ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታጣቂዎች ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለው፤ ስድስት ነዋሪዎች ታገቱ
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን እና ሕጻናትን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መታገታቸውን የሟች ቤተሰቦች፣ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣን ገለጹ።
ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለስልጣን፤ የቅማንት ማኅበረሰብ መኖሪያ በሆነው ጎዶ ሞላሊት ቀበሌ ለተፈጸመው ጥቃት "የፋኖ" ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
ታጣቂዎች፤ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ በሚገኘው ጎዶ ሞላሊት ቀበሌ ጥቃት የከፈቱት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እንደሆነ አምስት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በታጣቂዎቹ ጥቃት ሁለት ሴት ልጆቻቸው የቆሰሉባቸው ቄስ መላክ አምላኩ የተባሉ የቀበሌው ነዋሪ፤ መጀመሪያ የተኩስ ድምጽ የሰሙት ንጋት ላይ የከብቶች በረት ለመክፈት ከቤታቸው ሲወጡ እንደነበር ገልጸዋል።
ታጣቂዎች በቀበሌዋ ነዋሪዎች ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት እንደ "ብሬን እና ዲሽቃ" ያሉ ከባድ መሳሪያዎችን ተጠቅመው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ነዋሪዎች እና የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ፀጋ እንዳሉት በዚህ ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።
አንዲት የቀበሌው ነዋሪ በበኩላቸው ከጥቃቱ በኋላ ማክሰኞ ወደ አካባቢው የተመለሱ ወጣቶች ተጨማሪ የአራት ሰዎች አስከሬን እንዳገኙ አስረድተዋል።
እንደ ቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ገለጻ ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ አምስቱ በቀበሌው የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል ከታጣቂዎች ጋር "ሲታገሉ የነበሩ" መሳሪያ የታጠቁ ነዋሪዎች ናቸው። ከቀሪዎቹ ንጹሃን ሟቾች መካከል ደግሞ "የ18 ዓመት ሴት እና ከ15 እስከ 18 ዓመት የሚሆነው ዲያቆን" እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም አንዲት ሴት እና አንድ ዲያቆን መገደላቸውን ተናግረዋል። በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ብዛት 16 እንደሆነ የሚናገሩት የዝባለም ደረጄ የተባሉ አንዲት የቀበሌው ነዋሪ፤ ከሟቾቹ መካከል ወንድማቸው፣ የወንድማቸው ልጅ እና የአጎታቸው ልጅ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
"የአጎቴ ልጅ ሲዋጋ ነበር፤ እነዚያን [ወንድም እና የወንድም ልጅ] ግን ዝም ብለው በአፈና ነው የገደሏቸው" ሲሉ ሁለት ዘመዶቻቸው ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ መገደላቸውን አስረድተዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚናገሩት ቢያንስ ከአራት እስከ ስድስት የሚሆኑ ሰዎች በጥቃቱ ቆስለዋል። ከቆሰሉት ነዋሪዎች መካከል የ12 እና 16 ዓመት ሴት ልጆቻቸው እንደሚገኙበት ቄስ መላክ ተናግረዋል።
"የ12 ዓመቷ የተመታችው ጀርባዋን ነው። እርሳሱ አልወጣም ተብሎ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ገብታለች። ያችኛይቱ ከመዳፏ ዝቅ ብሎ እጇን ነው [የተመታችው]፤ አጥንቱን አድቅቆታል" ሲሉ በልጆቻቸው ላይ ደረሰውን ጉዳት ገልጸዋል።
ጎረቤታቸው የሆኑ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ቄስ ባለቤት ከእነ ልጃቸው በታጣቂዎች መወሰዳቸውንም አስረድተዋል።
ቢቢሲ ያነገገራቸው አምስት ነዋሪዎች ስድስት ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ልጆቻቸውን የያዙ ሁለት እናቶች እንደሚገኙበት አረጋግጠዋል።
የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት፤ "[ከታገቱት] አንዷ የሦስት ወይም ሁለት ዓመት ከምናምን ልጅ ያዘለች ነች፤ ሌላኛዋ ከእነ ልጇ የታገተች የአራት፣ አምስት ዓመት የሚሆን ልጅ የያዘች ነች" ብለዋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ከከፈቱ በኋላ በቀበሌው ሁለት ጎጦች የሚገኙ ቤቶችን በእሳት ማቃጠላቸውን እና ከብትን ጨምሮ የቀበሌው ነዋሪዎች ንብረቶችን መዝረፋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት "የቆጠርናቸው የተቃጠሉ ቤቶችን ብዛት 105" ነው ብለዋል።
የቁም እንስሳት እና ፍየሎችን ጨምሮ "2,500" እንስሳት መዘረፋቸውንም ገልጸዋል። እንደ ቀበሌው አስተዳዳሪ ገለጻ ጥቃቱ የቆመው የመከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል አድማ ብተና አባላት ወደ አካባቢው መንቀሳቀሳቸው ከተሰማ በኋላ ነው።
ሦስት የአካባቢው ነዋሪዎች በአካባቢው ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት በጎዶ ሞላሊት ቀበሌ አጎራባች አካባቢዎች ይገኛሉ ያሏቸውን "የፋኖ ታጣቂዎችን" ነው። ሁለት ነዋሪዎች በበኩላቸው "አድማ በታኝ ነው" ሲባል መስማታቸውን ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው "በፋኖ ታጣቂዎች" እንደሆነ የሚናገሩት የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት፤ ይህንን አይቀበሉትም።
ዋና አስተዳዳሪው፤ "የአድማ ብተና እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አካባቢ የደረሱት ጥቃት እየተፈጸመ ስለመሆኑ ለጭልጋ ወረዳ እና ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ከተገለጸ በኋላ" እንደሆነ ያስረዳሉ።
ጥቃት የደረሰበትን ጎዶ ሞላሊት ቀበሌ የሚያዋስኑት ወንበልሰክ፣ ሻርዳ፣ እንግድባ እና ሚኒባስክ ቀበሌዎችን "የሚቆጣጠሩት የፋኖ ታጣቂዎች" መሆናቸውን በመግለጽ፤ እኚህ ታጣቂዎች ጥቃቱን ፈጽመዋል የሚል መከራከሪያቸውን ያጠናክራሉ።
የጭልጋ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት ትናንት [ማክሰኞ] ባወጣው መግለጫ፤ በቀበሌው ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ ያደረገው "በፋኖ ጭምብል የተደራጀው ፅንፈኛ እና ዘራፊ ቡድን" ሲል የጠራውን አካል ነው።
በቀበሌው ንፁሃን አርሶአደሮች፣ አቅመ ደካማ አረጋውያን እና ሕፃናት ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ፣ የሃብት እና ንብረት ዘረፋ" መፈጸሙን አስታውቋል።
የወረዳው መግለጫ፤ "እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ስምንት ንፁሃን አርሶ አደሮች የሞቱ፣ አምስት የቆሰሉ እንዲሁም ስድስት ታፍነው የሄዱ ንፁሃን አርሶ አደሮች ግፍ እና በደል እንደደረሰባቸው [...] ልናሳወቅ እንወዳለን" ብሏል።
የወረዳው አስተዳደር፤ "ይህ ፅንፈኛ ቡድን ከዚህ በፊት ተፈጥሮ የነበረው የብሔር ግጭት እንዲነሳ በቀጠናው በንፁሃን ላይ መጠነ ሠፊ ግፍ ሲፈፅም ቆይቷል" ሲል ወንጅሏል።
በማዕከላዊ ጎንደር እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ "አጎራባች ቀበሌዎች የሚኖሩ የአማራ እና የቅማንት ማኅበረሰብን ከአሁን ቀደም ተፈጥሮ የነበረውን የብሔር ግጭት መልሶ እንዲከሰት የሚፈልጉ ፅንፈኛ አካላት" አሉ ሲልም ከስሷል።
የወረዳው አስተዳደር፤ "የሁለቱ ዞን አስተዳደር አካላት እና የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሕግ በማስከበር የንፁሃን አርሶ አደሮቻችን ሞት፣ የንብረት ውድመት እና መፈናቀል ሊታደጋቸው እንደሚገባ ልናሳስብ እንወዳለን" ብሏል።