ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነርነት የሥራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ተሰናበቱ

የሥራ ጊዜያቸው ያበቃው ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነርነት ተሰናበቱ።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ባለፉት አምስት ዓመታት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሸነር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሥራ ዘመናቸው ያበቃውን ዋና ኮሚሽነር ያሰናበቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ መሆናቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ለሚመራው ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ በዕጩነት ቀርበው ሰኔ 2011 ዓ.ም. ነበር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ መልኩ በዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የአመራርነት ዘመን የዜጎች መብት እንዲከበር በተደጋጋሚ ከመጠየቁ ባሻገር ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በዶ/ር ዳንኤል አመራርነት ዘመን ተሻሽሏል።

የተሻሻለው አዋጅ ኮሚሽኑ ያለ ቅድመ ማስታወቂያ በአገሪቱ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ስር የሚገኙ ሰዎችን ያሉበትን ሰፍራ እንዲሁም እንደ በትምህርት ቤት እና መጠለያ ጣቢያ ያሉ የሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን እንዲጎበኝ መብት የሚሰጥ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የተሻሻለው አዋጅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በምርጫ ወቅት ለሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ኮሚሽኑ ክትትል እንዲያደርግ ይፈቅዳል።

ኮሚሽኑ እንደገና ተዋቅሮ በዶ/ር ዳንኤል አመራር ሥር በቆየባቸው ዓመታት በመላው አገሪቱ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚመለከቱ ተከታታይ ዝርዝር ምርምራዎችን በማድረግ ሪፖርቶችን ሲያዋታ ቆይቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተቋም ጋር በመሆን ምርመራ አድርጎ ሰፊ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወቃል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኢሰመኮ ኮሚሽነር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2016 የተቋሙ የአፍሪካ ክንፍ ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። በተጨማሪም ኦክስፋምን፣ አርቲክል 19ን፣ የዓለም ባንክን እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦን (ዩኤስኤድ) አማክረዋል።

በበርካታ የሲቪል ማኅበራት ውስጥ የሠሩት ዳንኤል፤ የ1997ቱ ምርጫ ነጻ እንዲሆን እንዲሁም ሰብአዊ መብት እንዳይጣስ ያላሰለሰ ጥረት አድርገው የነበረ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለእስር ተዳርገው ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2009 ላይ 'አሊሰን ደስ ፎርጅስ አዋርድ ፎር ኤክስትራኦርዲነሪ አክቲቪዝም' የተሰኘ ሽልማት አግኝተዋል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እኤአ በ2021 ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ላበረከቱት የሕይወት ዘመን አስተዋፅኦ የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን (ዲኤኤስ) ተሸላሚም ነበሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሪጅናል ዴቨሎፕመንት ስተዲስ አግኝተዋል።

በተጨማሪም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በሌጋል ስተዲስ ሁለተኛ ዲግሪ የያዙ ሲሆን፤ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርት ወስደዋል።