ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የልጄ እና የእናቴ የመቃብር መስቀሎች ተሰርቀዋል"- በታንዛኒያ የመካነ መቃብር መንታፊዎች የፈጠሩት ቁጣ
በታንዛኒያ ምሥራቃዊ ሞሮጎሮ ከተማ የሚገኝ መካነ መቃብር ወድሟል።
በአንዳንዶች መቃብር ላይ የብረት መስቀል የነበረበት ክፍተት አለ፤ ሌሎች ደግሞ ዘራፊዎች ለነጋዴዎች ለመሸጥ ለማንሳት ሞክረው ያልተሳካላቸው ቦታ ላይ ሃይማኖታዊ ምልክቶች ታጥፈዋል።
በኮላ ማዘጋጃ ቤት ትንሽ መካነ መቅብር ክፍል ብቻ ከ250 በላይ የዝርፊያው ዒላማ ተደርገዋል።
ወንጀሎቹ በአብዛኛው የሚከሰቱት በሌሊት ምንም አይነት ደህንነት በማይኖርበት ጊዜ እና የመቃብር ሰራተኞች በሌሉበት ነው።
ቤተሰቦችን ለድንጋጤ መካነ መቃብሮቹን ደግሞ ለውድመት የዳረጉት ክስተቶች ቁጣን ቀስቅሰዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ፑደንሲያና ቹምቢ የሴት ልጇን እና የእናቷን መቃብር ለመጎብኘት በወር አንድ ጊዜ ወደ መካነ መቃብር ትሄድ ነበር፤ እና በጭንቀትዋ ሁለቱም ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ ብዙ ጊዜ ረክሰዋል።
የመጀመሪያው ዒላማ የተደረገው እ.አ.አ በ2000 የሞተችው የእናቷ መቃብር ነው።
በ2021 መገባደጃ ላይ ቤተሰቡ የተሰረቀውን መስቀል ለመተካት ገንዘብ ካጠራቀመ ከጥቂት ወራት በኋላ እ.አ.አ በ1997 በ15 ዓመቷ የሞተችው የልጇ መቃብር በዘራፊዎች ጉዳት ደርሶበታል።
ይባስ ብሎ ወይዘሮ ቹምቢ የልጇ መቃብር ላይ ያለውን መስቀል ለማስተካከል ከመወሰኗ በፊት፣ በእናቷ መቃብር ላይ ያለው አዲሱ መስቀል በዘራፊዎች ተመነተፈ።
ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ በመጋባት ውስጥ፣ የልጇን መስቀል ለመተካት ብረት አማራጭ እንዳልሆነ ተሰማት።
"ይህ የልጄ መቃብር ነው፤ አራተኛ ልጄ" አለች ወደ ኮንክሪት መስቀሉ እያመለከተች።
በዚህ የታንዛኒያ ክፍል የብረታ ብረት ፍላጐት እየጨመረ በመምጣቱ መስቀል እና ምልክቶችን ከመቃብር ላይ መስረቅ አሳሳቢ ሆኗል።
ወይዘሮ ቹምቢ "ይህን የሚያደርጉ ሰዎች የተረገሙ ናቸው ምክንያቱም ሁሉም ሰው በሚሆነው ነገር አዝኗል" ስትል ለቢቢሲ ቃሏን ሰጥታለች።
"አሁን መቃብሮችን ለመጠበቅ ክፍያ የሚጠይቁ አንዳንድ ወጣቶች አሉ በተለይም ሸክላ ያላቸው።"
የወ/ሮ ቹምቢ ወንድም አውጉስቲን ሬሚ፣ መላውን ማኅበረሰብ ያሳዘነ ነው ብሏል።
"ይህ በጣም ነውር ነው…እነዚህ መከበር የሚገባቸው አካባቢዎች እንደዚህ አይነት መጥፎ ድርጊት ሲፈጸምባቸው በእውነት በጣም ያማል።" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የመቃብር ስርቆቱ በአንዳንዶች ገንዘብ ለማግኘት ቅዱሳን ቦታዎችን እስከ ማርከስ የደረስ የሞራል ሕግጋት እስከ መጣስ የሚደርስ ያለውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያሳያል።
ወንጀለኞቹ በኪሎ ግራም ከ700 እስከ 870 የታንዛኒያ ሽልንግ ማግኘት ይችላሉ።
እዚህ ግባ የሚባል ገንዘብ አይደለም ነገር ግን ለአንድ ሰሃን ምግብ ወይም በአካባቢው የተሰራ አልኮል ለመግዛት በቂ ሊሆን ይችላል።
"የብረታ ብረት ነጋዴዎች ብዙ ጊዜ የሚገዙት ምንም አይነት ጥያቄ ሳይጠይቁ ነው" ሲል ለቢቢሲ የተናገረ አንድ ሰው ከመቃብር ላይ መስቀሎችን ሰርቆ ለብረታ ብረት ገበያ መሸጡን ተናግሯል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ግለሰብ መንታፊዎቹ መስቀሎቹን ወደ ብረት ነጋዴዎች ከመውሰዳቸው በፊት በመጀመሪያ ወደ ብየዳዎች እንደሚወስዱ እና ወደ ቁርጥራጭነት እንደሚቀይሯቸው ገልጿል።
ነጋዴዎቹ ራሳቸው ርካሽ የተሰረቁ ዕቃዎችን የመግዛት ወይም ሕጉን የመከተል ምርጫ ይገጥማቸዋል።
በሞሮጎሮ ከተማ መሀል የሚኖረው ኢዚሬ ራማድሃኒ በ2023 ከሌሎች የቆሻሻ ነጋዴዎች ጋር አንድ ሰው የተሰረቀ መስቀል ሊሸጥ ሲሞክር እንዴት እንደያዘ እና ለባለሥልጣናት ሪፖርት እንዳደረገ ያስታውሳል።
"ቀደም ሲል መስቀሎችን ያመጡልን ነበር። ነገር ግን ከመካከላቸው አንዱን ወደ ፖሊስ ወሰድን በኋላም የሶስት አመት ተኩል እስራት ተፈርዶበታል - ከዚያ በኋላ ስርቆቱ ቀንሷል አሁን ግን ተመልሷል" ሲሉ ሚስተር ራማድሃኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተሰረቀ ዕቃ እንደማይገዛ አጥብቆ ይናገራል።
"እዚህ መስቀል ከመጣ ሊሸጥልን የመጣው ሰው ችግር ውስጥ ይወድቃል ምክንያቱም ወደ ፖሊስ እንወስደዋለን"
ሌቦች በቀላሉ ለሌሎች ገዥዎች የሚሸጡ እንደ ሸክላ እና የእብነበረድ ማስጌጫዎች ያሉ ሌሎች የመቃብር ምልክቶች ላይ ማነጣጠር ጀምረዋል።
የሞሮጎሮ ጤና ጥበቃ ኦፊሰር የሆኑት ዶ/ር ንዲሚሌ ኪላቱ እንደተናገሩት የከተማው ባለስልጣናት አጥር እና ጠባቂዎችን በመመደብ የመቃብር ጥበቃን ለማሻሻል አቅደው ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሀብት እና ጊዜ ይጠይቃል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ።
"ዛሬ ወይም ነገ ማድረግ የምንችለው ነገር አይደለም"
የቁርጥራጭ ብረታ ብረት ነጋዴዎችን እንደ የመቃብር ምልክት እና የባቡር ሐዲድ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን መግዛት እንደማይገባቸው ለማስተማር ሃሳብ መኖሩን ጠቅሰዋል።
ለወንጀሎቹ ምላሽ የሰጠው የታንዛኒያ መንግሥት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪን ለመቆጣጠርም ቃል ገብቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶቶ ቢቴኮ የንግድ ፈቃድ ያላቸው የንግድ ድርጅቶች ህጎችን እና ደንቦችን እንዲያከብሩ አፅንዖት ሰጥተዋል።
"የሚፈለገው ያንን ለማስፈጸም እና ህዝቡ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዲማር ማድረግ ብቻ ነው። ህዝባችንን በማስተማር መሠረተ ልማቶቻችንን ከአደጋ ለመጠበቅ እንቀጥላለን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኃይማኖት አባቶችም ተከታዮቻቸው እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል የበለጠ እንዲተጉ ተማጽነዋል።
በሞሮጎሮ የሚገኙት ፓስተር ስቲቨን ሚሲጋራ ወጣቶች የተቀደሱ ቦታዎችን የማክበር አስፈላጊነት ላይ ለማስተማር የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
"በጋራ ክብራቸውን መመለስ አለብን፣ አንዳንድ ወጣቶች ለመጥፎ ተግባር እንደሚጋለጡ እናውቃለን ነገ ርግን ወደ ትክክለኛው መስመር ልንመልሳቸው እንችላለን" ብለዋል።