ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስለላ እንደሆነ የተጠረጠረው የቻይና ፊኛ ወሳኝ ክፍሎች ውቅያኖስ ውስጥ መገኘታቸውን አሜሪካ ገለጸች
ለስለላ ተግባር የተለቀቀ እንደሆነ የተጠረጠረው የቻይና ፊኛን አሜሪካ መታ ከጣለች በኃላ የፊኛው አካል የሆነና መረጃ የሚያነፈንፍውን ክፍል (ሴንሰርን) በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ መገኘቱን የአሜሪካ ጦር ገልጿል።
የፊኛውን ቅሪቶች ሲያፈላልግ የነበረው ቡድን “ወሳኝ የሆኑ የፊኛውን ክፍሎች፣ ጠቃሚ ሴንሰሮችና የኤሌክትሮኒክስ ከፍሎች” የጦሩ ሰሜን ዕዝ አስታውቋል።
ቀደም ብሎ ወሳኝ የሆኑ ወታደራዊ አካባቢዎችን እየሰለለ እንደሆነ አሜሪካ የገለጸችውን ፊኛ ስብርባሪ ቁሶች በኤፍ ቢ አይ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።
በየካቲት ወር መግቢያ ላይ አሜሪካ አንድን በራሪ አካል መትታ ከጣለች በኃላ በተከታታይ ሌሎች ሶስት በራሪ ቁሶችን መትታ አውርዳለች።
“የበራሪው ቁስ ግዙፍ ክፍል” ትላንት ሰኞ በደቡብ ካራይሎና ባህር ዳርቻ አቅራቢያ መገኘቱን የአሜሪካ ጦር ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ከ9 እስከ 12 ሜትር የሚረዝም እና የፊኛው አካል የሆነ አንቴና ከተገኙት ቁሶች አንዱ እንደሆነ መገናኛ በዙሃን ዘግበዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በከፍተኛ የከፍታ መጠን የሚንሳፈፈው ፊኛ መነሻው ቻይና እንደሆና የስለላ ተግባር እንዳለው ብትገልጽም ቻይና ግን ይህንን አስተባብላለች።
እንደ ቻይና ገለጻ ፊኛው የአየር ሁኔታን የመከታተል ዓላማ ብቻ ያለው ነው።
ከመጀመሪያው ክስተት በኃላ የአሜሪካ ተዋጊ ጀቶች በአላስካ፣ በአሜሪካና ካናዳ ድምበር በሚገኘው ሁሮን ሃይቅና በካናዳ ዩኮን ግዛቶች ምንነታቸው በግልጽ ያልታወቀ በራሪ አካላተን መትተው ጥለዋል።
በሁሮን ሃይቅ በራሪ አካሉን መቶ ለመጣል አሜሪካ የተኮሰችው ሚሳኤል ኢላማውን ስቶ ባልታወቀ ቦታ ላይ መቃጠሉን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሆኖም በሁለተኛው ኢላማውን አግኝቶ በራሪውን አካል አውርዷል።
የተተኮሰው ሚሳኤል 400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ነው።
በዝግታ የሚጓዘው እና ከመጀመሪያው ፊኛ በመጠኑ ያነሰው ያልታወቀው በራሪ አካል ኢላማ ወስጥ ለመግባት አስቸጋሪ እንደሆነ የአሜሪካ ወታደሮች ገልጸዋል።
የዋይት ኋውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪሪቢይ ሶስቱ በራሪ አካላት ጉዳት በማያደርሱበት አከባቢ ተመተው መጣላቸውን ትላንት ገልጸዋል።
በመሬት ላይ ባሉ ሰዎች ላይ “ቀጥተኛ ስጋት ባይፈጥሩም ለደህንነታችን፣ ለብሄራዊ ጥቅማችን እና ለበረራ ደህንንት ሲባል” ወድመዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በደቡብ ካሊፎርኒያ ተመትቶ የተጣለው ፊኛ የሶስት አውቶብሶች መጠን እንዳለው ተገልጻል።
ሁለተኛው በራሪ አካልና በአላስካ ተመትቶ የተጣለው ሌላ በራሪ አካል የ “አነስተኛ መኪና” መጠን ያለው ነው ተብሏል።