ቱርካዊው የክሪፕቶከረንሲ ተቋም ኃላፊ የ11,196 ዓመት እስራት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
ቱርካዊው የክሪፕቶከረንሲ ኃላፊ እና ሁለት የቤተሰቡ አባላት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማጭበርበር የ11,196 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።
ፋሩክ ፋታህ ኦዘር እአአ በ2021 ወደ አልባኒያ ሸሽቶ ነበር።
ቶዴክስ የተባለው ተቋሙ የኢንቨስተሮችን ገንዘብ ይዞ ሲንኮታኮት ነበር የሸሸው።
ባለፈው ሰኔ ከአልባኒያ ለቱርክ ተላልፎ ተሰጥቷል።
ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር በማስገባት፣ በማጭርበር እና በቡድን ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ግለሰቡ ለፍርድ ቤት “ግቤ ማጭበርበር ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት የልጅ ሥራ አልሠራም ነበር። ማንኛውንም ነገር ለመምራት የሚያስችል አቅም አለኝ። ይህንን ለማወቅ በ22 ዓመቴ የጀመርኩትን ድርጅት ማየት ትችላላችሁ” ማለቱን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል።
ኢስታንቡል በተካሄደው የፍርድ ሂደት እህቱ ሰሪፕ እና ወንድሙ ጉቬንም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
ተጠርጣሪዎች የተፈረደባቸው ለየብቻ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 2,027 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል።
በቱርክ በ2004 የሞት ቅጣት ከቀረ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዓመታት እስር መፍረድ የተለመደ ሆኗል።
አድናን ኦክታር የተባለው በቴሌቭዥን አክራሪ ቡድነኛነት ይሰብክ የነበረው ግለሰብ አምና በማጭበርበር እና በወሲብ ወንጀል 8,658 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።
ዐቃቤ ሕግ 40,562 ዓመት እንዲታሰር ነበር የጠየቀው።
ከሁለት ዓመታት በፊት የሊራ ዋጋ እየተዳከመ ሲሄድ ቱርካውያን ክሪፕቶከረንሲ መጠቀም ጀምረዋል።
ቶዴክስ የተቋቋመው በ2017 ሲሆን በአገሪቱ ዋነኛው ክሪፕቶከረንሲ መለዋወጫ ሆኖም ነበር።
የኢንቨስተሮች ገንዘብ በ2021 ድንገት ሲጠፋ ኃላፊው ተደብቋል።
አልባንያ ውስጥ ታስሮ በኢንተርፖል አማካይነት ወደ ቱርክ ተወስዷል።
ግለሰቡ የሸሸው 2 ቢሊዮን ዶላር ይዞ ነው ተብሎ የተዘገበ ቢሆንም ዐቃቤ ሕግ በቶዴክስ ምክንያት ኢንቨስተሮች ያጡት ገንዘብ 356 ሚሊዮን ሊራ ይጠጋል ብሏል።
በወቅቱ ገንዘቡ ወደ 43 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሲሆን አሁን ባለው የሊራ ገበያ ግን ገንዘቡ በዶላር 13 ሚሊዮን ይጠጋል።












