የዓለም ሕዝብ ቁጥር 8 ቢሊዮን ደርሷል የሚባለው ምን ያህል እውነት ነው?

ስምንት ጣቶቹን የሚያሳይ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር ከስምንት ቢሊዮን በላይ ተሻግሯል

የዓለማችን የሕዝብ ቁጥር ከ8.2 ቢሊዮን ወደ 10.3 ቢሊዮን እንደሚያድግ የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ ያሳያል።

በየዓመቱ ሐምሌ 4 የሚዘከረው የዓለም የሥነ ሕዝብ ቀንን ተገን አድርጎ የሚወጣው ዘገባ እንደሚተነበየው የምንኖርባት ምድር ሕዝብ ቁጥር እስከ አውሮፓውያኑ 2080ዎቹ ድረስ ዕድገቱን ይቀጥልና ከዚያ በኋላ ግን እያሽቆለቆለ ይመጣል።

ዘገባው እንደሚያስቀምጠው ግምት ከሆነ ዛሬ የተወለዱ ሰዎች በአማካይ ለ73.3 ዓመታት የሚኖሩ ሲሆን፣ ይህም ከ1995 ጋር ሲነፃፀር በ8.4 ዓመታት ከፍ ያለ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ላለፉት 50 ዓመታት ከአባላት አገራት የሕዝብ ቆጠራ በሚያገኘው መረጃ መሠረት የዓለማችንን ሕዝብ ቁጥር በተመለከተ ዘገባ ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል።

አባል አገራት ከሕዝባቸው ቁጥር ባለፈ የውልደት እና ሞት መጠን እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ የሚሏቸውን መረጃዎች ለተባበሩት መንግሥታት ያቀርባሉ።

ታድያ እነዚህ ቁጥሮች የሚታመኑ ናቸው?

የግምት ሳይንስ

“ያለንበትን ፕላኔት ሕዝብ ቁጥር ስሌት መሥራት ማለት የግምት ሳይንስ ነው” ሲሉ የሥነ ሕዝብ ባለሙያው ጃኩብ ቢጃክ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የሳውዝአምፕተን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጃኩብ ከሥነ ሕዝብ ሙያቸው ውጪ የምጣኔ ሀብት ምሑርም ናቸው። የሕዝብ ቁጥር ግምት ሲካሄድ እርግጠኛ የሚኮንበት ነገር ትክክልኛ ቁጥሩን አለመታወቁ ነው ይላሉ።

ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ፖፑሌሽን ሪፈረንስ ቢሮ የጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ቶሺኮ ካኔዳ በበኩላቸው “ይህ ተብሎ የሚነገር ቁጥር የለም” ይላሉ።

ታድያ ይህ ማለት የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች የሕዝብ ቁጥርን ለመገመት እና ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመተንበይ ቁጥሮችን ከዚህም ከዚያም ይመዛሉ ማለት አይደለም።

“በጣም ማሰብ የሚጠይቅ፣ ልምዳችን እና ዕውቀታችን ላይ ተመሥርተን እንዲሁም እያንዳንዱን መረጃ ተጠቅመን ነው የምንሠራው። በጣም ከባድ ነው” ይላሉ ዶ/ር ካኔዳ።

የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች በየጊዜው ግምታቸውን ያሻሽላሉ። ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ከ10 ዓመታት በፊት ያስቀመውን ግምት ትቶ በአውሮፓውያኑ 2100 ስድስት በመቶ አነስ ያለ የሕዝብ ቁጥር ይኖራል ሲል በያዝነው ዓመት ግምቱን አውጥቷል።

የሕዝብ ቁጥር መረጃዎች ለመንግሥታት እና ለፖሊሲ አውጪዎች እጅግ ጠቃሚ ግብዓቶች ናቸው። እነዚህን ቁጥሮች መሠረት በማድረግ ስለሚመጣው ጊዜ ከአሁኑ ውሳኔ ማሳለፍ ይቻላል።

የተባበሩት መንግሥታት የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ምን ይላሉ?

የቅርብ ጊዜ መረጃዎች

የ2024 የሕዝብ ቁጥር ግምት እንደሚያሳየው “በዓለማችን ካሉ አራት ሰዎች አንዱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገታቸው ጫፍ ደርሶ እየቀነሰ ባለባቸው አገራት ውስጥ ነው የሚኖረው።”

ነገር ግን 126 አገራት እና አካባቢዎች በሚቀጥሉት ሦስት አስርት ዓመታት የሕዝብ ቁጥራቸው በተከታታይ እየጨመረ ይመጣል።

ከእነዚህ መካከል አሁንም በርካታ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው እንደ ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን እና ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙበታል።

በአዲሱ ዘገባ መሠረት አማካይ የዕድሜ ጣራ እየጨረመ መጥቷል። ይህ የሰዎች አማካይ የዕድሜ ጣራ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በመጠኑ ቀንሶ ነበር።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ የተወለዱ ሰዎች በአማካይ ለሚቀጥሉት 73.3 ዓመታት ሊኖሩ ይችላሉ። በ1995 የተወለዱ ሰዎች በአማካይ ይኖራሉ ከተባለው ዕድሜ ይህ ቁጥር በ8.4 ዕድሜ ከፍ ያለ ነው።

ዘገባው እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2054 አማካይ የዕድሜ ጣራ 77.4 ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ይገመታል።

ስደት እና የሕዝብ ቁጥር መጨመር

የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በየክፍለ ዓለማቱ የተለያየ ቅርፅ አለው። ለምሳሌ እንደ አንጎላ፣ ማዕከላዊት አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኒጀር እና ሶማሊያ ያሉ አገራት በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ፈጣን የሚባል የውልደት መጠን ያስተናግዳሉ። በዚህ ምክንያት የሕዝብ ቁጥራቸው እጥፍ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚለው በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ስደት ለሕዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት እየሆነ መጥቷል።

የሕዝብ ቁጥር ዕድገታቸው ጫፍ የደረሰው ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣልያን፣ ሩሲያ እና ታይላንድን ጨምሮ 19 አገራት ስደት ባይታከልበት ኖሮ የሕዝባቸው ቁጥራቸው ቀስ ብሎ ነው የሚያድገው።

ዘገባው እንሚጠቁመው ስደት “አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ዩናይትድ ስቴትስ በ2054 የሕዝብ ቁጥራቸው ጫፍ ላይ የሚደርሰው ስደት በፈጠረው የተረጋጋ ዕድገት ምክንያት ነው።”

“ስደት የዓለማችንን ሕዝብ አሰባጥሮ ለማስቀመጥ የሚጠቅም መላ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ቢጃክ “ነገር ግን በርካታ አገራት ስደተኞችን አይቆጥሩም፣ አሊያም ደግሞ በ10 ዓመት አንድ ጊዜ የሕዝብ ቁጥር ሲቆጠር ነው የሚካተቱት።”

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, “ስደት የዓለማችንን ሕዝብ አሰባጥሮ ለማስቀመጥ የሚጠቅም መላ ነው”

አንዳንድ አገራት ደግሞ በቀጥታ ሕዝባቸውን ከመቁጠር ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ይጠቀማሉ። “ለምሳሌ የሞባል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር። ነገር ግን ይህ ቁጥር እንደ ዋና መረጃ ለመውሰድ ገና ብዙ ይቀረዋል። ይህንን መረጃ የበለጠ መረዳት ይጠበቅብናል” ይላሉ።

ዶ/ር ካኔዳ እንደሚሉት የስደት ሂደትን መከታተል ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ከውልደት መጠን በላይ በፍጥነት የማደግ አዝማሚያ ይታይባቸዋል።

“በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ የሚባል የውልደት መጠን ያላቸው አገራት እንኳ ወደዜሮ አይወርዱም። ነገር ግን ስደት ነገሮችን በፍጥነት ሊቀይር የሚችል ነው። ለምሳሌ በጦርነት አሊያም በተፈጥሯዊ አደጋ ምክንያት በየሚከሰት ስደት።”

ቢሆንም ዓለም አቀፍ የሰዎች ስደት እንደ በጎ ጎን ብቻ ሊታይ አይገባም የሚሉት ደገሞ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ትንተና ዘርፍ ኃላፊ ክሌር ሜኖዚ ናቸው።

ስደት “ብቻውን የሕዝብ ቁጥር መመናመንን የሚታደግ ወይም ደግሞ እያረጀ ያለን ሕዝብ የሚያድስ ተደርጎ እንደ መፍትሔ መወሰድ የለበትም።”

የሕዝብ ቁጥር መረጃ አስፈላጊነት

የአንድ ሕዝብ ቁጥር ማጥናት እንዲሁም ውጤቱን ፖሊሲ ለማውጣት መጠቀም የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው።

የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች፤ የሕዝብ ቆጠራ ከክርስቶስ ልደት በፊት 4000 ዓመተ ዓለም ጀምሮ በባቢሎን ሥልጣኔ እና በሜሶፖታሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ እንደሆነ ያምናሉ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሕዝብ ቆጠራ ቴክኖሎጂ ብዙ ርቀት የተጓዘ ቢሆንም የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች ሥራ እየከበደ እንጂ እየቀለለ አልመጣም።

የሕዝብ ቆጠራ ለአገራት ዕቅድ እና ፖሊሲ የጎላ ጠቀሜታ አለውnaire with a pencil.

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሕዝብ ቆጠራ ለአገራት ዕቅድ እና ፖሊሲ የጎላ ጠቀሜታ አለው

ዶ/ር ካኔዳ እንደሚሉት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ በምጣኔ ሀብት ያደጉ አገራት ሳይቀሩ ለፍፁምነት የተቃረበ የሕዝብ ቁጥር መረጃ ለማግኘት ይቸገራሉ፤ ለዚህ ደግሞ አንደኛው ምክንያት “መንግሥት ላይ ያለ እምነት መመናመን እና ለግላዊ መረጃ ያለው አመለካከት ነው።”

የተባበሩት መንግሥታት “የሕዝብ ቁጥር መረጃን ለማዳበር የሚወጣ አንድ ዶላር ከምጣኔ ሀብት በሚገኝ ጥቅም ምክንያት 32 ዶላር ትርፍ ይኖረዋል” ይላል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚመክረው የሥነ ሕዝብ መረጃን በጥብቅ መሰብሰብ ያለበት ተጋላጭ በሚባሉ አካባቢዎች ነው።

“ለምሳሌ የመረጃ ጥራታቸው የደከመ በሚባሉ ቦታዎች ዕድሜያቸው ከ15 አስከ 19 የሚሆኑ እናቶችን የተመለከተ መረጃ የለም፤ እነዚህ ቦታዎች ደግሞ የውልደት መጠናቸው ከፍ ያለ ነው።”

የተባበሩት መንግሥታት ይፋዊ የሕዝብ ቁጥር መረጃ እና ትንበያ ሲያወጣ ይህ ለ28ተኛ ጊዜ ነው። የአሁኑ ዘገባ የወጣው ከአውሮፓውያኑ 1950 እስከ 2023 ባሉት ጊዜያት የተሰበሰቡ 1700 የሕዝብ ቆጠራዎችን መሠረት አድርጎ ነው።