ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በውጭ ምንዛሬ ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ ማግኘት ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, National Bank of Ethiopia
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ (አካውንት) ያላቸው ደንበኞች የቪዛ እና የበረራ ትኬት ማቅረብ ሳይጠበቅባቸው ለዓለም አቀፍ የበይነ መረብ (ኦንላይን) ግብይቶች የሚውል የውጭ ምንዛሬ ክፍያ ካርድ እንዲያገኙ ፈቀደ። የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ ለመክፈት ተቀምጦ የነበረው የ100 ዶላር የግዴታ ተቀማጭ ገንዘብም እንዲቀር ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትናንት ረቡዕ የካቲት 4/2018 ዓ. ም. የውጭ ምንዛሬ መያዝ፣ ማግኘት እና መጠቀምን በተመለከተ የተቀመጡ ገደቦችን ይበልጥ ያላላ ማሻሻያ ይፋ አድርጓል። ብሔራዊ ባንክ አዲሶቹን ለውጦች ይፋ ያደረገው በሐምሌ 2016 ዓ. ም. በወጣው የውጭ ምንዛሬ መመሪያ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ነው።
አረንጓዴው መጽሐፍ በመባል የሚጠራው ይህ መመሪያ የወጣው በሐምሌ 2016 ዓ. ም. የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ መሆን ሲጀመር ነበር። መመሪያው የውጭ ምንዛሬ ከመንግሥት ተመን ወጥቶ ገበያ መር እንዲሆን ያስቻለ መሆኑም ይታወሳል።
አሁን የተደረገው ማለውጥም ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ ላይ የተደረጉ ለውጦች አካል እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አዲሶቹ ማሻሻያዎች "የውጭ ምንዛሬ ገበያን የበለጠ ለማጎልበት በማሰብ" ተግባራዊ እንደሆኑም ገልጿል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ባንኮች እና የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችን መስጠት የሚችሉት ወደ ውጭ ለሚጓዙ ደንበኞቻቸው ነበር። የውጭ ምንዛሬ የሚጫንበትን ይህንን ካርድ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን የውጭ ጉዞ ትኬት እና ቪዛ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር።
ይህም ኢትዮጵያውያን ከዓለም አቀፍ የበይነ መረብ (ኦንላይን) የግብይት መድረኮች እቃዎችን እንዳይሸምቱ ወይም የሚፈልጓቸው አገልግሎቶች ለማግኘት የደንበኝነት ምዝገባ (subscription) እንዳይፈጽሙ አድርጓቸው ቆይቷል።
ብሔራዊ ባንክ ትናንት ይፋ ባደረገው ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ካርድ ለማግኘት ተቀምጦ የነበረውን የውጭ ጉዞ ቅድመ ሁኔታ አንስቷል።
ባንኮች ለደንበኞቻቸው "በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ካርዶችን እንዲያወጡ እና በሒሳብ ባለቤቱ ጥያቄ መሠረት የቪዛ እና የጉዞ ትኬት ሳያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ እንዲጭኑ" እንደተፈቀደላቸው አዲሱ መመሪያ ያስረዳል።
ባንኮች የሚሰጡት ካርድ "ለውጭ አገር ክፍያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት" ጭምር የሚያገለግል እንደሚሆን ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።
የባንኩ መግለጫ እንደሚያስረዳው ዓለም አቀፍ ካርድ ማውጣት የሚችሉት የውጭ ምንዛሬ አካውንት ያላቸው ደንበኞች ናቸው።
ብሔራዊ ባንክ በተመሳሳይ የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ ለመክፈት ተቀምጦ የነበረው የ100 ዶላር አነስተኛ ተቀማጭ እንዲቀር ወስኗል። የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ ለመክፈት ምን ያህል ዶላር መቀመጥ አለበት የሚለውን ባንኮቹ ራሳቸው እንዲወስኑ መፈቀዱን መመሪያው ላይ ሰፍሯል።
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ በሚገኝባቸው ሌሎች መንገዶች ላይም ተቀምጦ የነበረውን ቪዛ እና የጉዞ ትኬት የማቅብ ግዴታ አስቀርቷል። በቀደመው አሠራር ለሕክምና ወደ ውጭ የሚጓዙ ሰዎች የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ቪዛ፤ ከተቻለም የጉዞ ትኬት እንዲያቀርቡ ይጠየቁ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲሱ መመሪያ መሠረት ለሕክምና እና ትምህርት ወደ ውጭ የሚጓዙ ሰዎች ቪዛ እና የአውሮፕላን ትኬት ሳያቀርቡ እስከ 20,000 ዶላር ድረስ ማግኘት ይችላሉ።
ሌላኛው የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ አገር ገንዘብ መላክ ከሚችሉበት መንገድ ጋር የተያያዘ ነው። በአዲሱ አሠራር የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ ያለው ደንበኛ "ለትዳር አጋሩ እና ለልጆቹ የትምህርት፣ የሕክምና እና የጉዞ ወጪ ክፍያ" መፈጸም ተፈቅዶለታል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን "ከአገር ውጭ ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው እገዛ" የሚውል እስከ 3,000 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ወደ ሌላ አገር መላክ ይችላሉ። ይህንን የውጭ ምንዛሬ የሚልኩበትን አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ እንዳለባቸው መመሪያው ላይ ተጠቅሷል።
ከ10,000 ሺህ ዶላር በላይ ይዘው ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ነዋሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው በጉምሩን የማሳወጅ አሠራር በአዲሱ ማሻሻያ እንዲቀር ተደርጓል። "የትኛውንም ያህል መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ያለ ጉምሩክ ሰነድ" መመንዘር ውይም ተቀማጭ ማድረግ እንደሚቻል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
ከተመዘገቡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች የተጣራ ትርፍ ወይም የትርፍ ድርሻ የሚያገኙ አካላት ገንዘባቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የሚከተሉት አሠራርም በአዲሱ ማሻሻያ ተቀይሯል። ከዚህ ቀደም በነበራው አሠራር ይህ ፈቃድ የሚሰጠው በብሔራዊ ባንክ ነበር።
ትናንት ይፋ የተደረገው አሠራር ደግሞ ባንኮች፤ "ዕውቅና ከተሰጣቸው እና ከተመዘገቡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች የሚገኝ የተጣራ ትርፍ ወይም የትርፍ ድርሻ ወደ ውጭ አገር እንዲላክ የመፍቀድ" ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።
ባንኮች ይህንን ፈቃድ ሲሰጡ ግን ወደ ውጭ የሚላከው የገንዘብ መጠን በዚያን "ጊዜ ከተገኘው ጠቅላላ ትርፍ ወይም የትርፍ ድርሻ የማይበልጥ መሆኑን" ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች በሌላ አገር መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ሚያደርጉበት አሠራር በአዲሱ መመሪያ ተዘርግቷል። ተቋማቱ በውጭ አገር ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት "የመዋዕለ ነዋያቸውን ሁኔታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያስመረመሩ" ሲፈቀድላቸው እንደሆነ ተገልጿል።















