ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን፣ የኢራንና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸውን እስረኞች ወደ ቁም እስር ማዛወሯ ተገለጸ
ኢራን በማረሚያ ቤት እስር ላይ የነበሩ የአሜሪካ እና የኢራን ጥምር ዜግነት ያላቸውን አምስት እስረኞችን ወደ ቁም ውስጥ እስር ማዛወሯን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ሲያማክ ናማዚ፣ ኢማድ ሻርጊ እና ተጨማሪ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ሞራድ ታህባዝ የተባሉት ግለሰቦች አንድ ስሙ ካልተገለጸ አራተኛ ግለሰብ ጋር ከእስር ቤት መለቀቃቸውን የአንደኛው ግለሰብ ጠበቃ ተናግረዋል።
አምስተኛው አሜሪካዊ ቀደም ብሎ መለቀቁን የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ባለሥልጣን ገልጸዋል።
ግለሰቦቹን ለማስለቀቅ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ንግግር ሲደረግ ነበር።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አድሬን ዋትሰን “ይህ የሚያበረታታ የመጀመሪያው እርምጃ ቢሆንም በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ግለሰቦች መታሰር አልነበረባቸውም። ሁሉም ወደ አሜሪካ እስከሚመለሱ ድረስ እረፍት አይኖረንም” ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ተልዕኮ፣ ጥምር ዜግነት ያላቸው ዜጎች ከቴህራን ኢቪን እስር ቤት መለቀቃቸውን እንዳረጋገጠ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ሮይተርስ የመንግሥት የዜና ወኪል የሆነውን ኢርናን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ስምምነቱ በሦስተኛ አገር አሸማጋይነት የተፈፀመ ሲሆን በስምምነቱ መሰረትም በደቡብ ኮሪያ እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ የነበረው ገንዘብ እንዲለቀቅ እና ወደ ኳታር እንዲላክ ከስምምነት ተደርሷል።
በደቡብ ኮሪያ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው የኢራን ገንዘብ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከእስር ከተለቀቁት ግለሰቦች አንዱ የሆነው ናማዚ ወንድም ባባክ “ ይህ አዎንታዊ ለውጥ ቢሆንም፤ ናማዚ እና ሌሎች ወደ ቤታቸው እስከሚገቡ አናርፍም። ይህ እውን የሚሆንበትን ቀን መቁጠራችንን እንቀጥላለን” ብሏል።
የ51 ዓመቱ ናማዚ መጀመሪያ የታሰረው እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ሲሆን ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ክስ 10 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተፈርዶበት ነበር።
የ58 ዓመቱ ሻርጊ እህት በበኩሏ፣ ሻርጊ በአውሮፓውያኑ 2018 ሚያዝያ ወር ላይ ከታሰረ በኋላ ከእስር እንዲለቀቅ በፕሬዝደንት ባይደን እና በመንግሥት ባለሥልጣናት ሥራ እምነት እንዳላት ተናግራለች።
የ67 ዓመቱ የንግድ ሰው እና የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ታህባዝ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ሥር የዋለው ጥር 2018 ላይ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ነበር።
ኢራን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአብዛኛው ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ክስ ጥምር ዜግነት ያላቸውን በርካታ ዜጎችን አስራለች።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቴው ሚለር እንዳሉት ከእስር ከተለቀቁት አምስት ግለሰቦች ሁለቱ ማንነታቸው እንዳይገለጽ ፈልገዋል።
“በአሜሪካ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር እየተነጋገርን ነው። የእነዚህን ግለሰቦች ጤና እና ደኅንነት በቅርበት እየተከታተልን ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ግለሰቦቹን ከእስር ለማስፈታት ለዓመታት ድርድር ሲካሄድ የቆየ ሲሆን እርምጃው በአሜሪካ እና በምዕራብ አገራት በእስር ላይ ሚገኙ ኢራናውያንን ጋር ከሚደረግ የእስረኛ ልውውጥ እንዲሁም አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለቸውን ማዕቀብ ለማላላት የተደረሰው ስምምነት አካል ነው ተብሏል።
ሆኖም አሁንም ቢሆን የአሜሪካ ዜጎች ኢራንን ለቀው ለመውጣት በርካታ ሳምንታትን ሊወስድባቸው እንደሚችል ሮይተርስ ድርድሩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ ምንጭን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኒው ዮርክ ታይምስ በአሜሪካ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ኢራናውያን እስረኞች በስምምነቱ መሰረት ሊለቀቁ እንደሚችሉ የዘገበ ሲሆን፣ ነገር ግን ዋይት ሃውስ እስረኞቹን ለማስለቀቅ ለቴህራን ስላቀረበው ነገር ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጠም።