ዩኬ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ስምምነት ላይ ደረሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ፣ ኬንያና እና ሶማሊያ ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ስምምነት ላይ ደረሰች።
ከሶስቱ አገራት ጋር የተፈጸመው ስምምነት በቀጣናውን ያለውን አለመረጋጋት ለመቅረፍ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።
በዚህም ስምምነት መሰረት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሶስቱ አገራት ሽብርተኝነት በመዋጋት ረገድ ፖሊሲዎችን እንዲያወጡ የሚረዳም 12.5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግም የዩኬ የደህንነት ሚኒስትር ቶም ቱገንድሃት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ፣ የኬንያ እና የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በድንበራቸው ላይ ያለውን የጋራ ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሲያገኙ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነም ተገልጿል።
በሶስቱ አገራት የሚገኙት እነዚህ የድንበር አካባቢዎች አብዛኛውን ጊዜ የተገለሉ እና ደህንነታቸውም ያልተጠበቀ በመሆኑም አገራቱ የሚገጥማቸውን ስጋቶች ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የዩኬ ደህንት ሚኒስትሩ በእነዚህ አካባቢዎችም የአልሻባብ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የሽብር ተግባር የሚፈጽሙት የሚያስተዳድሩ ባለስልጣናት ባለመኖራቸው ነው ብለው ያምናሉ።
የአልሻባብ ታጣቂዎች ባለፉት ወራት በቀጣናው ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ የቆዩ ሲሆን ቡድኑ አሁንም ስጋት እንደሆነ ተገልጿል።
ከዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚጠረጠሩ የሽብር ተግባራትን የአካባቢው ማህበረሰብ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሪፖርት እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው።












