ከግብፅ የተነሳው እና ባለቤቱ ያልታወቀው 5 ሚሊዮን ዶላር የጫነው የግል አውሮፕላን

ወርቅና ዶላር

በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ጭኖ የተገኘው የግል አውሮፕላን አነጋጋሪ ሆኗል።

አውሮፕላኑ ከገንዘቡ በተጨማሪ ሐሰተኛ ወርቅ እና የጦር መሣሪያም ጭኗል።

የተነሳው ከግብፅ መዲና ካይሮ ነው። እስካሁን ድረስ በግብፅም ይሁን በዛምቢያ ማንም ሰው አውሮፕላኑ ላይ የተጫነው ንብረት የእኔ ነው አላለም። በጉዳዩ ላይ ምርመራ ተከፍቷል።

መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። መላ ምቶችም እንደዚሁ።

በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው ያለበት ምናልባት የግብፅ ወይም የዛምቢያ የፖለቲካ አልያም ወታደራዊ አመራሮች ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ አሉ።

አውሮፕላኑ በረራ ሲያደርግ የመጀመሪያው ይሆን? ወይስ በርካታ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ተመሳሳይ ጉዞ አድርገው በስተመጨረሻ የተያዘው ይህ አውሮፕላን ይሆን?

አውሮፕላኑ ውስጥ የተገኙት ስድስት ግብፃውያን እና በሉሳካ የተቀበሏቸው ግለሰቦች ከሰሞኑ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ከተያዙት ዛምቢያውያን የተወሰኑት በስለላ እንዲሁም በማጭበርበር ገንዘብ በማግኘት ተከሰዋል።

ጉዳዩ ይፋ የወጣው በጋዜጠኞች ምርመራ ነው። ‘Matsda2sh’ የተባለ ድረ ገጽ ግብፃውያን እጃቸው እንዳለበት ይገልጻል።

መረጃው እንደወጣ በግብፅ ካይሮ የሚገኘው ጋዜጠኛ ካሪም አሳድ ቤቱ በሌሊት ይፈተሽና ይታሰራል።

መጀመሪያ ላይ ያለበትን ያወቀ አልነበረም። የግብፅ ጋዜጠኞች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በዛምቢያ ፖሊስ ስለተያዘው አውሮፕላን መረጃ ማውጣት ጀመሩ።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት የግብፅ ወታደራዊ አመራር የሆኑ ሦስት ሰዎች እና አንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለሥልጣን መሆናቸው ተገለጸ።

ካሪም አሳድ ከመያዙ በፊት በድረ ገጹ ይፋ ያደረገው መረጃም ይሄው ነበር።

ጋዜጠኞች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ካሪም ከእስር ተለቀቀ።

የግብፅ መንግሥት እስካሁን ይፋ ያደረገው ጋዜጠኛው ድረ ገጽ ላይ የጻፈው አውሮፕላን የግል እንደሆነ እና በካይሮ በኩል እንዳለፈ ብቻ ነው።

ግብፅም ይሁን አመራሮቿ ከጉዳዩ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለም አክሏል።

ጉዳዩ ከዛምቢያም ጋር ሊገናኝ ይችላል። ወርቁን በሻንጣ ይዞ ይጓዝ የነበረው ዛምቢያዊ የፀጥታ ቁጥጥር ክፍልን ለማለፍ አልተቸገረም። በአውሮፕላኑ ዛምቢያ፣ ሉሳካ ከገቡ ግብፃውያን ጋርም ተገናኝቷል።

ይህ እንዲሆን ማን እንደፈቀደ አይታወቅም።

የዛምቢያ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት ግን ጉቦ በመስጠት ነው ሁሉም ነገር የተከናወነው።

ወርቅ በሻንጣ ይዞ የነበረው ግለሰብ አውሮፕላኑ ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ከወርቁ ግማሹን ሸጧል። የቀረውን ወርቅም እንዲሸጥ ተጠይቋል።

እየሸጠ የነበረው ወርቅ ሐሰተኛ መሆኑን ገዢዎቹ ይወቁ አይወቁ ግልጽ አይደለም።

የደኅንነት ሰዎች በቦታው ደርሰው አውሮፕላኑን ፈትሸዋል። ሰዎቹን ያሰሯቸው ግን ወዲያውኑ አልነበረም።

አውሮፕላኑን የፈተሹት ደኅንነቶች አውሮፕላኑ ውስጥ በነበሩ ግብፃውያን 200 ሺህ ዶላር እንደተሰጣቸው ስለተጠረጠረ ምርመራ ተከፍቷል።

ማንንም ሳያስሩ አውሮፕላኑ እንዲጓዝ እንዲፈቅዱ ነው ጉቦው የተሰጣቸው።

ስለ ጉዳዩ እንደተሰማ ግን ሌሎች ደኅንነቶች ወደ አውሮፕላኑ አቅንተው በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው።

ተጠርጣሪዎቹ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ የጦር መሣሪያ እና ወደ 100 ኪሎ ግራም የሚሆን ሐሰተኛ ወርቅ ይዘው ለምን አውሮፕላን ውስጥ እንደተገኙ ማብራራት አልቻሉም።

ሐሰተኛ ወርቁ የተሠራው ከኮፐር፣ ኒኬል፣ ቲን እና ዚንክ ከተባሉ ንጥረ ነገሮች ነው።

የተያዙበት አውሮፕላን ማረፊያ
የምስሉ መግለጫ, ተጠርጣሪዎቹ የተያዙበት አውሮፕላን ማረፊያ

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 10 ሰዎች የአንደኛው ጠበቃ ዛምቢያዊው ማኬቢ ዙሉ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ መጀመሪያ ላይ በአውሮፕላኑ ውስጥ የተያዘው ገንዘብ 11 ሚሊዮን ዶላር ተብሎ ነበር የተመዘገበው። ኋላ ላይ ደግሞ 7 ሚሊዮን ዶላር ነው ተባለ። በስተመጨረሻ 5.7 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ተገለጸ።

ግለሰቦቹ ከመያዛቸው በፊት ከአውሮፕላኑ የወጣ ገንዘብ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል።

የተያዙት ዛምቢያውያን እና የሌላ አገር ሰዎች የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው እስከሚደርስ በእስር ቤት እንዲቆዩ ሲደረግ ስድስቱ ግብፃውያን ግን ሆቴል እንዲቆዩ ለምን እንደተወሰነ ጠበቃው ግልጽ አልሆነላቸውም።

ሐሰተኛውን ወርቅ አውሮፕላኑ ውስጥ ለሽያጭ ያቀረበው ግለሰብ ከመጀመሪያው ከዛምቢያ ፖሊስ ጋር ተባብሮ በመሥራት መረጃ ሲያቀብል ነበር ተብሏል።

ከዚህ ክስተት በኋላ ሐሰተኛ ወርቅ በመሥራት የተጠረጠሩ በርካታ ዛምቢያውያን ታስረዋል።

‘ኢጂፕት ቴክኖክራትስ’ የተባለ ቲንክ ታንክ እንደሚለው፣ ከ300 በላይ ግብፅ የሚገኙ ምሥጢራዊ ድርጅቶች ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር የማስገባት ሥራ ይሠራሉ።

ፕሬዝዳት አብደል ፈታህ አልሲሲ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከአገሪቱ እየወጣ እንደሆነ የሚገልጹም አሉ።

ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች እና ነጋዴዎች የአልሲሲ አስተዳደር እንደሚፈረካከስ በመፍራት ገንዘብ እያሸሹ እንደሆነ ይገመታል።

በዛምቢያ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹ ሲቀርቡ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ምናልባት እነዚህ መረጃዎች ነገሩን ከማጥራት ይልቅ ወደ ተጨማሪ ጥያቄዎች ያመሩም ይሆናል።