ለ23 ሰዓታት፣ 16 ሺህ ኪሎሜትር ተጉዘው ከ60 ዓመታት በኋላ የተገናኙት ወንድማማቾች

ወንድማማቾቹ ሲገናኙ እንግዳ ስሜት እንዳልተሰማቸው ራሰል ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Family photo

የምስሉ መግለጫ, ወንድማማቾቹ ሲገናኙ እንግዳ ስሜት እንዳልተሰማቸው ራሰል ይናገራል።

በመካከላቸው ያለው ርቀት 16 ሺህ ኪሎሜትር ነው። ለመገናኘት 23 ሰዓታት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።

ለመገናኘት 60 ዓመታት ጠብቀዋል። ራሰል ጎውደር 64 ዓመቱ ነው። ታላቅ ወንድሙን ለመተዋወቅ ዓመታት ጠብቋል።

ደቡብ ዌልስ ከሚገኘው ቤቱ ወደ አውስትራሊያ ተጉዞ የ69 ዓመት ወንድሙ ፒተርን አግኝቷል።

ወንድማማቾቹ ሲገናኙ እንግዳ ስሜት እንዳልተሰማቸው ራሰል ይናገራል። "በደስታ ተሞላን" ይላል።

ወንድማማቾቹ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዋቅም ቀጠሮ ይዘዋል።

ጄይ እና ጂል ከተባሉ ወላጆቻቸው ለንደን ውስጥ ነበር የተወለዱት።

ጂል በ15 ዓመቷ ነበር ፒተርን የወለደችው። ጥንዶቹ ሳይጋቡ ነበር ልጁን የወለዱት። በ1950ዎቹ ሳያገቡ መውለድ ማኅበራዊ ነቀፋ ያስከትላል።

ስለዚህም ልጃቸውን በማደጎ ወደ አውስትራሊያ ላኩት። ፒተር አውስትራሊያ አደገ። ሬይ እና ጂል ተጋብተው ራሰልን ወለዱ።

ከዚያም ሕይወታቸው ስላለፈ ፒተር ስለ ወላጆቹ ማወቅ አልቻለም።

ፒተር ስለ ወላጆቹ ያወቀው ከማደጎ እህቱ ነበር። ከዚያም የልጅ ልጁ ወንድሙ ራሰልን አፈላልጋ አገኘች።

ወንድማማቾቹ የሥጋ ዘመድ መሆናቸው በዘረ መል ምርመራ ተረጋግጧል።

የራሰል እህት ወንድም እንዳለው ነግራዋለች። እናቱ ግን ስለ ወንድሙ ፒተር አውርታ አታውቅም።

እናቱ በካንሰር ልትሞት ጥቂት ጊዜ ሲቀራት "ልነግርህ የምፈልገው ነገር አለ" አለችው።

እውነታውን ሳትነግረው ሞት ቀደማት። "እናቴ በነገሩ እንዳዘነች አምናለሁ። እውነታውን ግን ሳላውቅ ቆይቻለሁ" ይላል።

ጄይ እና ጂል ከተባሉ ወላጆቻቸው ለንደን ውስጥ ነበር የተወለዱት።

የፎቶው ባለመብት, Supplied

የምስሉ መግለጫ, ጄይ እና ጂል ከተባሉ ወላጆቻቸው ለንደን ውስጥ ነበር የተወለዱት

እናቱ የበኩር ልጇን በማደጎ ሰጥታ እንዴት ለዓመታት እንደኖረች ጥያቄ ሆኖበታል። ምሥጢሯን የተናገረቸውም ለሴት ልጇ ነበር።

"ልጇን አጥታ እንዴት ለዓመታት እንደኖረች አላውቅም። በየቀኑ ስለ ልጇ ታስብ ነበር ማለት ነው። ልጄ ትምህርት ቤት የገባበት ቀን ምን ይመስላል? ልጆች ወልዶ ይሆን? የሚሉትን ማሰብ ለእሷ ከባድ ነበር" ይላል ራሰል።

ራሰል ባለ ትዳር እና የልጅ አባት ነው። አውስትራሊያ ተጉዞ ለዓመታት ያላየውን ወንድሙን አግኝቷል።

ወንድማማቾቹ በአስደናቂ ሁኔታ ተመሳሳይ ተክለ ሰውነት አላቸው።

ፒተር ቤት ሲገናኙ መጀመሪያ ላይ ተጨባበጡ። በአካል እንዲገናኙ ያገዟቸው ዘመድ አዝማዶች ቅጽበቱን በካሜራ ቀርጸው አስቀርተዋል።

ወንድማማቾቹ

የፎቶው ባለመብት, Family photo

የምስሉ መግለጫ, የወንድማማቾቹ 17 ቤተሰቦች ገናን አብረው ለማክበር ቀጠሮ ይዘዋል

የወንድማማቾቹ 17 ቤተሰቦች ገናን አብረው ለማክበር ቀጠሮ ይዘዋል።

ራሰል ወንድሙን ለማግኘት ዓመታትን ጠብቋል። ፒተር ለማደጎ መሰጠቱ ቅያሜ እንዳልፈጠረበት ተናግሯል።

"ደም ቢያስተሳስረንም የተለያየን ሰዎች ነን። በሌላኛው የዓለም ክፍል በተለየ መንገድ ነው ያደገው" ይላል ፒተር።

ምናልባት ስንገናኝ ምቾት የሚነሳ ነገር ይኖር ይሆን? ብለው መስጋታቸው አልቀረም። ነገር ግን "ተፈጥሯዊ ስሜት" እንደተሰማቸው ይናገራሉ።

ራሰል ፒተርን ሲያገኘው "እናታችን በሕይወት ብትኖር ኖሮ 85 ዓመት ይሞላት ነበር" ሲለው ሁለቱም ስሜታዊ ሆነዋል።

"እናታችን 85ኛ ዓመቷን ታከብር በነበረበት ዕለት እኔ እና ወንድሜ ተገናኝተን ጥሩ ጊዜ ማሳለፋችን የአጋጣሚ ጉዳይ ነው" ይላል።

ግን ደግሞ "የእጣ ፈንታ ጉዳይ" እንደሆነም ይገምታሉ።

"ልጆቿ ቢራ እየጠጡ ሲያወሩ ማየት ያስደስታታል። የእጣ ፈንታ ነገር ሆኖ ነው እንጂ ወንድም እንዳለኝ ሳላውቅ ሙሉ ሕይወቴን እኖር ነበር" ይላል ፒተር።

ለዓመታት ያልተገናኙት ወንድማማቾች ሦስት ሳምንት በቂ ነው ብለው አያስቡም።

ራሰል "ሕይወቴ ተለውጧል" ይላል።

"ጥሩ ጊዜ ላይ ነው የተገናኘነው። ገና አብሮ ማክበር ያስደስታል። ከወንድሜ ጋር ሥጋ ጥብስ ልበላ ነው ብዬ እንደማወራ አስቤ አላውቅም ነበር። ለማመን ይከብዳል" ሲልም ያክላል።