ቻይናውያን የቤት እና የንግድ ተቋማት ባለቤት እንዳይሆኑ የሚገድበው የቴክሳስ ሕግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይና የተወለደው ጄሰን ዩዋን ቴክሳስን መኖሪያው ካደረገ ከራረመ።
የአሜሪካ ዜግነት ያለው ዩዋን ቴክሳስ ሕይወት የመሠረተባት ግዛት ናት።
ያገለገሉ መኪኖችን በመሸጥ እና በመለወጥ ኑሮውን ይመራል።
ቴክሳስ የመረጣት ግዛት እና ቤቱ ሆና ብትቆይም በቅርቡ የጸደቀ የግዛቲቱ ሕግ ግን መጪ ዕጣ ፈንታውን ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።
የቴክሳስ ምክር ቤት ሴኔት 'ቢል 17' ወይም ኤስ ቢ 17 የተሰኘ ሕግ አጽድቋል።
ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም. ተግባራዊ የሚሆነው ሕግ ከቻይና፣ ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ የመጡ ወይም የእነዚህ አገራት ኩባንያዎች የንብረት ግዢ እና ኪራይ ላይ ገደብን ጥሏል።
ባለሥልጣናቱ ይህ ሕግ የወጣበት ምክንያት ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
እንደ ዩዋን ላሉት ደግሞ አድሏዊ እና እሱን የሚመስሉ ሰዎች በቴክሳስ ተቀባይነት እንደሌላቸው መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።
"ሕጉ ፀረ ስደተኛ፣ ፀረ እስያውን በተለይም በቻይና አሜሪካውያን ላይ ያነጣጠረ ነው" ሲሉ በቴክሳስ የዲሞክራት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት እና ይህንን ሕግ የሚቃወሙት ጂን ዉ ይናገራሉ።
አዲሱ ሕግ በቴክሳስ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እንደሚጎዳም ነው ፖለቲከኛው ለቢቢሲ የተናገሩት።
ወደ ግዛቲቷ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ኢንቨስትመንት ሊያመጡ የሚችሉ ኩባንያዎች ዓይናቸውን ወደ ሌሎች አማራጮች እያማተሩ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Ning Li
ሕጉ ምን ይዟል?
በቴክሳስ ገዢ ግሬግ አቦት ሰኔ 13/2017 ዓ.ም. ተፈርሞ ሕግ የሆነው ኤስቢ 17 የውጭ አገራት "ተገዳዳሪዎችን" ለማራቅ አሜሪካ የጣለችው "ከበድ ያለ እገዳ" እንደሆነም አቦት ገልጸዋል።
ሕጉ ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ተብለው የተፈረጁ አገራት ዜጎች እና ድርጅቶች መኖሪያ ቤቶችን፣ የንግድ ተቋማት፣ እና የእርሻ መሬቶችን በቴክሳስ ግዛት ባለቤት እንዳይሆኑ ይከለክላል።
በተጨማሪም መከራየት የሚችሉትም ከአንድ ዓመት በታች ላነሰ ጊዜ እንዲሆን ገደብ ጥሏል።
በሕጉ ላይ የተጠቀሰችው የመጀመሪያ አገር ቻይና ናት።
ቤይጂንግ የተከሰሰችውም "አሜሪካን በምጣኔ ሃብት፣ በወታደራዊ እና በፖለቲካዊ መስክ ለመቅደም በምታደርገው ጥረት አፍራሽ፣ አስገዳጅ እንዲሁም የከፋ ተጽእኖዎችን እየተጠቀመች እያደከመቻት ነው" ተብላለች።
ይህንን ሕግ የተላለፉ ከ250 ሺህ ዶላር በላይ ክፍያ ወይም የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
የአሜሪካ ዜግነት፣ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) ያላቸው ወይም ትክክለኛ ቪዛ ያላቸው አንድ መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ይፈቀድላቸዋል።
ሆኖም ሕጉን እየተቹ ያሉ አካላት ቻይናዊ በሙሉ ያልተገባ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ አድሏዊ አሠራርን የሚተገብር ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Office of the Texas Governor
'ቻይናውያንን ያገለለው ሕግ'
በአዲሱ ሕግ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱት የቻይና ዜጎች ናቸው።
በቴክሳስ ግዛት ውስጥ 120 ሺህ ትውልደ ቻይናውያን እንደሚኖሩ ከሁለት ዓመት በፊት የተሰበሰበ አሃዝ ያሳያል።
በቅርቡ ከቴክሳሰ ኤኤንኤም ዩኒቨርስቲ የተመረቀችው እና ሕጉን ተቃውማ በፍርድ ቤት ከከሰሱት መካከል አንዷ የሆነችው ኩዊንሊን ሊ "ሕጉ እጅጉኑ አስደንግጦኛል" ብላለች።
"ሰብዓዊ መብቶች የሉም ማለት ወደ ኋላ 150 ዓመታትን መመለስ ነው፤ ልክ እንደ የባቡር መንገድ ሥራ ላይ የነበሩ የቀን ሠራተኞች" ትላለች።
ፍርድ ቤት ሕጉ እሷን አይመለከታትም በሚል ክሷን ውድቅ ያደረገ ቢሆንም፤ አጠቃላይ ሂደቱ ግን በአእምሮ ጤናዋ ላይ ጉዳት አድርሶብኛል ትላለች።
"ብዙዎች እዚህ መጥተው እንዳይማሩ እንዲሁም እንዳይሰሩ ያግዳቸዋል። ምክንያቱም በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ማለፍ ፈታኝ ነው" ስትል ታስረዳለች።
ዩዋን ከሥራ ውጪ ጊዜውን የሚያሳልፈው ሕጉን ተቃውሞ በመሟገት ነው።
ሕጉ ከመጽደቁ በፊት በተለያዩ የአደባባይ ሰልፎች ተሳትፏል።
እንዲሁም የሕዝብ አስተያየት ለመስብሰብ ለተቋቋመው ኮሚቴ ይህ ሕግ ' ዘ ቻይኒዝ ኤክስክሉዥን አክት ኦፍ 2025' (ቻይናውያንን ያገለለው የ2025 ሕግ) ተብሎ ሊጠራ ይገባል ብሏል።
ይህ በአውሮፓውያኑ 1882 የወጣው እና 'ዘ ቻይኒዝ ኤክስክሉሽን አክት' የተሰኘውና ፀረ ቻይና የሆነውን ሕግን የሚያስታውስ ነው።
የዚያን ጊዜው አወዛጋቢ ሕግ ቻይናውያን የጉልበት ሠራተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የከለከለ ነው።
"ልክ እንደ እኔ ያሉ ሰዎችን በትውልድ አገራቸው ተመሥርቶ የቤት ባለቤት መሆን አይችሉም ብሎ ማገድ አድሏዊ አሠራር መሆኑ ግልጽ" ነው ይላል ዩዋን።
ዩዋን የሁለቱ ልጆቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሚያሳስበው የገለጸ ሲሆን፣ ለልጆቹ መታገል እንዳለባቸው እንደሚያስተምራቸው ያስረዳል።
የቻይና ኩባንያዎች ሌላ አማራጮች ይፈልጋሉ
ዩዋን አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደንበኞቹ የቻይና ስደተኞች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሕጉ ሊያስከትለው የሚችለው የንግድ ተጽእኖ ላይ ስጋት አድሮበታል።
እንደሱ ያሉ ትናንሽ የንግድ ተቋማት የቻይና ማኅበረሰብ የሚገለገልባቸው ናቸው።
በቴክሳስ ካሉ ትናንሽ የንግድ ተቋማት በተጨማሪ፣ ከቻይና የሚመጡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዚህ ሕግ መጎዳታቸው አይቀሬ እንደሆነም ዩዋን ያስረዳል።
ከአውሮፓውያኑ 2011 አስከ 2021 ባለው ወቅት 34 የቻይና ኩባንያዎች 2.7 ቢሊዮን የካፒታል ኢንቨስትመንት በማድረግ 4682 ሥራዎችን በቴክሳስ መፍጠር እንደቻሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዘገባ አመልክቷል።
አንዳንድ የቻይና ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት ከቴክሳስ ግዛት ውጪ አማራጮችን እየፈለጉ ነው ተብሏል።
በዳላስ የሪል ስቴት ወኪል የሆኑት ናንሲ ሊን በርካታ ቻይናውያን ደንበኞቻቸው የኢንቨስትመንት ዕቅዳቸውን እየተዉ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል በኤሌክትሪክ ተሽካርካሪዎች እና በፀሐይ ኃይል ዘርፍ የተሰማሩ ይገኙበታል።
"ይህ ጉዳይ እልባት ካላገኘ ለቻይና ኩባንያዎች ወደ ቴክሳስ ለመግባት በጣም ፈታኝ ይሆናል። ቀድሞውኑ በቴክሳስ የሊዝ ውል ያላቸው ማደስ አይችሉም፤ ከቻሉም ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ መሆን አለበት" ሲሉ ያስረዳሉ።
ለቻይና አሜሪካውያኑ የመሬት ባለቤትነት መብት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ የትግል ታሪክ ነው።
ቀደም ሲል በቴክሳስ አሜሪካዊ ዜግነት የሌላቸው መሬት እንዳይገዙ የሚገድበው የመሬት ሕግ እስከ አውሮፓውያኑ 1965 ድረስ በሥራ ላይ ነበር።
ነገር ግን ሕጉ አድሏዊ፣ ፀረ ልማት እና ምክንያታዊ ያልሆነ በሚል ተሽሮ ነበር።
ለአዲሱ ሕግ መነሻው ምንድን ነው?
የቴክሳስ ገዢ ግሬግ አቦት ዋነኛ ትኩረታቸው የቴክሳስ ነዋሪዎች ደኅንነት እና ፀጥታ ጉዳይ ነው ይላሉ።
ቢቢሲ የአስተዳደሪውን ቢሮ አስተያየት በጠየቀበት ወቅት ቻይናን ጨምሮ "ጠላት የሆኑ የውጭ ተገዳዳሪዎች በቴክሳስ የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ ሊፈቀድላቸው አይገባም" የሚለውን ከዚህ ቀደም የወጣ መግለጫ ልኳል።
ለዚህ ሕግ አጥብቀው ከተከራከሩት መካከል ወግ አጥባቂ የሆነው የቴክሳስ ፐብሊክ ፖሊሲ ፋውንዴሽን የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ) አባል የሆኑት ቸክ ደ ቮር አንዱ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት "ጠላት የሆኑ መንግሥታትን ከወታደራዊ ሰፈሮች፣ ከእርሻ መሬቶች እንዲሁም እንደ ላውግሊን ካሉ የአየር ኃይል ሰፈር እና መሠረተ ልማቶች ማራቅ ያስፈልጋል።"
ባለሥልጣናቱ ለዚህ ሕግ መነሻ የሚሉት ቻይናዊው ነጋዴ ሱን ጓንግከሲን በቴክሳስ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2016 አስከ 2018 ባለው ጊዜ የገዙት 60 ሺህ ገደማ ሄክታር መሬት ነው።
ይህ መሬት ከላውጊሊን አየር ኃይል ጣቢያ አጠገብ የሚገኝ እና ለነፋስ ኃይል ማመንጫነት ይውላል መባሉ አወዛጋቢ ሆኗል።
የመሬቱ ግዥ በአሜሪካ የውጭ ኢንቨስትመንት ኮሚቴ የጸደቀ ቢሆንም፣ ቴክሳስ ከአራት ዓመት በፊት ከአንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች ጋር "በወሳኝ መሠረተ ልማት" ላይ የሚደረጉ ስምምነቶችን የሚከለክል ሕግ አውጥታለች።
በዚህም የተነሳው የቻይናው ነጋዴ ፕሮጀክት እንዲሰረዝ ተደረገ።
ነጋዴው ሱን፣ የቻይና የኮሚኒስት ፓርቲ አባል እንዲሁም በቻይና ጦር ሠራዊት ውስጥ የቀድሞ ከፍተኛ መሪ ከመሆናቸው አንጻር ሌሎች የስለላ ዕቅድ ነበራቸው ሲሉ የቴክሳስ ሴናተር ጆን ኮርኒ ወንጅለዋል።
ሱን ለዚህም ምላሽ ሰጡ። በአንድ የንግድ ሥራ አስፈጻሚያቸው በኩል ባቀረቡት ክስ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህንን ፕሮጀክታቸውን ከብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ውጪ ማድረጋቸውን አሳይተዋል።
መቀመጫውን በዋሸንግተን ያደረገው የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2023 ባለው ወቅት ቻይና በአሜሪካ ላይ የሰለለችባቸው 224 ጉዳዮችን ማግኘቱን መረጃዎችን ዋቢ አደርጓል።
"እውነተኛ አደጋ ተደቅኗል" ይላሉ በቤይጂንግ የኤፍቢአይ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሆልደን ትሪፕሌት።
ነገር ግን የአሜሪካ የሲቪል ነጻነቶች ኅብረት ፋውንዴሽን ባልደረባ የሆኑት ፓትሪክ ቶሜይ ከአዲሱ የቴክሳስ ሕግ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ባለሥልጣናት በስህተት የቻይናን ሕዝብ ከቻይና መንግሥት ጋር አንድ እያደረጉት ነው ይላሉ።
"በቴክሳስ ውስጥ ቻይናውያን መኖሪያ ቤት ስላላቸው ወይም በመከራየታቸው በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ምንም ዓይነት መረጃ የለም" ይላሉ።
ብሔራዊ አዝማሚያ
በቻይና ላይ ያነጣጠረው ኤስቢ 17 በአሜሪካ የመጀመሪያው ሕግ አይደለም።
ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ በቻይና ላይ ያነጣጠሩ እና የውጭ ዜጎች የንብረት ባለቤትነትን የሚገድቡ 50 ሕጎች በአብዛኛው በሪፐብሊካን በሚመሩ 26 ግዛቶች መውጣታቸውን ኮሚቴ 100 የተሰኘው የቻይና-አሜሪካ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አስታውቋል።
እነዚህ አብዛኞቹ ሕጎች ያለፉት ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ ነው።
ወቅቱም የቻይና ተንሳፋፊ የስለላ ፊኛ በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ከተፈጠረው የአገራቱ ውጥረት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተነግሯል።
የትራምፕ አስተዳደር የቻይና ዜጎች በአሜሪካ የእርሻ መሬት እንዳይገዙ ለማገድ ማቀዱንም ገልጿል።















