የዩናይትድ ድል፣ የሊቨርፑል እና የኤቨርተን አስደናቂ ሽንፈት

ማርከስ ራሽፈርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አራተኛ ሳምንት የቅዳሜ መርሃ ግብር አስደናቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነበር።

በመጀመሪያው የምሳ ሰዓት ጨዋታ ወደ ሳውዝሃምፕተን ያቀናው ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል።

በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ቅርፅ አልባ የነበረው ዩናይትድ በስድስት ደቂቃዎች አከታትሎ ባስቆጠራቸው ግቦች የሳውዝሃምፕተንን ስታድየም ጭጭ አሰኝቷል።

ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች እረፍት በፊት በሊቨርፑል በገዛ ሜዳው ተረትቶ የነበረው ዩናይትድ አስፈላጊ የሚመስል ሦስት ነጥብ ይዞ ነው የተመለሰው።

ሳውዝሃምፕተኖች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት የዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ያዳናት ሲሆን፣ ቀያዮቹ ሰይጣኖችን ያነቃቃች ነበረች።

ማቲያስ ደ ሊክት በማንቸስተር ማሊያ የመጀመሪያ ግቡን በማስቆጠር የኤሪክ ቴን ሀግን ቡድን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ማርከስ ራሽፈርድ ከፍፁም ቅጣት ምት ስፍራ ውጪ የመታት ኳስ ቋሚውን ጨርፋ መረብ ላይ ማረፍ ችላለች።

ሁለት ለምንም እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል የገቡት ዩናይትዶች በሁለተኛው አጋማሽ የኳስ እንቅስቃሴን ተቆጣጥረው በልበ-ሙሉነት ሲጫወቱ ታይተዋል።

የሳውዝሃምፕተኑ አምበል ጃክ ስቴፈንስ የዩናይትዱ አሌሀንድሮ ጋርናቾ ላይ በፈፀመው ጥፋት በቀይ ካር ከሜዳ ከተሰናበተ በኋላ በጭማሪ ደቂቃ ጋርናቾ ኳስ እና መረብ በማገናኘት የዩናይትድን ድል አረጋግጧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ኦልድ ትራፈርድ ተጉዘው ዩናይትድን 3 - 0 የረቱት ሊቨርፑሎች ‘የጫጉላ ጊዜያቸው’ አብቅቷል።

አሠልጣኝ አርን ስሎት የመጀመሪያውን ሽንፈት ሲቀምሱ፣ ኖቲንግሀም ፎረስት ከ54 ዓመታት በኋላ በአንፊልድ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

የአሠልጣኝነት መንበሩን ከየርገን ክሎፕ የተረከቡት አርን ስሎት የመጀመሪያዎቹን ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን አንድም ግብ ሳይቆጠርባቸው ነው እዚህ የደረሱት።

ኖቲንግሀም ፎረስት በካለም ሀድሰን-ኦዶይ ግሩም ጎል ሊቨርፑልን በሜዳ መርታቱን ተከትሎ የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን የአሠልጣኙ “የጫጉላ ጊዜ” አብቅቷል ብሏል።

ሊቨርፑል የፎረስትን ተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኖት ታይቷል። አንድ ጨዋታ ሳይሸነፍ እዚህ የደረሰው ሊቨርፑል ክብረ-ወሰኑ ባጭሩ የተቀጨ ሲሆን፣ ፎረስት ደግሞ ግስጋሴውን ቀጥሏል።

በሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ኤቨርተን አስደናቂ የሽንፈት ታሪክ ሲያስመዘግብ ቼልሲ ድል ቀንቶታል።

ኤቨርተን በመጀመሪዎቹ 30 ደቂቃዎች በማክኒል እና ካልቨርተን ሉዊን ጎሎች አስተን ቪላን በሜዳው 2 ለምንም መምራት ችሎ ነበር። ነገር ግን በ36ኛው ደቂቃ ዋትኪንስ ያስቆጠራት ኳስ ለቪላዎች ተስፋ ሰጥታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ በ58ኛው ደቂቃ ዋትኪንስ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ በማከል ኤቨርተን ላይ ጫናውን አበረታ። ጨዋታው ሊገባደድ ሩብ ሰዓት ገደማ ሲቀሩት ፈረንሳዊው ጆን ዱራን በግራ እግሩ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ የኤቨርተንን ልብ ሰብራለች።

ኤቨርተን በሁለት ተከታታይ ሳምንታት 2 ለባዶ እየመራ በመሸነፍ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። አልፎም በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፈው ከ66 ዓመታት በኋለ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

መሪው ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ብሬንትፈርድን በመርታት የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ቼልሲ ደግሞ በንኩንኩ ግብ ቦርንመዝን ማሸነፍ ችሏል።

ዛሬ እሑድ 10፡00 ሰዓት ተጠባቂው የሰሜን ለንደን ደርቢ በቶተንሀም ሜዳ ይደረጋል። ኦዴጋርድ እና ራይስን ያጣው አርሰናል ከስፐርስ ፈተና ይጠበቅዋል ተብሎ ተገምቷል።