ትራምፕ፣ ግምዣ ቤት እና የግምጃ ቤት ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት ላይ ክስ ያቀረቡት።
ዳኛው ለውሳኔያቸው ማብራሪያ ሲሰጡ "ስሱ የሆኑ እና ሚስጢራዊ መረጃዎች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ" ብለዋል።
የዳኛው ውሳኔ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውጭ ያለ ሰው የሚኒስቴሩን ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ተሿሚዎችን እና የሌሎች ሠራተኞችን መረጃ ማግኘት አይችልም ይላል።
ዳኛው አክለው እስካሁን መረጃ ያገኙ ሰዎች በእጃቸውን ያለውን 'ኮፒ' ወዲያውኑ እንዲያጠፉት አዘዋል።
ክሱን ካቀረቡት መካከል አንዱ የሆኑት የኒው ዮርክ አቃቤ ሕግ ሌቲካ ጄምስ የትራምፕ አስተዳደር የኢላን መስክ ዶጅ የግላ መረጃን እንዲያገኝ "ያልተገደበ ፈቃድ" ሰጥተዋል ይላሉ።
"ባለፈው ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ የኒው ዮርክ ነዋሪዎች ግላዊ መረጃቸው ለኢላን መስክ እና ለዶጅ ተላልፎ መሰጡትን ነግረውኛል" ብለዋል።
ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ሆነው እንዲመረጡ ትልቅ ተጋድሎ አድርጓል።
በመስክ የሚተዳደር ዶጅ የተባለው መሥሪያ ቤት ዩኤስኤይድ የተባለው የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት የሚደጉመውን ገንዘብ እንዲቀንስ እርምጃ ወስዷል።
የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምር ለበርካታ ሀገራት በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ድጋፍ ያደርጋል።












