ደቡብ ኮርያ፤ ሰሜን ኮርያ ተጨማሪ የኒውክሌር መሳሪያ እንዳታመርት የሚደረግ ስምምነትን እንደምትቀበል ገለጸች

የደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት፤ ሰሜን ኮርያ ያሏትን የኒውክሌር መሳሪያዎች በማስወገድ ፋንታ ተጨማሪ የማምረት ተግባሯን እንድታቆም በዶናልድ ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን መካከል የሚደረግ ስምምነትን እንደሚቀበሉ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ምያንግ፤ ሰሜን ኮርያ በዓመት ከ15 እስከ 20 ተጨማሪ የኔውክሌር መሳሪያ እያመረተች እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ተጨማሪ መሳሪያዎችን ማምረት እንድታቆም ማድረግ ሙሉ በሙሉ የኒውክሌር መሳሪያ እንዳይኖራት ከማድረግ አንጻር "ተጨባጭ እና ትክክለኛ ጊዜያዊ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ" እንደሆነም ገልጸዋል።
ሰሜን ኮርያ ራሷን የኔውክሌር ኃይል ባለቤት አድርጋ ያቀረበቸው በአውሮፓውያኑ 2022 ሲሆን መሳሪያዎቿን በጭራሽ እንደማታስወግድም ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም ፒዮንግያንግ የኒውክሌር መሳሪያዎችን እንድታስወገድ የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም። ከ2019 ጀምሮም ወደ ንግግር ለመመለስ የቀረቡላትን ጥሪዎች አልተቀበለችም።
የደቡብ ኮርያው ፕሬዝዳንት፤ "ኒውክሌርን የማስወገድ የረጅም ጊዜ ግባችንን ጭራሹኑ ባንተውም፤ ሰሜን ኮርያ ኒውክሌር እና ሚሳኤል የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ማድረግ ግልፅ ጥቅሞች እንዳሉት አምናለሁ" ብለዋል።
"ጥያቄው የመጨረሻ ግብ [በሆነው ኒውክሌርን ማስወገድ ላይ] ፍሬ አልባ የሆነ ሙከራ እያደረግን እንጸናለን ወይስ ተጨባጭ ግብ አስቀምጠን፤ የተወሰነውን እናሳካለን የሚል ነው" ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል።
ባለፈው ሰኔ ወር ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ሊ፤ ከሰሜን ኮርያ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመስረት እና ውጥረቶችን ማርገብ ይፈልጋሉ። ባለፈው ዓመት ሀገሪቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በማስገባታቸውን ከመንበራቸው በተነሱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዩዌል የስልጣን ዘመን የሁለቱ ሀገራት ውጥረት ተካርሮ ነበር።
አዲሱ ፕሬዝዳንት፤ አሜሪካው መሪ ዶናልድ ትራምፕ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር የኒውክሌር ንግግርን በድጋሚ እንዲያስጀምሩ ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2019 በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ከሰሜን ኮርያ ጋር ይህንን ንግግር ማድረግ ጀምረው የነበረ ቢሆንም ሰሜን ኮርያ የኒውክሌር ተቋማቷን እንድታፈርስ በዋሽንግተን መጠየቋን ተከትሎ ተቋርጧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ሊ በበኩላቸው ትራምፕ እና ኪም "በተወሰነ ደረጃ የእርስ በእስር መተማመን ያላቸው እንደሚመስል" በመጥቀስ ሁለቱ መሪዎች በድጋሚ ለንግግር እንዲቀመጡ ማድረግ ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ ደቡብ ኮርያን እንደሚጠቅም እንዲሁም ለዓለም ሰላም እና ደህንነት አስተዋጾ እንደሚያደርግ አክለዋል።
ደቡብ ኮርያ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ነች። ምክር ቤቱ በኒውክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት ሰሜን ኮርያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ለዓመታት ያደረጋቸው ጥረቶች በቻይና እና ሩሲያ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።
በዚህ የተነሳ የጸጥታ ምክር ቤቱ ለደቡብ ኮርያ ሊቆም አልቻለም ብለው ያስቡ እንደሆነ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ሊ፤ በቀጥታ ከመመለስ ተቆጥበዋል።
"የተባበሩት መንግሥታት እውነተኛ ሰላም ያለባት ዓለም ለመፍጠር አለመቻሉ ግልጽ ቢሆንም፤ አሁንም ቢሆን በርካታ ወሳኝ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል። ጸጥታ ምክር ቤቱ ላይ ሪፎርም የማድረግ ሀሳብን "እምብዛም ተጨባጭ ያልሆነ" መሆኑን አክለዋል።
ቻይና የሰሜን ኮርያ የኒውክሌር ፕሮግራም እውን እንዲሆን እየተባበረች እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዝዳንት ሊ፤ "ለማወቅ አደጋች ነው" ሲሉ መልሰዋል። አሁን ባላቸው መረጃ መሰረት ግን ቻይና ድጋፍ እያደረገች ነው ብለው እንደማይረዱ ጠቁመዋል።















