ዜሌንስኪ ከአገር ክህደት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አባረሩ

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከአገር ክህደት ጋር የተያያዙ ጥሰቶችን በመጥቀስ የአገሪቱን የደኅንነት መሥሪያ ቤት (ኤስቢዩ) ኃላፊ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ከኃላፊነት አነሱ።

በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ከ60 የሚበልጡ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ የቀድሞ ባልደረቦች ከዩክሬን በተቃራኒ ከሞስኮ ጎን ተሰልፈዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

በሕግ አስከባሪ አካላት ላይ ከጠላት ጋር በመወገን እና ከአገር ክህደት ጋር በተያያዘ 651 ክሶች ተምስርተዋል ብለዋል- ፕሬዝዳንቱ።

ዕሁድ አመሻሽ ላይ ዜሌንስኪ በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ “እንዲህ ዓይነቱ የአገርን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች... [የሁለቱ ድርጅቶች] ኃላፊዎቹ ላይ በጣም አሳሳቢ ጥያቄዎችን ያስከትላሉ።"

ፕሬዝዳንቱ አክለውም "እነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ ትክክለኛ ምላሽ ያሻቸዋል” ብለዋል።

የዩክሬን ደኅንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ኃላፊዋ ኢቫን ባካኖቭ ከዜሌንስኪ ጋር ከልጅነት ጀምረው ጓደኛሞች ነበሩ። ኃላፊዋ ከሥራቸው እንዲሰናበቱ የተደረገው እአአ በ2014 ሩሲያ በኃይል በተቆጣጠረቻት ክራይሚያ የቢሮው ኃላፊ የሆኑት ግለሰብ መታሰራቸውን ተከትሎ ነው።

በዚህም ኦሌህ ኩሊንች በአገር ክህደት ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በተያያዘ ዜና ዩክሬን በፈጠረችው ወታደራዊ ጫና በርካታ ቁጥር ያላቸው የሩሲያ የጦር መርከቦች ከክራይሚያ ወደ ምሥራቅ ኖቮሮሲስክ ወደብ ተንቀሳቅሰዋል።

ውጤቱ የተገኘው ኪዬቭ ከምዕራባውያን አጋሮቿ ተጨማሪ የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ የሚሳኤሎችን ስለተቀበለች ነው ተብሏል።

አሁን የሩሲያ የፀጥታ ምክር ቤት ኃላፊ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ዩክሬን ክራይሚያን ልትወጋ ከወሰነች “የዓለም ፍጻሜ ይሆንባታል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።