አማቶቿን በመርዛማ እንጉዳይ የገደለችው አውስትሪያላዊት የፈጠረችው ድንጋጤ

አማቶቿን በመርዛማ እንጉዳይ በመግደል ጥፋተኛ የተባለችው ኤሪን ፓተርሰን

የፎቶው ባለመብት, Nine

የምስሉ መግለጫ, አማቶቿን በመርዛማ እንጉዳይ በመግደል ጥፋተኛ የተባለችው ኤሪን ፓተርሰን

በአውስትራሊያ አማቶቿን በመርዛማ እንጉዳይ የገደለችው ግለሰብ አውስትራሊያውንን ብቻ ሳይሆን ታሪኩን የሰሙትን ሁሉ አስደንግጧል።

ጉዳዩ የተፈጠረው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በገጠራማ አውስትራሊያ ነዋሪ የሆነችው ኤሪን ፓተርሰን የተሰኘችው ግለሰብ አማቶቿን ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም. ለምሳ ግብዣ ጠራቻቸው።

ከሳምንት በኋላ ግን ያልተጠበቀው ደርሶ ሦስቱ ሲሞቱ፣ አንደኛው ከሳምንታት ሕክምና በኋላ ሕይወታቸው ተርፏል።

ግለሰቧ ሆን ብላ አማቶቿን በዱር እንጉዳይ በመመረዝ ክስ ተመሠረተባት።

ሞርዌል በተሰኘችው አነስተኛ ገጠራ ከተማ ለረጅም ጊዜ ከቆየ የፍርድ ሂደት በኋላ፤ ግለሰቧ ሦስቱን ዘመዶቿን (አማቶቿን) በመመረዝ እንዲሁም በአንደኛው የግድያ ሙከራ ጥፋተኛ ተብላለች።

የ70 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የነበሩት የባሏ አባት ዶናልድ ፓተርሰን እና እናት ጌይል ፓተርሰን፣ የባለቤቷ እናት እህት የ66 ዓመቷ ሄዘር ዊልኪንሰን ሕይወታቸው አልፏል።

የሄዘር ባለቤት እና ፓስተሩ ኢያን ዊልኪንሰን ተርፈው በሆስፒታል ለሳምንታት ሕክምና ካደረጉ በኋላ አገግመዋል።

ፍርድ ቤቱ ሰኞ፣ ሰኔ 30/2017 የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲያሳልፍ ኤሪን በፀጥታ ተሞልታ ትታይ ነበር።

ራሷን የእንጉዳይ አፍቃሪ እንዲሁም የሚበሉ ዕጽዋት ሰብሳቢ ብላ የምትጠራው ኤሪን ለችሎቱ "አሰቃቂ አደጋ" ነው በሚል ምስክርነቷን ሰጥታ ነበር።

ነገር ግን ዘጠኝ ሳምንታትን በፈጀው የፍርድ ሂደት ግለሰቧ 'ዴዝ ካፕ' ተብሎ የሚጠራውን ገዳይ እንጉዳይ በመጠቀም አማቾቿን ለሞት እንዳደረገቻቸው ማስረጃዎች ቀርበዋል።

ግለሰቧ በሐሰት ካንሰር አለብኝ በሚል አማቶቿን አታላ ይህንን "ገዳይ ምግብ" አቅርባላቸዋለች ተብሏል። ወንጀሏንም ለመደበቅ ለፖሊስ እንደዋሸች እና መረጃዎችንም ለማጥፋት ሞክራ እንደነበር ፍርድ ቤቱ መረጃ አግቻለሁ ብሏል።

ቢፍ ዌሊንግተን የተሰኘው ምግብ

የፎቶው ባለመብት, Supreme Court of Victoria

የምስሉ መግለጫ, ቢፍ ዌሊንግተን የተሰኘው ምግብ

ብርቱካናማው ሰሐን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚያች ቅዳሜ ዕለት ጌይል እና ዶናልድ አማታቸው ቤት የደረሱት "የብርቱካን ኬክ" ይዘው ነበር።

ከእነሱም ጋር ባል እና ሚስቱ ዊልኪንሰኖች አብረዋቸው ነበሩ።

በዚህ ምሳ ላይ የኤሪን ባለቤት ሲሞን ፓተርሰን አልተገኘም።

ከባለቤቱ ጋር የተለያየው እና በግጭት ውስጥ ያለው ሲሞን ባልና ሚስቱ እንዲህ በጸብ በሚናጡበት ወቅት ምሳ ላይ መገኘት "ምቾት ነስቶኛል" በሚል ከአንድ ቀን በፊት አልገኝም አለ።

ኤሪን በዚያች ዕለት ማለዳውን ቢፍ ዌሊንግተን የተሰኘው እና ስቴክ በእንጉዳይ ማጣፈጫ ተደርጎ በኬክ መልኩ የሚጋገረውን ምግብ ሠራች።

በሕይወት የተረፉት ኢያን ለችሎቱ እንደተናገሩት ምግቡ፤ ተፈጭቶ በቅቤ እና በክሬም የተለወሰደ ድንች (ማሽድ ፖቴቶ)፣ ፎሶሊያ በጎን ተደርጎ በግራጫማ ሰሐን ሆኖ ለአራቱ ሲቀርብ፤ ለራሷ ግን ምግቡ የቀረበው ብርቱካናማ ቀለም ባለው ሰሐን ነበር።

ኤሪን ድንገት ባለቤቷ ሃሳቡን ቢቀይር በሚል ለእሱም በግራጫማ ሰሐን ምግብ አቅርባ የነበረ ሲሆን፣ በኋላም ፍሪጅ ውስጥ አስገብታዋለች።

መጀመሪያ ላይ ባለቤቷን ለመግደል አቅዳ ነበር በሚል ተወንጅላ የነበረ ቢሆንም በክሱ ሳይካተት ቀርቷል።

ኤሪን ካንሰር እንዳለባት ተናግራ እንግዷቿን ከማስደንገጧ በፊት ምሳው በሳቅ እና በጨዋታ የተሞላ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።

አማቾቿም ለልጆቿ እንዴት ይህንን አስደንጋጭ ዜና መንገር እንዳለባት ምክር ለገሷት።

ከዚያም ምሳው እንደ ጅማሮው በጸሎት ተጠናቀቀ።

ነገር ግን በዚያች ምሽት እንግዶቹ በሙሉ ታመሙ።

ሕመሙም ጠንቶባቸው በማግስቱ አራቱም ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ። ዶናልድ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 30 ጊዜ እንዳስመለሳቸው ለዶክተሩ ተናገሩ።

ጥርጣሬዎችም ወዲያውኑ ነው መሰማት የጀመሩት።

ባልየው ሲሞን ሚስቱ እንዲህ ዓይነት ምሳ አዘጋጅታ መጥራት ለእሷ ያልተለመደ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ኢያን እና ባለቤቱ ደግሞ በኤሪን ቤት ሲጋበዙ የመጀመሪያቸው ነው።

ለሌሎቹ በሙሉ ግራጫ ቀለም ባለው ሰሐን ምግቡን አቅርባ ለምን የእሷ በተለየ ቀለም ቀረበ በሚልም ሕይወታቸው ያለፈው ሄዘር ተገርመው እንደጠየቁም ተገልጿል።

ሊዮንጋታ በተሰኘው ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩት አማቶቿ ጋባዣቸው ኤሪን ታማለች ወይ የሚል ጥያቄ አቀረቡ።

እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ከቀናት በኋላም መርማሪዎች ተመሳሳይ ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ።

ኤሪንንም "እነሱን ያሳመማቸው ምን እንደሆነ እና አንቺስ ለምን አልታመምሽም? የሚለውን ለመረዳት እየሞከርን ነው" ሲሉ መርማሪዎች ጥያቄ ወረወሩላት።

የኤሪን ፓተርሰን መኖሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የኤሪን ፓተርሰን መኖሪያ ቤት

"ብዙ ኬክ በልቼ አስመለሰኝ"

ለችሎቱ ምስክርነቷን የሰጠችው ኤሪን እንግዶቿ ከሄዱ በኋላ ማዕድ ቤቱን ማጽዳቷን እና አማቶቿ ያመጡትን ኬክ መብላት እንደጀመረች ተናግራለች።

"መጀመሪያ ትንሸ ኬክ በላሁ፤ ከዚያም ማቆም ስላልቻልኩ ትንሽ፣ ትንሽ ስል ሳላውቀው ሁሉንም ኬክ ጨረስኩት። እናም ከፍተኛ ጥጋብ ተሰማኝ" ብላለች።

"ከዚያም ሽንት ቤት ሄጄ ሁሉንም አስመለስኩት እና ከዚያም ተሻለኝ" ስትል አክላለች።

ኤሪን ከምሳው ከሁለት ቀናት በኋላ አሞኛል ብላ ወደ ሆስፒታል ሄደች።

ልጆቼም የቀረውን ትራፊ በልተዋል ማለቷን ተከትሎ እሷም ሆነ ልጆቿ ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ የሕክምና ባለሙያ ቢጠይቃትም መጀመሪያ አልተቀበለችውም ነበር።

ሌሎች እንግዶች ምግቡን ተመግበው በጠና መታማቸውን ያየ አንድ "የተገረመ" ዶክተር ለእሷ እና ለልጆቿ ደኅንነት በማሰብ ፖሊስ እንዲረዳው ደወለ።

ሆኖም የጤና ባለሙያዎች እሷንም ሆነ ልጆቿን ሲመረምሩ አማቶቿ ይታይባቸው የነበሩት ዓይነት ምልክቶች እንደሌላቸው እና የዴዝ ካፕ እንጉዳይ መመረዝ እንዳላጋጠማቸው ተረዱ።

ለ24 ሰዓታት ያህል ለጥንቃቄ በሆስፒታል ካቆዩዋት በኋላ ኤሪን ወደ ቤቷ ተመለሰች።

መረጃዎችን ማጥፋት

አማቶቿ ሕመማቸው መጥናት ጀመረ። የማያቋርጥ ተቅማጥ፣ እና ትውከትም አገርሽቶ የሰውነት አካሎቻቸው መሥራት ተሳናቸው።

አማቶቿ በሕይወት እና በሞት መካከል በሚያጣጥሩበት ወቅት ኤሪን መረጃዎችን ለመሸፈን ሙከራዎችን እያደረገች እንደነበር ዐቃቤ ሕግ አሳውቋል።

ከሆስፒታል ከወጣች ከአንድ ቀን በኋላ ኤሪን ወደ አንድ የቆሻሻ መጣያ በመሄድ የምግብ ማድረቂያ መሳሪያ ስትጥል የደኅንነት ቪዲዮ አሳይቷል።

በኋላ ላይ የምግብ ማድረቂያው ገዳይ እንጉዳዮች ይዞ እንደነበር መረጃዎች ተገኝተዋል።

ምሳውን ባዘጋጀችበት በዚያን ወቅት ኤሪን ሦስት ስልኮችን ትጠቀም እንደነበር እና ወዲያውኑ ሁለቱ ደብዛቸው መጥፋቱ ተገልጿል።

ለፖሊስ ምርመራ ያስረከበችው ስልክ ባዶ እና ምንም መረጃ የሌለው ነበር።

እንጉዳዩን የት እንደገዛችው ኤሪን ጥያቄ ሲቀርብላት ሜልቦርን በሚገኝ በአንድ የእስያውን መገበያያ መደብር እንደሆነ እና ሰፈሩንም እንደማታስታውሰው ገልጻለች።

የእንጉዳዩ የምርት ስም ወይም ደረሰኝ እንዳላት ስትጠየቅም ምርቱ የታሸገበት ምንም ጽሁፍ እንደሌለው እና በጥሬ ገንዘብ እንደከፈለች ተናግራለች።

ነገር ግን መርማሪዎች ከምሳው በፊት በነበረው ሳምንት ዴዝ ካፕ እንጉዳይ በአቅራቢያዋ ባሉ ሁለት ከተሞች በድረ-ገጽ የሚሸጡ ሰዎች ፎቶዎችን ለጥፈው እንደነበር ተረዱ።

የኤሪን የኢንተርኔት ታሪክም ቢያንስ አንድ ጊዜ አንደኛውን ድረገጽ መቃኘቷን አሳይቷል። የተንቀሳቃሽ ስልኳ ሁለቱንም ስፍራዎች መጎብኘቷ እንዲሁም በዚህ ጉዞዋ የምግብ ማድረቂያ መሸመቷን የቦታ መረጃ አሳየ።

ግለሰቧ የምግብ ማድረቂያ መሳሪያ የለኝም ብትልም የአጠቃቀም መመሪያው በማዕድ ቤቷ መሳቢያ ውስጥ ተገኝቷል።

በተጨማሪም በአንድ የፌስቡክ ገጽ ላይ መሳሪያውን እንደምትጠቀምበት በኩራት ለጥፋ ነበር።

የዲጂታል መርማሪዎች ስልኳ ላይ ባደረጉት ፍተሻ 'ዴዝ ካፕ' የሚመስል እንጉዳይ ስትመዝን የሚያሳይ ፎቶ አግኝተዋል።

ኤሪን በችሎቱ ላይ የምሳ ግብዣውን ካደረገች ከቀናት በኋላ ምግቡ ሳታውቀው በድንገት ይህንኑ የደረቀ እንጉዳይ ይዞ እንደነበርና ይህም ከመደብር ከገዛችው እንጉዳይ ጋር ተቀላቅሎባት በስህተት መጠቀሟን አስታውቃለች።

ነገር ግን በመፍራቷ ለማንም አለመናገሯን ገልጻለች።

የኤሪን ባለቤት ሲሞን ፒተርሰን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የኤሪን ባለቤት ሲሞን ፒተርሰን

ኤሪን አማቶቿን ለምን መረዘች?

ሲሞን ለፍርድ ቤት እንደተናገረው ባልና ሚስቱ በአውሮፓውያኑ 2015 ከተለያዩ በኋላ ግንኙነታቸው መልካም ነበር ብሏል።

ሆኖም ባልና ሚስቱ በገንዘብ፣ በልጆች ድጋፍ፣ በትምህርት ቤት እና በንብረት ላይ አለመግባባት በመፈጠሩ ሁኔታዎች በአውሮፓውያኑ 2022 ተቀይሯል ብሏል።

ሆኖም ይህንን የእነሱን አለመግባባት ለቤተሰቦቹ መጥፎ ከመመኘት ጋር አይያያዝም ብሏል።

"ከአባቴ ጋር በተለየ መልኩ ነበር የሚግባቡት። ሁለቱም ለዕውቀት እና ለትምህርት ፍቅር ነበራቸው" ይላል።

ሲሞን በሚንቀጠጥ ድምጽ ባለቤቱ "የአባቴን ለስላሳ ባህርይ ትወደው ነበር" የሚል ምስክርነት ሰጥቷል።

ሆኖም ኤሪን በሰጠችው ምስክርነት ከቤተሰቡ የመነጠል ስሜት ይሰማት እንደነበር እና ቤተሰቡም ትንሽ ያበሳጩዋት እንደነበር አምናለች።

ኤሪን በፌስቡክ ሲሞንን "የማትረባ፤ ሰነፍ" የሚል እና ቤተሰቦቹንም "ተስፋ የለሽ" በሚል የስድብ መልዕክት እንደጻፈችለት ዐቃቤ ሕግ በችሎቱ ላይ አንብቧል።

የኤሪን ጠበቆች በበኩሉ የላከችው መልዕክት "ጉዳት የሌለው መለፍለፍ" ነው ብለዋል።

ሆኖም ዐቃቤ ሕግ ለግድያው ምክንያት አላቀረበም።

የኤሪን ጠበቆች በበኩላቸው "እንደ ቤተሰቦቼ የምወዳቸው የምትላቸውን አማቶቿን ለመግደል ምን ምክንያት አላት?" ሲሉ ምንም ግልጽ የሆነ ምክንያት የለም ሲሉ ተከራክረዋል።

"ወላጆቼ በሕይወት የሉም። አያቶቼ ጭምር፤ እነሱ ብቻ ናቸው ያሉኝ ቤተሰቦች። በጣም ነው የምወዳቸው" ስትል ኤሪን ለፖሊስ ተናግራ ነበር።

በተጨማሪም ካንሰር ታምሜያለሁ ያለችው ክብደት ለመቀነስ ቀዶ ሕክምና የማድረግ ዕቅዷ ስላሳፈራት ያቀረበችው ሽፋን ነው ብለዋል ጠበቆቿ።

ጠበቆቿ የተንቀሳቃሽ ስልክ መከታተያ ትክክለኛ ቦታን የማያሳይ እንዲሁም ገዳዮቹ እንጉዳዮች ያሉበትን ከተማ ስለመጎብኘቷ መረጃ የለም ሲሉ ተከራክረዋል።

ኤሪን ምግቡን ከበላች በኋላ እንደሌሎቹ ባይሆንም ታማ እንደነበር እና ስላስመለሳትም አልጠናባትም ብለዋል።

መረጃዎቹን ለማጥፋት ሙከራዎች ማድረጓን እና መዋሸቷንም በተመለከተ በአደጋ የሞቱት እንግዶቿ እሷ ገድላዋለች በሚል እንዳትወቀስ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ መረጃዎችን "ሆን ብሎ በመቀጣጠል፣ ከትርክቱ ጋር ስለማይገጥም አማራጭ ማብራሪያዎችን ሆን ብሎ በመተው ግለሰቧን ጥፋተኛ አድርጓታል" ሲሉ ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ኤሪን በርካታ ውሸት ተናግራለች ብሏል።

ኤሪን ፓተርሰን በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለች ሲሆን፣ የዕድሜ ልክ እስራት በቅርቡ እንደሚወሰንባት ይጠበቃል።