እነ አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, SM
“ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በትጥቅ ትግል ለመቀየር” በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩት አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ፣ የቴአትር አዘጋጅ ዳግማዊ ፈይሳ እና ፍላጎት አብርሃምን ጨምሮ 17 ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ፈቀደ።
በዚሁ መዝገብ ተጠርጥረው የቀረቡት ሌሎች ሶስት ግለሰቦች በአንጻሩ 11 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቅዶባቸዋል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ይህንን ብያኔ ያስተላለፈው ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 13/2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በነበረው የችሎት ውሎ ነው።
ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ዕለት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ግራ ቀኙ ያቀረቧቸው ጥያቄዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር።
በማክሰኞ ዕለቱ የችሎት ውሎ መርማሪ ፖሊስ ሀያዎቹ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ሲጠይቅ ጠበቆች በአንጻሩ የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀው እንደነበር ጠበቃ አያሌው ቢታኔ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት እነ አርቲስት አማኑኤል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ “አሸባሪ መረጃዎችን በማጋራት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚያውክ ተግባር ፈጽመዋል” በሚል እንደተጠረጠሩ ፍርድ ቤት አስታውቆ ነበር።
በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ ተጠርጣሪዎቹ፤ “ገንዘብ ለሽብር ቡድኑ ሎጅስቲክስ መግዣ ለማዋል ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል፣ በትጥቅ ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ” እንደተገኙም የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ ከጠየቀው 14 የምርመራ ቀን ውስጥ 13 ቀን ተፈቅዶለት ነበር።
መርማሪ ፖሊስ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ማክሰኞ በነበረው የችሎት ውሎ ላይ ነበር።
በእነዚህ ቀናት ውስጥ የአራት ተጠርጣሪዎች የኤሌክትሮኒክስ ምርመራ ውጤትን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
መርማሪ ፖሊስ፤ “በዚህም የመጣው ውጤት ተጠርጣሪዎች ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የፀረ ሠላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለመሆኑ መረዳት ተችሏል” ሲል በዕለቱ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ገልጿል። ይሁንና አሁንም ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመጥቀስ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት የጠየቁት ጠበቆች በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ “ሰፊ ክርክር” ማድረጋቸውን ጠበቃ አያሌው ተናግረዋል።
እንደ ጠበቃው ገለጻ የዋስትና መብት እንዲፈቀድ የቀረበው ዋነኛ መከራከሪያ “የቀረቡት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች፤ ፖሊስ እነዚህን ተጠርጣሪዎች ይዞ በማቆየት መመርመር የማያስችለው ነው” የሚል ነው።
ተጨማሪ ምርመራ ይደረግባቸው የተባሉት እንደ ኤሌክትሮኒክ ያሉ ማስረጃዎች “መንግሥት እጅ ላይ ያሉ” በመሆናቸው ተጠርጣሪዎች “ምስክሮችን የሚያባብሉበት ወይም መረጃ የሚያጠፉበት” መንገድ የለም የሚል ክርክር ከጠበቆች በኩል መቅረቡን አቶ አያሌው አስረድተዋል።
በተጨማሪም ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሁከት እና ብጥብጥ ማስነሳት በመሆኑ “የዋስትና መብት እንደማያስከለክል” ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ጅምር የምርመራ መዝገብ ተቀብሎ እንዲመለከት በጠበቆች መጠየቁን አቶ አያሌው ተናግረዋል።
ጠበቃው እንደሚያስረዱት ፍርድ ቤት መዝገቡን እንዲመለከት የተፈለገው ፖሊስ እስካሁን ባደረገው ምርመራ “ማን ላይ ምን ተገኝቷል?” ጉዳዩ “የሚያስከስስ ነው ወይ?” እንዲሁም “ፖሊስ በትክክል በሚገልጸው ልክ ስራውን እየሰራ ነው ወይ?” የሚሉትን ለማረጋገጥ ነው።
የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ችሎቱ፤ የመርማሪ ፖሊስን ጅምር የምርመራ መዝገብ እንደተቀበለ እና መዝገቡን ተመልክቶ በሁለቱ አካላት ጥያቄዎች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ እንደቀጠረ ጠበቃው አስታውሰዋል።
ዛሬ በጉዳዩ ላይ ብያኔ ለመስጠት የተሰየመው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ በመዝገቡ ከተካተቱት 20 ተጠርጣሪዎች ውስጥ አስራ ሰባቱ እያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ያሬድ ገብረፃዲቅ (በማኅበራዊ ሚዲያ ስሙ ያያ ዘልደታ)፣ ፍስሃ እያዩ እና ጌትነት ታከለ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ግን 11 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንደተፈቀደባቸው ጠበቃ አያሌው ገልጸዋል።
ጠበቃው እንደገለጹት፤ ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ከሌሎቹ ተለይተው የምርመራ ጊዜ የተፈቀደባቸው “ወንጀል ፈጽመዋል ሊያስብል የሚያስችል ነገር አለ” በሚል ነው።
በገንዘብ ዋስትና እንዲወጡ የተፈቀደላቸውን የእነ አርቲስት አማኑኤልን ክፍያ ለመፈጸም ሂደት መጀመሩን የተናገሩት ጠበቃው፤ በዛሬው ዕለት ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።












