የጆ ባይደን አስተዳደር ሕንዳዊ-አሜሪካዊው የዓለም ባንክን እንዲመሩ አጨ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይድን ሕንዳዊ አሜሪካዊው የንግድ ሥራ አስፈጻሚ አጃይ ባንጋስ የዓለም ባንክን እንዲመሩ እጩ አድርገው አቀረቡ።
ይህ ዜና የተሰማው ዓለም ባንክ የአየር ንብርት ለውጥን ለመከላከል የሚሰጠውን ትኩረት እንዲጨምር አሜሪካ የምታሳድረውን ጫና በጨመረችበት ወቅት ነወ።
ባንጋስ ‘ማስተርካርድ’ የተባለውን ግዙፉን የፋይናንስ ተቋም ከ10 ዓመት በላይ የመሩ ሲሆን አሁን ላይ በግል ተቋም ውስጥ ይሰራሉ።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ባንጋስ በግሉ ዘርፍ ያካበቱት ልምድ የዓለም ባንክን ግቦች ለማሳካት ይረዳል ሲሉ ተናግርዋል።
የዓለም ባንክን ቀጣይ መሪ የመሾም ኃላፊነት የባንኩ ቦርድ ነው።
የዓለም ባንክ ለሶስት እጩዎችን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ማቀዱን ገልጸ በቀጣዩ ሰኔ አዲስ ኃላፊ እንደሚሾም ገልጾ ነበር። የዓለም ባንክ ሴት አመልካቾች ይበረታታሉም ብሎ ነበር።
እንደ አሜሪካ ሁሉ ሌሎች አገራት ጥቆማ ስለማቅረባቸው የተባለ ነገር ግን የለም።
ለአገራት በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያበድረውና አሜሪካ ትልቁን ድርሻ የምታበረክትበት የዓልም ባንክ በተለምዶ መሪው የሚመረጠው በአሜሪካ ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሃላፊ ጄንት ያለን የዓልም ባንክ ትክክለኛውን አጀንዳ ትኩረት እንዲያደርግ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሃላፊዋ ጨምረውም አሁን በአሜሪካ በኩል በእጩነተ የቀረቡት አጃይ ባንጋስ፤ በተለየ ሁኔታ ለውጥ ላይ የተካኑ ናቸው ያሉ ሲሆን በመንግሥት፤ በኩባንያዎችና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን በማስተሳስር የተዋጣላቸው ናቸው ብለዋል።
የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ባንጋ ስራቸውን የጀመሩት በተወለዱበትና አባታቸው ወታደራዊ መኮንን በነበሩበት ሕንድ ነው።
ባንጋ ከ‘ማስተርካርድ’ እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ከተለዩ በኃላ በአንድ የግል ተቋም ውስጥ እየሰሩ ይገኛሉ።
በግሉ ዘርፍ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማበረታታ ያለመና ከኋይት ሃውስ ጋር የሚሰራ መርሃግብር ላይ ተባባሪ ሊቀመንብር ናቸው።
ባንጋ የሚመረጡ ከሆነ አሁን በስራ ላይ ያሉትን በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታጩትን እና በሚቀጥለው ሰኔ ከኃላፊነት እለቃለሁ ያሉት ዴቪድ ማልፓስ ይተካሉ።
ማልፓስ ባንኩ ያለውን ሃብት የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል በማዋል በኩል የሚወስዱት እርምጃ አዝጋሚ ነው የሚል ትችት በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ይቀርብባቸዋል።












