በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ 15 ሰዎች ሞቱ

የኢቦላ ወረርሽኝ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Image

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአዲስ መልኩ በተከሰተው የኢቦላ ወረረሽኝ ምክንያት ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቫይረሱ መኖር የተረጋገጠው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ሆስፒታል በመጣች የ34 ዓመት ነፍሰ ጡር ሴት እንደነበር ሚኒስቴሩ አክሏል።

ግለሰቧ የኢቦላ ምልክቶች የሆኑት ከፍተኛ ትኩሳት እና ተደጋጋሚ ትውከት አጋጥሟት ነበር።

በርካታ የአካል ክፍሎቿ አገልግሎት መስጠታቸውን ተከትሎ ግለሰቧ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ህይወቷ አልፏል።

ለዘመናት በጦርነት በምትናወጠውና የጤና ስርዓቷ ደካማ በሆነው የማዕድን ሃብታሟ ኮንጎ ወረርሽኙ ሲከሰት ይህ ለ16ኛ ጊዜ ነው።

በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ወረርሽኝ በማዕከላዊ ካሳይ ግዛት ሲሆን 28 ተጠርጣሪዎች መመዝገባቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የጤና ባለስልጣናቱ እጅን በደንብ አድርጎ በተደጋሚ መታጠብን ጨምሮ ከፍተኛ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ርቀትን መጠበቅ እና ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎች እንዲከተሉ በጽኑ አሳሳስበዋል።

አሁን የተከሰተው ብዙም ያልተለመደውና ዛየር የተሰኘው የኢቦላ ዝርያ ሲሆን ገዳይ መሆኑንም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት "የቫይረሱን ስርጭት በፍጥነት ለመግታት እና ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እየሰራ" መሆኑን አስታውቋል።

ከሞቱት 15 ሰዎች መካከል አራቱ የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ተቋሙ አክሏል።

"ወረርሽኙ ከመዛመቱ ጋር ተያይዞ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል። ምላሽ ሰጪ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ የተያዙ እና ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። ይህም ለሁሉም ሰው በተቻለ ፍጥነት ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ነው" ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አክሎ ገልጿል።

ዲሞክራቲክ ሪፐሊክ ኮንጎ ከዚህ አይነት ኢቦላ ለመከላከል 2000 ኤርቬቦ የተሰኘ ክትባትን ጨምሮ ውጤታማ የሆነ የህክምና ክምችት እንዳላት ተቋሙ አክሏል።

በአገሪቷ ለመጨረሻ ጊዜ ከሶስት ዓመት በፊት የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ስድስት ሰዎችን ገድሏል።

የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው በአውሮፓውያኑ 2018-2020 የተከሰተው ሲሆን በዚህም 2000 የአገሪቱ ዜጎች ሞተዋል።

አመጣጡ ከሌሊት ወፎች እንደሆነ የሚገመተው ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በአውሮፓውያኑ 1976 ነበር።

የኢቦላ በሽታ በአካልና ደም ንክኪ፣ ከአፍ፣ ከአፍንጫ እንዲሁም ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች በሚወጡ ፈሳሾች ይተላለፋል።