"ዛቻዎች" በርትተውብኛል ያለችው ቻይና ወታደራዊ በጀቷን ከፍ አደረገች

የቻይና ጦር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ወታደራዊ በጀቷን በ7 በመቶ ከፍ ልታደርግ ነው።

ናሽናል ፒፕልስ ኮንግረስ የተሰኘው የቻይና ፓርላማ ነው ይህን ዕቅድ ይፋ ያደረገው።

የቤጂንግ ወታደራዊ የዓመት በጀት 225 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ከዚህ በአራት እጥፍት ይበልጣል።

ነገር ግን ወታደራዊ ትንታኔ ሰጪዎች ቻይና የጦር በጀቷን አሳንሳ ታቀርባለች ሲሉ ይወቅሳሉ።

ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬጊያንግ ለፓርላማው እንደተናገሩት “ከውጭ የሚመጡ ቻይናን ለመጨቆን የሚደረጉ ሙከራዎች እየተበራከቱ ነው።”

“ጦር ሠራዊቱ መጠናከር አለበት። ሥልጠናም ይበልጥ መጠንከር አለበት። ሁሉም ዝግጁ ሊሆን ይገባል” ሲሉ አክለዋል።

የቻይና ናሽናል ፒፕልስ ኮንግረስ ፓርላማ ዢ ሺንፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ማረጋገጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከወታደራዊ በጀት አልፎ ቻይና በዚህኛው ዓመት ከቀደምቱ በተነፃፃሪ ዝቅ ያለ የ5 በመቶ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዳለች።

ዓመታዊ ጉባዔ በመባል የሚታወቀው የቻይና ፓርላማ ሁለት ክፍሎች አሉት።

በዚህኛው ዓመት የሚደረገውን ጉባዔ የሚለየው የገዢው ኮሚዩኒስት ፓርቲው ቅርፅ እንደአዲስ ሊጎበኝ መሆኑ ነው።

አልፎም በዚህ ጉባዔ ፕሬዝደንት ሺንፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ የሃገሪቱ መሪና የጦር ሠራዊቱ አዛዥ ሆነው ይሾማሉ።

ዢ ለሶስተኛ ጊዜ የተመረጡት ባለፈው ጥቅምት ፓርቲዎች በአብላጫ ድምፅ ለሳቸው ድጋፉን ከሰጠ በኋላ ነው።

በዩክሬን ምክንያት የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት በሻከረበት አልፎም አሜሪካ ሰማይ ላይ የታየችው በራሪ ፊኛ ተመትታ መውደቋን ተከትሎ ሁለቱ ሃገራት በተፋጠጡበት ወቅት ነው ቻይና ወታደራዊ በጀቷን ከፍ ያደረገችው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቻይና በሚቀጥሉት ዓመታት ታይዋንን ልትወር ትችላለች ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

ባለስቲክ ሚሳዔል መተኮስን ጨምሮ ቻይና በታይዋን ድንበር አካባቢ የሰማይና የየብስ ወታደራዊ ልምምዶች ታደርጋለች።

ቻይና፤ ራሷን በራሷ የምታስዳደረው ታይዋን ተገንጥላ የወጣች ክልል እና አንድ ቀን ወደ ቤጂንግ የምትመለስ ግዛት ናት ትላለች።

ፒፕልስ ኮንግረስ በጉባዔው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

በቻይና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና የምጣኔ ሃብትና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመረምር ሲሆን ከፕሬዝደንቱ ያነሳ ኃይል ነው ያለው።

የዢ የቅርብ ታማኝ ወዳጅ የሆኑት ሊ ኪያንግ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ናሽናል ፒፕልስ ኮንግረስ ወረቀት ላይ ትልቅ ሥልጣን ያለው ፓርላማ ተደርጎ ቢቆጠርም ቻይና ውስጥ የገዢውን ፓርቲ ውሳኔዎች ከማሳለፍ ያለፈ ሚና የለውም።